ደቦሎቹ አንበሳ ጀግንነታቸው፣ ክራንቻ ጥርሳቸው፣ ዘንጣይ ጥፍራቸው፣ ቡጢ መዳፋቸው፣ ደቋሽ ክንዳቸው ተኮንኖ፤ የበግ-መምህሮቻቸው እንከፍ ምስኪንነትን፣ ስልብ ሙክትነትን እያዩ ሲያድጉ አንበሳነታቸውን ጠልተው በግ መኾንን ይናፍቃሉ!
ተኩላው የአንበሳን ደቦሎች ለመግደል አይመጣም፤ ይልቁንም አንበሳነታቸውን እንዲጠሉ ሊያደርጋቸው ይመጣል እንጂ። ዛሬ ትውልዱን ከማንነቱና ከአባቶቹ ትውፊት ለመለየት የሚሠራው ሥራ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም የሚካሄድ ስውር የማምከኛ መርዝ ነው።
ዘመናዊነት ማለት ራስን ማወቅ፣ ጥበብን መጨመር፣ እሴትን ማዳበርናና ግርማን መላበስ ነበረበት፤ ነገር ግን ዛሬ ለልጆቻችን የሚሰጣቸው ዘመናዊነት ራስን መጥላት ኾኗል።
የአባቶቻቸው ጽናት “ኋላ ቀርነት”፣ የወንድን ልጅ ግርማ “አምባገነንነት”፣ የሴት ልጅ ውበትና ልዕልና ደግሞ “ጭቆና” ተብሎ ይተረጎማል።
ደቦሎቹ (ወንዶች) አንበሳ ጀግንነታቸው፣ ክራንቻ ጥርሳቸውና ደቋሽ ክንዳቸው—ይኸውም ቤተሰብንና እውነትን የመከላከል አቅማቸው—በየመገናኛ ብዙኃኑና በምሁራን ይኮነናል።
ከዚያ ይልቅ እንከፍ ምስኪንት፣ ፍዝ ተከታይነት፣ የዋህ ተስማሚነት፣ ስልብ ጃንደርባነት እነፈየተቆለጳጰሰ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም ኾኖ ተብለው ወደ መገናኛ ብዙኃን በሚመጡት “ሊቃውንት” ይጋታሉ።
ይህንን ሲሰሙም በራሳቸው ተፈጥሮ ያፍራሉ። ያኔ ልባቸውን አዝለው፣ ክራንቻቸውን ደብቀው፣ ጥፍራቸውን ሸጉጠው፣ ክንዳቸውን አስልለው፣ “ሥልጡን በግ” ለመኾን ይጣጣራሉ።
እርሱ ዐዲሱ አንበሳነት፣ ወንድነት፣ አባወራነት ነውና!
ይህኛው የመንፈሳዊነት ስለባና እጅግ ረቂቅ ነው። እውነተኛ መንፈሳዊነት ለአምላክ ማደርና ለእውነት መቆም ኾኖ ሳለ፣ በበግ-መምህራኑ ትርክት ግን መንፈሳዊነት ማለት እንከፍ ምስኪንነትና ስልብ ሙክትነት ኾኗል።
በዚያም ድክመትን እንደ ትሕትና፣ ፍርሃትን እንደ መንፈሳዊነት፣ አድርባይነትን ደግሞ እንደ ታዛዥነት እንዲቆጥሩት ይደረጋሉ።
በዚህም ምክንያት ትውልዱ ጽድቅን የሚፈጽምበት ወኔው ተሰልቦ፣ ለማንም ባዕድ አጀንዳ ወዶ ገብ ባርያ ይኾናል። ትውልዱ አንበሳነቱን ጠልቶ በግ መኾንን ሲናፍቅ፣ ተኩላው ሥራው ቀላል ይኾንለታል።
ትውልዱ በሰውነቱ አንበሳ ቢመስልም፣ በልቡ ግን የበግነትን ባርነት ያጸደቀ፣ ሙክት ጃንደርባነቱን የተቀበለ፣ ስልብ ድልብነቱን የወደደ ይኾናል።
የራሱን እሴት፣ የራሱን ባህል፣ የራሱን ሃይማኖት ከምንም በላይ የራሱን ተፈጥሮ ወንድነት መክሊቱን እንደ ሸክም እያየ፣ የባዕዳኑን ፍርፋሪ እንደ ትልቅ ዕውቀት ይለቅማል።
ልጆችህ ክራንቻቸውንና ጥፍራቸውን—ይኸውም ወኔያቸውንና ማንነታቸውን—እንዳይጠሉ አድርገህ አሳድጋቸው። አንበሳ “አንበሳ” መኾኑ በረከት እንጂ እርግማን አለመኾኑን፣ ወንዱ አባወራ መኾኑም ሚና፣ ግዴታ፣ ኃላፊነት እርሱም ለጽድቅ መኾኑን በተግባር አሳያቸው።
ከአልጫ መምህራንና ከስልብ ሊቃውንት ትርክት ልባቸውን ጠብቅ። ካልኾነ ግን፣ ነገ በቤትህ ውስጥ አንበሳ ኾን፣ ለማንም ጌታ የሚሰግድ፣ ባርነቱን የወደደና ያጸደቀ ወዶ ገብ ባርያ ታቅፈህ ትቀራለህ።
ይህ “የመብት” ጥያቄ ሳይኾን ጃንደርብነትን የሚጠየፍ የአባወራው ትውልድ የሕልውና ዘመቻ ነው።
🚨 ምስኪን፣ ስልብ፣ ሙክት፣ ድልብ፣ ልብአልባ፣ አልጫ ምሁርም በኾኑ በጎች የተማሩ ደቦሎች፦ “በግ-አንበሶች” መልካም፣ ልክ፣ ተገቢና ውብ የኾነው አኗኗር የመምህሮቻቸው የዋህነት፣ ደግነት፣ ጅልነት፣ ፈሪነት፣ ፍዝነት ይመስላቸዋልና፤ የእነርሱን አንበሳነት፦ወኔያምነት፣ ኃይለኝነት፣ ደፋርነት፣ ጉልበተኛነት.... ይጠየፉታል።
0 Comments