✍ ናትናኤል ሰሎሞን | በማለዳ ንቁ | ኢትዮጵያ አውታር
መቼም ኹላችንም እስከዛሬ የመጣነውን ነን፡፡ ታሪካችንን ነን፡፡ የማንነታችን ትንታኔ በታሪካችን ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚለው እኛ የትናንት ነን፡፡
ማሕበረሰብእም ከዚህ የተነሳ እሱም የራሱ ትናንት አለው፤ የራሱ ታሪክ አለው፡፡ ስለዚህ በጥቅሉም ሲኬድ 'ዓለም' የምንለው አጠቃላዩ የጋራ ነገራችንም የራሱ ታሪክ አለው፡፡
የዓለም ታሪክ የየዘመናቱ ትውልድ ታሪክ ነው፤ እየተዋለድን በምንቀጥለው ባሕርይ በኩል የምንጽፈው ኑሮ አለ፡፡ አበው የሰው ልጅ በውጪና በውስጥ የተጻፈበት መጽሐፍ ነው ይላሉ በትርጓሜ፡፡ (ራእ. 5) 'ሰው' ሲሉ መላውን የሰውን ዘር ስለኾነ፣ ዓለምም መጽሐፍ ናት ስለዚህ፡፡ ገጾቿ የየዘመናቷ ትውልዶች ናቸው፡፡ ሕይወት እስከቀጠለም ድረስ ይህ እውነታ ይቀጥላል፡፡
ይህ በመጻፍ ሂደት ላይ ያለው አጠቃላይ ታሪካችን፣ ጉዞዉ በመዋለድ ባሕርያችን ላይ ይመካል፡፡ ወይም በሌላ አቀማመጥ፣ እየተዋለድን ስለቀጠልን ነው አጠቃላይ እንደ ሰው የሚነገረው ታሪካችን ቀጥሎ ያለው፡፡ ማንነታችን በመዋለድ የዘር ሕግ እየተተረተረ በታሪክ መገለጹን እስካሁን ቀጥሎአል፡፡
የመዋለድ ሥርዓታችን በባሕርያችን ውስጥ ካሉት አንዱ ከእፅዋት ባሕርይ የተዘረጋ ነው፡፡ ወንጌልን የሚተረጉም መንፈሳዊ ድርሳን ስለዚህ ነገር ሲናገር 'አዳም (የሰው ልጅ) በሦስት ኃይላት ጸና፤ በኃይለ ዘርዕ፣ በኃይለ እንስሳና በኃይለ ንባብ' ይለዋል፡፡ ኃይለ ዘርዕ የሚለው የአዝርዕትን ግብር ነው፤ የመዘራት፣ የመብቀል፣ የማፍራትና የመድረቅ ባሕርያቸውን፡፡
ይህን የባሕርይ ሥርዓት በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ስናየው የመፀነስ፣ የመወለድ፣ በዕድሜ የመቆየትና የመሞት ዑደታችን ኾኖ እናየዋለን፡፡ ትውልድ በዚህ መስመር ይመጣል፤ በዚሁ መስመር ይኼዳል፡፡ በነገራችን በመንፈሳዊው ታሪክ አዳምና ሔዋን የዛፍ ፍሬ በልተው ወደዚህ ዓለም ወረዱ የሚባለው የዚህ እውነታ ቅኔ ነው፡፡
ባሕርያችን ለዚህ ጥልቅ ሀሳብም ላለው ሥርዓት በመተዳደሩ በመዋለድ ሕግ ወደፊት እንቀጥላለን፡፡ ታሪካችንን እየጻፍን እናልፋለን፡፡ በየዘመናቱ ከእኛ የሚገለጡትም ሥልጣኔዎች ከእኛ የተነሳ በዚህ በዛፉ ባሕርይ ይመላለሳሉ፡፡ ይዘራሉ፤ ይበቅላሉ፤ ይለመልማሉ፤ ያፈራሉ፤ ይጠወልጋሉ፤ ደርቀው ይጠፋሉ፤ እንደገና ደግሞ ብቅ ይላሉ፡፡
በዓለም ታሪክ ታላላቅ የሚባሉ ሥልጣኔዎች በጊዜያቸው መጥተው በጊዜያቸው ኼደዋል፡፡ እርግጥ ኼደዋል ሲባል ሙሉ ለሙሉ አይጠፉም፡፡ ቅሪቶቻቸው በአንድም በሌላም ይቀጥላል፡፡ በዘመናቸው የገለጡት ሀሳብና ሥራ ሳይለወጥም ሆነ ተለውጦ ወደ ቀጣዩ ይሻገራል፡፡ ሽምግልና የልጅነትና የወጣትነት ድምር ዕውቀትም እንደኾነው፣ አኹን ያለንበት ሥልጣኔም ካለፉት የጥንትም የቅርብም ሥልጣኔዎች ተሰብስቦ ተሰርቷል፡፡
እ.ኤ.አ ፅንሰቱ በ1500 ዓ.ም እንደተጠነሰሰ የሚታሰበው የዛሬው ዘመን ግዙፍ ሥልጣኔ፣ በአንድ ዓይነተኛ መልኩ ከቀድምቶቹ ይለያል፡፡ በዓለም አቀፋዊነቱ! ኹሉም የጊዜው የሰው ልጅ ሊባል በሚያስደፍር መልኩ በዚህ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓትና ባሕሉ ተጠምቋል፡፡ በቂ ዝርዝሩ የዚህ ሥልጣኔ አንድ ውጤት ከሆነው ከመገናኛው መረብ በሚገባ የሚገኝ ቢኾንም፣ ለመቀንጨብ ያህል እንዲኾን ግን በዙሪያችን እንዲህ ከቦን የምናየው ዓለም አቀፍ ኑሮ አጀማመርና ሥሪቱ እንዴት ነው? የሚለውን በአጭሩ እንየው፡፡ ይጠቅማል፡፡
1. ፅንስትና ልደት
የታሪክ ምሁራን በጋራ እንደሚስማሙት፣ ደርሰን ያለንበት ዘመናዊው ዓለም ከ3 ዋና ዋና የዘመን አብዮቶች መሠረቱን ያነሳል፡፡ እርግጥ በማእከልነት የሚጠቀሰው ሦስተኛው የታሪክ አንጓ ነው፡፡ እኛም እዚህ የምንዳስሰው ሦስተኛውን የዘመን ገጽታ ነው፡፡ ኾኖም ኹለቱን መሠረቶቹን ግን በመጠኑ ጠቃቅሰናቸው እናልፋለን፡፡ እንጀምር፡፡
1.1 የአክዚያል ዘመን - The axial age (800-200BCE)
ካርል ጃስፐርስ (Karl Jaspers) የሚባል አንድ የጀርመን ፈላስፋና የታሪክ መርማሪ፣ ያለንበት ዘመናዊው ዓለም መሠረት ከዚህ ታላቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ከተነሳበት የታሪክ ሂደት እንደሚመዘዝ ይሞግታል፡፡ ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ ከ800 እስከ 200 ዓ.ዓ ባለው ዘመን የነበረው ይህ ወቅት፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ ታላቅ የሀሳብና የሃይማኖት አብዮት የታየበት ጊዜ ነበረ፡፡ ስማቸው ዛሬ ድረስ በጉልህ የሚነገርላቸው እንደነ ሶቅራጠስ በኋላ አፍላጦን (plato)፣ ቡድሃና ኮንፊሺየስ ከዛ ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላዩ የሰው ልጆች የሥነ ዕውቀትና የሞራል እሳቤዎች ላይ ዓይነተኛ ለውጥ ያመጡ ሥራዎቻቸውን በዘመኑ ሊገልጹ ችለዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ዋና ዋናዎቹ የምሥራቁ ዓለም ሃይማኖቶች ማለትም ቡድሂዝም፣ ሂንዱይዝም፣ ኮንፊውሺያኒዝምና ዞራስትሪያኒዝም ልደታቸውን በዚያ ዘመን አግኝተዋል፡፡ ሌላው በነ ሶቅራጠስ በኩል የዛሬው ዘመን ፍልስፍና የሚባለው የአስተሳሰብ ዘዬም መነሻውን በግሪክ አድርጎ በወቅቱ ተጀምሯል፡፡ በተጨማሪም ክርስትናን ጨምሮ የኋላ ዘመን የአብርሃም ሃይማኖቶች መውጪያ የሚባለው የዕብራዊው ዓለም የነብያት ባሕልም ከጊዜው ዋና መልኮች ውሰጥ አንደኛው ነበር፡፡
የዚህ ዘመን ታላቅ የለውጥ ነጥብ ተብሎ የሚጠቀሰው፣ የሰው ልጆች ከላይ ከተጠቀሱት መነሻ እሳቤዎች በኋላ ከንግርታዊና ትውፊታዊ የአስተሳሰብ ክበቦች (mythical tribal thinking) ወጥቶ፣ ግለሰባዊ ንቃተ ሕሊና ላይ ወዳተኮሩ የሞራልና የምክንያታዊነት የአእምሮ መንገዶች መሸጋገሩ ነበር፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች ነገሩን እንዲህ ሲሉ በአጭሩ ይገልጹታል - Modern human consciousness began here.
1.2 የክርስትና መነሣትና ያስከተለው አብዮት - The christian-Late Antique Transformation (1-6CE)
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተለኮሰው የክርስትና ችቦ የተነሳ፣ ታላቂቱ የሮም ግዛት በ4ተኛው ክ/ዘመን ገደማ ክርስትናን ይፋዊ የመንግሥት ሃይማኖት ማድረጓ የዚህ ዘመን ታላቅ የለውጥ አቅጣጫ ነበረ፡፡ ዛሬ የምናውቀው የምዕራቡ ዓለም የሥነ መንግሥት፣ የአኗኗርና የዕውቀት ባሕል ከዚህ የሽግግር እጥፋት በኋላ ቅርጽና ይዘቱን እያገኘ ሊኼድ ችሏል፡፡ የኛይቱ ሀገር የወቅቱ የአክሱም ዘመነ መንግሥቷ ኢትዮጲያም በ328 ዓ.ም አከባቢ ክርስትናን በዐዋጅ ስለመቀበሏ አንዘነጋም፡፡
1.3 ዘመናዊው ዓለም አቀፍ ሥርዓት - The Modern Global System (1500-1800CE)
ዛሬ የምናውቀውና የምንኖርበት የአስተሳሰብ ሥርዓት መቼ ተወለደ ከተባለ፣ 1500ዓ.ም ተጠቃሹ ዘመን ነው! እነሆ የዛሬው ዘመን ብዙ ነገር፣ ከዛሬ 500 ዓመት በፊት ተጀመረ! የዛሬው ዘመን ዋና የመሠረት ድንጋይ የኾነው ይሄ ጊዜ፣ አራት ታላላቅ የለውጥ ደረጃዎችን አልፎ አኹን ያለበት ጋ ደርሷል፡፡ ተራ በተራ እንያቸው፡፡
1.3.1 የመስፋፋት ዘመን - The Age of Exploration
ከ1500 በፊት፣ የዓለም ትውልዶች በሮቻቸውን ዘግተው እንደሚኖሩ ጎረቤቶች አስቧቸው፡፡ አውሮፓ፣ አፍሪካ፣ የሩቅ ምሥራቁ ዓለምና ሌላውም የዓለም ክፍል በየተነጠለ ስፍራውና ባሕሉ ይኖር ነበር፡፡ ከዚህ ክ/ዘመን ወዲህ ግን የያፌት ልጆች (አውሮፓውያን) የተፈጥሮ ሃብቶችንና ግንኙነቶችን ያስተሳሰሩ ኀሠሣዎቻቸውን በመጀመራቸው፣ ዛሬ ፈፍቶና ከጡዘቱ ወጥቶ የምናውቀው ዓለም አቀፉ ትስስር (Globalization) በዓለም የታሪክ እርሻ ላይ መብቀሉን ጀምሯል፡፡
0 Comments