✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ትዳራችንን ሊያፈርሱ፣ ልጆቻችንን ሊበትኑ ዐይናቸውን አፍጠው፣ ጥርሳቸውን አግጥጠው ለመጡት ጠላትና ምንደኞቹ “ጾታዊ ጥቃት” የትርጉም ገደብ ወሰን የለውም! ቤት እስካፈረሰ ድረስ እንደፈለጉት ይተረጎማል!
ተረድታችሁኝ ከኾነ ደጋግሜ የጻፍኩላችሁ እሴታችንን የሚያበላሽ፣ የሚበርዝና የሚደልዝ፣ የሚሰርዝም ልምምድ ይኸው የጠላት ስልት ነው።
ቃላት ማኅበረሰቡ ሲጠቀምባቸው፣ ሲታነጽባቸው ከመጡበት ዐውድ እየወጡ በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት እየተለጠጡ የመጡበት፣ ከዚህም የተነሳ ልብ አልባ ትውልድ ያፈራንበት ነገር።
ለምሳሌ፦ ጃንደርባ የሚለውን ቃል አጽድቀውልን እንደተሰየምንበት፣ እንደተጠራንበት!
ማስተዋላችሁ ከእናንተ ጋር ያለ አስተውሉ! ማስትሬትና ዶክትሬታችሁ፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንትነታችሁ አላልኩም፤ ማ.ስ.ተ.ዋ.ላ.ች.ሁ እንጂ! እርሱ ከአስተዋዩ ልብ ፍጹም የራቀ ነውና!
ጥንታዊው፣ ባህላዊውና ሃይማኖታዊው የቤተሰብ መዋቅር (አባወራነት) ለዘመኑ “ግራ ዘመም” አሳቢዎች እንደ ትልቅ እንቅፋት ይታያል።
እንደ እነ አንቶኒዮ ግራምሺ ላሉ “ፈላስፋዎች” እና ተከታዮቻቸው ያስቀመጡት “የባህል የበላይነት” መመሪያ፣ አንድን ማህበረሰብ ለመቆጣጠር መጀመሪያ ባህሉንና የቤተሰብ መሠረቱን ማዳከም እንዳለበት ያስተምራል።
ዛሬ በሀገራችን በተጨባጭ በተግባር እየታየ ያለውም ይኸው ነው!
ለምሳሌም ቀደም ሲል “ጥቃት” የሚባለው ነገር ግልጥ የኾነ አካላዊ ጉዳትና አስነዋሪ ድርጊቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። አሁን ግን ይህ ቃል እንደ ላስቲክ እየተለጠጠ፣ እንደ ማስቲካ እየተጎተተ በትዳር ውስጥ የሚኖር ማንኛውንም ተፈጥሯዊ አለመግባባት ሁሉ እንዲያካትት እየተደረገ ነው።
👉 በትዳር ውስጥ የሚፈጠር ጊዜያዊ ቅሬታ ወይም መኮራረፍ እንደ “ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት” ተቆጥሮ የክስ ፋይል እንዲከፈትበት ይገፋፋል።
እውነተኛና አሰቃቂ የኾኑ ጾታዊ ጥቃቶች (እንደ አካላዊ ድብደባና አስገድዶ መድፈር ያሉ) ባሉበት ዓለም፣ ጥቃቅን የኾኑ የጠባይ ግጭቶችን፣ መኮራረፍን ወይም አለመግባባትን “ጥቃት” በሚል ጎራ ውስጥ ማካተት እውነተኛውን ችግር አደብዝዞ ለመለያየት ያመቻቻል።
“ምንም ነገር ሴቷ ደስ ያላላት ሁሉ” ጥቃት ከተባለ፣ በትዳር ውስጥ የሚኖር የሰከነ ውይይትና መተራረም የማይቻል ይኾናል።
🚨 የሚፈለገውም እርሱ ነውና ሴቶቻችን ላይ በግልጥ ከሚፈጸመው በደል ይልቅ ወንዱን በተለይም አባወራውን የሚያስኮንን፣ የሚያስጠላው ተፈልጎ በየመገናኛ ብዙሃኑ፣ በየዩቲዩቡ ላይ ይሸቀልበታል ይራገባልም!
ለምን?
መጀመሪያውኑም እኮ ለሴቶች አልመጣም!
🚨 ትዳርን ለማፍረስ፣ ቤተሰብን ለመበተን፣ ልጆቻችንንም ወላጅ አልባ፣ መረንም ለማድረግ እንጂ! ይህ ዛሬ ለብዛታቸው ስፍር ቁጥር ያጡት ግራምሺያውያን ግራዘመም ግብር የማይከፍሉ ነገር ግን በልጆቻችን ሕይወት የሚነግዱ “ግብረሰናይ” ተቋማት ተልዕኮ ነው።
👉 ባልና ሚስት በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ በሚያሳዩት የባህርይ መለዋወጥ፣ በተለይም ደግሞ ሴቷ ላይ በሚታይ ተለዋዋጭ ስሜት እርሷ ደስ ያላላትን ነገር ሁሉ “ጥቃት” በሚል ስም መፈረጅ፣ ትዳርን በፍርሃት፣ ላልገቡበትም በጥርጣሬ እንዲሞላ ያደርጋል።
🚨 የወንዱን መሪነትና ኃላፊነት እንደ “ጭቆና” በመሳል አባወራው በቤቱ ውስጥ ሥርዓት እንዳያሲዝ፣ በቅጥ እንዳያስተምርና በልበሙሉነት እንዳይመራ እጁን በሕግና በ”ጥቃት” ስም ያስሩታል።
ወንዱ በትዳሩ ውስጥ ያለውን ኃላፊነትና መሪነት እንዳይወጣ በሕግና በ”ጥቃት” ስም አጥር ይበጅለታል። ይህም፦ጥንካሬንና ቆራጥነትን እንደ “ጠበኝነት” እንዲሳሉ ማድረግ።
ባል በቤቱ ውስጥ በነፃነት እንዳይናገር ወይም ሥርዓት እንዳያስተምር “ጥቃት አደረስክ” ተብሎ ሊከሰስ እንደሚችል በማስፈራራት ወንድነቱ እንዲሰለብ ያደርገዋል።
ይህ ሁሉ ጩኸትና የቃላት መለጠጥ ለሴቶች መብት ታስቦ ሳይኾን፣ ጠንካራውን የቤተሰብ ግንብ ግድብም “ጾታዊ ጥቃት” በተባለ “ሚሳኤል” ለማፍረስ የታለመ ነው።
(ግድብ አፍራሾቹ ብዩ ያዘጋጀሁት መድረክን ታስታውሳላችሁ?)
ግራ ዘመም ርዕዮተ-ዓለሞች ቤተሰብን “የጭቆና መገኛ” አድርገው ስለሚመለከቱ፣ በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ሰበቦችን በማጋነን ባልና ሚስትን እንደ ባላንጣ እንዲተያዩ ያደርጋሉ።
መተማመንን ያጠፋሉ፤ በትዳር ውስጥ መቻቻልና ይቅርታን በሕግና በክስ ይተካሉ። ትውልዱ አንድነትና ውሕደትን ፈጽሞበት ትውልድ የሚያፈራበትን ፍቅር በሕግ ትምክህት ከተካ(ሕግ አለልኝ ብሎ ከተመካ) ጥፋቱ ራሱ ማቆም ወደማይችልበት ደረጃ ያደርሰዋል።
በዚያም አባወራነት ይፈርሳል፤ ጠንካራ አባወራ የሌለው ቤተሰብ ደግሞ ለውጭ ተጽዕኖና ለርዕዮተ-ዓለም ጥቃት፣ ለባህል ወረራ ግራምሺ እንዳለውም ነባር እሴቱን ለማጣት በቀላሉ የተጋለጠ ይኾናል።
ስለኾነም ባልና ሚስት እርስ በርስ እንደ ጠላት እንዲተያዩ፣ መተማመን እንዲጠፋና በመጨረሻም ልጆች ያለ አባት ጥበቃ እንዲበተኑ ማድረግ ነው። አባወራው የተሰለበበት፣ ወኔ ያጣበት ቤት ደግሞ ለጠላትና ለምንደኞች የርካሽ ትርፍ ምንጭ ይኾናል።
ትዳራችንንና እሴቶቻችንን የሚጠብቀው የእኛ የጸና አቋም ብቻ ነው። የውጭ ኃይሎች በሚያቀብሉት፣ የራሳችን የተማሩ ማስትሬትና ዶክትሬት የሠሩ፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት የተባሉቱም የሚፈተፍቱትና ልጆቻችንን የሚግቱት “የትርጉም መርዝ” ቤታችንን እንዳይፈርስ፣ በወንዱ ልባችን ጨክነን የአባወራነትን ክብር ጠብቀን፣ የቤተሰባችንን የማኅበረሰባችንንም ደኅንነት ልንከላከል ይገባል!
0 Comments