ለምስኪን ልዕልናው ታይታና ይኹንታው

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት በእብሪት ለታጀረው ምስኪን አባቱ በሰጠው ጸጋ በልጽጎ ጽድቁን ከመፈጸም ይልቅ ለታበየበት ልቡ ታይታና ይኹንታ ቀለቡ ነው!

ምስኪንነት ባዶነትን በጩኸት፣ ድክመትን ደግሞ በአስመሳይነት የመሸፈን ጥበብ ነው። እውነተኛው አባወራ አምላኩ የሰጠውን ጸጋ ተረድቶ፣ ያንን ጸጋ ለቤተሰቡና ለትውልድ ግንባታ (ለጽድቅ) ሲያውለው፤ ምስኪኑ ግን ያንኑ ጸጋ ለታይታ ፍጆታ ያውለዋል።

ለምስኪኑ ሕይወት ማለት ሌሎች ስለ እሱ የሚሰጡት ምስክርነት እንጂ፣ እሱ በራሱ ማንነት ላይ ያለው ጽኑ አቋም፣ የሚገነባውም ጠንካራ ስብዕና አይደለም።

ምስኪኑ “ዘመናዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትኁት፣ ጥሩ፣ መልካም፣ ደግ፣ ቸር፣ ለጋስ፣ ታማኝ...” ተብሎ በሚወደድበት ጠባይ ተቀባይነትን ለማግኘት ሌት ተቀን ይዳክራል። ይህ ድካሙ ግን ከንጽሕና የመነጨ ሳይኾን፣ የሰዎችን “ይኹንታ” እንደ አደንዛዥ ዕፅ ስለሚፈልገው ነው።

ይህ በአባወራው ሥልጠናና ምርመራ መሠረት ልብ አጥፊ እጅግም ስር የሰደደ በሽታ ነው!

ሰዎቹ “ጎበዝ” ካላሉት ይሞታል፤ “መንፈሳዊ” ካላሉት ባዶነቱ ያንገበግበዋል። “ጎበዝ፣ ጠንካራ፣ መንፈሳዊ፣ ትኁት...” መባልን አልፈልግም ቢል እንኳ ውሸቱን ነው፤ እነርሱን ከማጣት ደዌ፣ ችጋርም ይዞት በጠና ይታመማል።

በመኾኑም ሰውነቱን በጠንካራ ስብዕና አንጾ ወደ ተፈጠረለት ልዕልና ለማድረስ የማይችል አልጫ፣ ሰነፍና ሰበበኛ ይኾናል። እውነተኛ ስብዕና መገንባት ዋጋ ያስከፍላል፤ በታይታ ለመኖር ግን ድራማ ብቻ ይበቃዋልና እርሱም ድራማውን ሲሠራ፣ ታይታና ይኹንታ ሲዘራ፣ ልቡ ጠፍቶ ትውልድንም አጥፍቶ ነገር ግን እንደርሱ ያለ በሁለት ወገን የተሳለ “ዘመናዊ መንፈሳዊስ የት ይገኛል” ተብሎ ያልፋል።

ይህ በእብሪት የታጀረ ምስኪን፦ ስሜታዊነቱ የነገሠበት፣ እርሱም ለስሜቱ ባርያ የኾነበት ነው። እውነቱን ከመጋፈጥ ይልቅ በሰበብ መሸሸግን ይመርጣል። ለሰበብ አስባቡም ቁጥር ስፍር የለውም፤ ከሰማይ ከዋክብት ከባሕር ዳር አሸዋም ይበዛል።

ጸጋው የተሰጠው እንዲያገለግልበትና ትውልድ እንዲታደግበት ኾኖ ሳለ፣ እሱ ግን ጸጋውን ጠልቶና ጥሎ ባልተሰጠው ጸጋ ልዕልናን ይሻል።

መንፈሳዊነቱ “እዩኝ፣ ስሙኝ፣ ተቀበሉኝ፣ አድንቁኝ” የሚል የቅብጠት የቀላጭም ነው፤ ዘመናዊነቱም “አድንቁኝ፣ መርቁኝ” እንጂ። እነዚህን “አልፈልግም” ይላል እንጂ ከምግብና ከመጠጥ፣ ከዐየርና ከእውነት ይልቅ የሚፈልጋቸው ኾኗል።

ከሰዎች ዓይን ርቆ በሚሠራው ሥራ ውስጥ ታማኝነት የለውም፤ ምክንያቱም እዚያ ጋር ጭብጨባ የለም፤ በዚያ ታይታና ይኹንታ፣ ውዳሴና ክብርም የለም።

ስለዚህም በድብቅ ከሚያየው አምላክ አንጻር መንፈሳዊነቱም የአስመሳይ፣ ንስሃውም የአድርባይ እንጂ እውነተኛ ተነሳሂ ልቡና የለውም፤ ይህም ምን ቢማር፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንትም ቢኾን እርግጥ ነው! ልብ በጠፋበት ሰውነት ንስሃ የአፍ ላይ ንባብ ነውና!

ወንዴሜዓለም! ታይታና ይኹንታ ቀለብህ ከኾኑ፣ አንተ ከማንም ባርያ ፈንጋይ በፊት የስሜትህ ባሪያ ነህ! በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ጥላ አትጠለል! እውነተኛው ልዕልና የሚገኘው፣ ከአባወራነቱም ማማ የምትደርሰው ሰዎች በማያዩህ ስፍራ በምትፈጽመው ጽድቅና በምትገነባው ጠንካራ ስብዕና ነው።

ምስኪንነትህን አስቀድሞ ሳይጥልህ ቀድመህ አውልቀህ ጣለው፤ ታይታና ይኹንታ በሚገኝበት ማዕድ ላይ መሰየምህን አቁም!

አለበለዚያ ሰው መኾን አትችልም!

ፈጣሪ የሰጠህ ጸጋ ለታይታ ሳይኾን ለጽድቅ መፈጸሚያ ነው። በሰዎች ጭብጨባና ይኹንታ ማረፍ የአሰሶች ዕጣ ነው፤ በእውነት፣ እምነትና እሴትህ ጸንተህ፣ በጸጋህ በልጽገህ ተገኝ እርሱ የአባወራነት ልዕልና ነው!

Post a Comment

0 Comments