✍️ ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር
እየጻፍኩት ባለው መጽሐፍ ውስጥ እኔው የፈጠርኩት "ዓለምነህ" የተባለው አንዱ ገጸ ባሕሪ በፍጹም እየተግባባን አይደለም። እያፈነገጠ አስቸገረኝ። ከገጽ መሀል ቀድጄ ላወጣው ሳስብ እራሱ ዓለምነህ እንዲህ እያለ ምገተኝ፦
"የፈጠርከኝ ገጸ-ባሕሪ ብቻ ሳልሆን የገዛ ነፍስህ ውስጥ ያለሁ ጥልቅ ጥያቄ ሆኜ ብቅ ያልኩኝ ነኝ። ለአንተ "የሀሳብ ወንበዴ" ልመስልህ እችላለሁ። አንተ ብቻ አይደለህም ደራሲያን ብዙ ጊዜ ገጸ - ባሕሪያቸው የራሳቸውን ሕይወት ዘርተው ሲያምጹባቸው "ተቆጣጠርኳቸው" ይሉና ይገድሏቸዋል፤ እውነቱ ግን ገጸ-ባሕሪው ከደራሲው ምናብ አልፎ የእውነትን ነርቭ ሲነካ መገላገያ መንገዱ እሱን ነቅሎ መጣል ሳይሆን፣ እሱ የከፈተውን የሀሳብ በር ተከትሎ መጓዝ ነው።" አለኝ።
የሚለውን ስሙና "ይዳኘኝ ያየ" ማለቴ "ይዳኘኝ ያነበበ" ብዬ ለብይን ወደ እናንተ መጣሁ
መምህር ኃይለ መለኮት፦ (በቁጭት) "ዓለምነህ፣ አንተ የምትለው እኮ ጥልቁን የሰው ልጅ ውድቀት ወደ ድል ለመቀየር መሞከር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው አዳም የታዘዘውን ሕግ በመተላለፉ ከክብሩ ተዋረደ። ሞትና መከራ ወደ ዓለም የመጡት በዚህ እምቢተኝነት ነው። ይህንን "የንቃተ-ህሊና ሽግግር" ብሎ መጥራት እባቡ በገነት የተጠቀመበትን ያንኑ አታላይ ቋንቋ እንደመድገም አይቆጠርም?"
ዓለምነህ ፦ (በተረጋጋ ድምፅ) መምህር፣ እኔ የምለው አዳም "ተሳሳተ" ሳይሆን "መረጠ" ነው። እስቲ አስበው፣ አዳም በገነት ውስጥ የነበረው ኑሮ የአንድ ትልቅ የአትክልት ስፍራ ጠባቂነት እንጂ የሰውነት (Humanity) ኑሮ አልነበረም። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በአምሳሉና በምሳሌው ከሆነ፣ የመፍጠርና የመወሰን ባሕርይ ሊኖረው ይገባል። በገነት ውስጥ ግን አዳም ምንም ነገር አይወስንም፤ ሁሉም ነገር ተወስኖለታል። ዕፀ በለስን እንዳይበላ እንኳን ተወስኖበታል። መብላቱ ግን ከፈጣሪው ጋር ለመለያየት ያደረገው የመጀመሪያው "የጉልምስና" ውሳኔ ነው።
መምህር ኃይለ መለኮት፦ (እየተቃወሙ) ግን ያ ውሳኔ እኮ እርግማንን አመጣ! "በግንባርህ በላብህ ወዝ ብላ" ተባለ። "ወደ መሬት ትመለሳለህ" ተባለ። ይህ እንዴት ምርቃት ሊሆን ይችላል? ሰላምን አጥቶ ወደ ጦርነት፣ ህይወትን አጥቶ ወደ ሞት መውረድ እንዴት ታላቅነት ይሆናል? አዳም ገነትን ያጣው ባለመታዘዝ በኩራትና በትዕቢት እንጂ በጥበብ አይደለም።
ዓለምነህ፦ ልክ ነህ መምህር፣ ላብና ሞት መጡ። ነገር ግን ላብ ባለበት "ፈጠራ" አለ። ሞት ባለበት "ትርጉም" አለ። በገነት ውስጥ አዳም ቢቆይ ኖሮ፣ ዛሬ የምናያቸው ጥበቦች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ እና አንተ ራሱ የምታስተምረው ነገረ-መለኮት አይኖሩም ነበር። ምክንያቱም አስፈላጊነት (Necessity) የፈጠራ እናት ነች። አዳም ከገነት ሲወጣ "ፍጡር" መሆኑ አብቅቶ "ታሪክ ሰሪ" ሆነ። እግዚአብሔር አዳምን የባረረው ስላልወደደው ሳይሆን፣ አዳም የገዛ እጆቹን ተጠቅሞ የራሱን ዓለም እንዲሰራ ፈቃዱ ስለነበረ ነው።
መምህር ኃይለ መለኮት፦ (በጥልቀት እያሰቡ) አንተ የምትለው አዳም "አመጸኛ ጀግና" (Rebellious Hero) ነው እያልከኝ ነው። ነገር ግን ያለ ፈጣሪ እርዳታ ሰው የራሱን ገነት መገንባት እንደማይችል ታሪኩ ያስተምረናል። ከገነት መውጣት ማለት ከብርሃን ወደ ጨለማ መግባት ነው። አዳም ከወጣ በኋላ ወንድም ወንድሙን ገደለ፣ ዓለም በክፋት ተሞላች። ይህ ነው "ታሪክ ሰሪነት"?
ዓለምነህ፦ (ፈገግ ብሎ) መምህር፣ ጨለማ ከሌለ ብርሃን አይታወቅም። አዳም ክፋትን ባያውቅ ኖሮ ደግነትን መምረጥ አይችልም ነበር። በገነት ውስጥ አዳም ደግ የነበረው ሌላ አማራጭ ስለሌለው ነው። እውነተኛ ግብረ-ገብነት (Ethics) የሚጀምረው ክፋትን ማድረግ እየቻልን ደግነትን ስንመርጥ ነው። ስለዚህ አዳም ወደ ምድር የወረደው "እንስሳዊ ቅንነትን" ትቶ "ሰብዓዊ ምርጫን" ለመለማመድ ነው። ውድቀቱ በእውነቱ ወደ ላይ (Upward fall) የተደረገ ጉዞ ነው።
መምህር ኃይለ መለኮት፦ (መጽሐፋቸውን እየዘጉ) ይህ የአንተ ፍልስፍና አደገኛ ቢሆንም፣ የሰውን ልጅ የመፍጠር ፍላጎትና ነጻነት የሚተነትንበት መንገድ ግን ለየት ያለ ነው። ቢሆንም ግን፣ ያ የናፈቅነው ገነት አሁንም በውስጣችን አለ፤ አዳም ይዞት የወጣው ትልቁ ቅጣት ያንን ናፍቆት ነው።
ዓለምነህ፦ በትክክል መምህር! ያ ናፍቆት ነው እኛን ጸሐፊ፣ ፈላስፋና አማኝ ያደረገን። አዳም ባይወጣ ኖሮ እኛ ዛሬ ይህንን ውይይት አናደርግም ነበር።
መምህሩ ስልካቸው ጠርቶ ውይይቱን ገታ አድርገው ሊያናግሩ ተነስተው መራመድ እንደጀመሩ፣ ዓለምነህ ብዕሩን አንስቶ ይህንን ማስታወሻ መጻፍ ጀመረ፥
የአዳም ከገነት መውጣት በተለምዶ እንደሚነገረው የትዕዛዝ መጣስ ውጤት ሳይሆን፣ የሰው ልጅ "ፍጡርነትን" ጥሎ "ፈጣሪነትን" ለመጎናጸፍ ያደረገው የመጀመሪያው የነጻነት አብዮት ነው። ገነት ፍጹም ናት፤ ፍጹምነት ደግሞ ለለውጥና ለእድገት በር ዝግ ነው። በአንድ ስፍራ ላይ ፍጹምነት ካለ፣ እዚያ ስፍራ ላይ "ታሪክ" የለም። አዳም በገነት ውስጥ በነበረበት ወቅት፣ ህሊናው ገና ያልበቀለ ዘር ነበር። መውደቅ (The Fall) የተባለው ክስተት፣ በእውነቱ የሰው ልጅ ህሊና ከማህፀን የወጣበት "የልደት ምጥ" ነው።
የገነት "ውበት" እንደ እስር ቤት ነበር ለአዳም። ገነት ለሰው ልጅ የተሰጠች "ጎጆ" ሳትሆን፣ የማወቅ ጉጉቱን የምትገታ "ወርቃማ እስር ቤት" ነበረች። አዳም በገነት ውስጥ እያለ የራሱ "እኔነት" (Self-consciousness) አልነበረውም። ሁሉንም ነገር የሚያገኘው በጸጋ እንጂ በጥረቱ ስላልነበረ፣ ማንነቱ ከፈጣሪው ማንነት ጋር ተዋህዶ የቀረ የጥላ ያህል ነበር። ዕፀ በለስን መብላት ማለት ደግሞ ይህንን "ጥላነት" ጥሎ፣ የራስን ጥላ መጣልና የራስን ብርሃን መፈለግ ነው። ይህም "የሁለትዮሽ እውቀት" (Duality) መጀመሪያ ነው። ጥሩና መጥፎን መለየት ማለት፣ ዓለምን በፈጣሪ አይን ብቻ ማየትን አቁሞ፣ በራስ አይን መተርጎም መጀመር ነው። "ውድቀት" ሳይሆን "መቆም" ነው።
አዳም ወደ ምድር የወረደው ወድቆ ሳይሆን፣ በራሱ እግር ለመቆም ቆርጦ ነው። በገነት ውስጥ "ስህተት" መስራት አይቻልም ነበር፤ ስህተት በሌለበት ደግሞ "ጥበብ" አይኖርም። የሰው ልጅ ታላቅነቱ የሚመነጨው ስህተት ሰርቶ ከመታረሙና ካለማወቅ ተነስቶ እውቀትን ከመገንባቱ ነው። ስለዚህ አዳም ከገነት መውጣቱ፣ ከማይለወጥ ደስታ (Static Bliss) ወደሚለወጥና ወደሚገነባ ህይወት (Dynamic Life) የተደረገ ሽግግር ነው። ምድር የአዳም ቅጣት ሳትሆን፣ የእምቅ ኃይሉ መፈተኛ የናፍቆት ፍልስፍና (The Philosophy of Yearning) ላብራቶሪ ነች።
አዳም ከገነት ይዞት የወጣው ትልቁ ስጦታ "ጉድለት" ነው። ገነት ውስጥ ሁሉም ነገር ሙሉ ነበር፤ ሙሉነት ደግሞ ፍላጎትን ይገድላል። አዳም በጎደለው ምድር ላይ ሲቆም ግን፣ ያንን የጎደለውን የመሙላት ጥማት የጥበብ፣ የሳይንስና የፍልስፍና ምንጭ ሆነው። የሰው ልጅ ስልጣኔ በሙሉ "ገነትን በምድር ላይ የመድገም" ሙከራ ነው። ይህ ናፍቆት ባይኖር ኖሮ፣ ሰው ዛሬም ድረስ በደመነፍስ የሚመራ እንስሳ ሆኖ በቀረ ነበር። አዳም "ባይወድቅ" ኖሮ፣ ዛሬ የምናደንቃቸው ታላላቅ የሰው ልጅ ስኬቶች ባልተፈጠሩ ነበር። የመጨረሻው ድል፡ ሞት እንደ ነጻነት አደረገ።
በገነት ውስጥ ሞት አልነበረም፤ ሞት በሌለበት ደግሞ የህይወት ዋጋ አይታወቅም። አዳም ሟች መሆኑን አውቆ ወደ ምድር መውረዱ፣ እያንዳንዱን ቅጽበት ትርጉም እንዲሰጣት አስገድዶታል። ሞት ለሰው ልጅ "ጊዜን" ሰጥቶታል። ጊዜ ደግሞ የታሪክ መስሪያ ጥሬ እቃ ነው። አዳም ከገነት የተባረረው ረጅም እድሜ እንዲኖረው ሳይሆን፣ አጭር እድሜውን በታላቅ ትርጉም እንዲሞላው ነው።
የአዳም ታሪክ የአንድ በደለኛ ታሪክ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና ከፈጣሪ ጥገኝነት ወጥቶ የራሱን ዓለም ለመፍጠር ያደረገው "ታላቅ የነጻነት ጉዞ" ነው። አዳም ወደ ምድር የመጣው ገነትን አጥቶ ሳይሆን፣ ምድርን ገነት ለማድረግ የሚያስችለውን "የመፍጠር አቅም" ይዞ ነው።
ከገነት መውጣት እንደ ስደት ሳይሆን እንደ "ምረቃ" ሊታይ ይችላል። አዳም ከገነት ሲወጣ የተሰጠው "በግንባርህ ላብ ብላ" የሚለው ቃል፣ የሰው ልጅ በገዛ ጥረቱ ዓለምን የመለወጥና የመፍጠር ስልጣን እንደተሰጠው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። እውቀት ያለ ህመም አይገኝም። አዳም የገነትን ሰላም የገበረው ለነጻነትና ለዕውቀት ሲል ነበር። በገነት ውስጥ ጊዜ ቆሞ ነበር፤ መውደቅ ግን ታሪክን ፈጠረ። ሰው የራሱን ታሪክ መጻፍ የጀመረው ገነትን ጥሎ ሲወጣ ነው።
አዳም ከገነት ሲወጣ ይዞት የወጣው ትልቁ ሀብት "ናፍቆትን" ነው። ይህ ናፍቆት ነው ለሰው ልጅ ጥበብን፣ ስነ-ጽሁፍንና ፍልስፍናን የሰጠው። ወደ በፊቱ ፍፁምነት ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት የሰው ልጅን ስልጣኔ እንዲገነባ አድርጎታል። ስለዚህ፣ መባረሩ የአንድ ፍጡር ውድቀት ሳይሆን፣ የፈጣሪን መልክ የያዘው ሰው በራሱ እግር ቆሞ አምላክን እንዲመስል የተሰጠው ታላቅ የፈተና ሜዳ ነው።
ባጭሩ፣ አዳም ከገነት የወጣው በመሸነፍ ሳይሆን፣ "ሰው" ለመሆን የከፈለውን ዋጋ ይዞ ወደ ሰፊው ዓለም የተሰማራ የመጀመሪያው ጀብደኛ መንገደኛ ሆኖ ነው።
ልክ በዚህ ጊዜ መምህሩ ስልካቸውን ወደ ኪሳቸው እየከተቱ፣ የዚህን ሰው ልብ የሚያሸንፉበትን፤ ወደረኞች የማይቋቋሙትን ጥበብና አንደበት እንዲሰጣቸው ፈጣሪያቸውን በልባቸው ተማጽነው ለዳግም ውይይት ወደ ወንበራቸው ተመለሱ።
አሁን ጥያቄዬ፣ ዓለምነህን፤ ነቅዬ ልጣለው ወይስ ተክዬ ላቆየው ??
0 Comments