✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ወንድነትን ብሎም አባወራነትን የመኮነኑ አባዜ ሀገራትን ወደማይወጡት ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እየከተታቸው ቢኾንም ችግሮቻችንን የገቢ ምንጭ የማድረጉ የሆዳደርነት አባዜያችን መድኃኒት ፈላጊ ሳይኾን ተወዳጅ ቁስል አካኪ አድርጎናል።
በዘመናዊው ከእርሱም ብሶ በመንፈሳዊው ዓለም አባትነት ወይም አባወራነት እንደ ቀድሞው የክብርና የኃላፊነት ቦታ ተደርጎ ከመታየት ይልቅ፣ በብዙ ወገኖች ዘንድ እንደ አላስፈላጊ ወይም እንደ ጭቆና ተምሳሌት ተደርጎ የመኮነን አባዜ እየሰፈነና እየሰፋ መጥቷል።
ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይኾን፣ በማህበረሰቡ መዋቅር ላይ ጥልቅ እና አደገኛ የኾኑ ክፍተቶችን(ስንጥቆችን) እየፈጠረ ይገኛል።
አባወራነትን የመኮነኑ አዝማሚያ ሀገራትን ወደማይወጡት ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እየከተታቸው ቢኾንም፣ የሚገርመው ግን ይህንኑ ችግር መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ለገቢ ምንጭነትና ለፖለቲካዊ ትርፍ የመጠቀም “የሆዳደርነት” አባዜ ሠልጥኗል። ለችግሩ መድኃኒት ፈላጊ ከመኾን ይልቅ፣ በተወዳጅ ቁስል አካኪነት መኖር የብዙዎች ምርጫ ኾኗል።
አባት በቤተሰብ መዋቅር ውስጥ የሕግ፣ የሥርዓት እና የጥንካሬ ተምሳሌት በመኾኑ፣ የአባወራነት ሚና ሲኮነንና ሥልጣኑ ሲላላ በቤት ውስጥ የሚኖረው የተፈጥሮ የሥልጣን ተዋረድ ይናጋል።
አንድም ቤተሰቡ፣ ማኅበረሰብና ትውልዱ ቅጥና ሥርዓት ያጣል።
ይህ ደግሞ ልጆች ገደብን እንዳያውቁ፣ ለሥርዓት እንዳይገዙ እና በፈለጉት ስሜት ብቻ እንዲነዱ በማድረግ ሥርዓት የሌለው መረንም የኾነ ትውልድ ያፈራል።
በተለይም ለወንድ ልጆች አባት የወንድነት ትርጉም የሚቀሰምበት ቀዳሚው ምንጭ በመኾኑ፣ አባትነት ሲኮነንና ወንድነት እንደ “መርዛማ” ባህሪ ሲቆጠር ታዳጊዎች ማንነታቸውን የሚገነቡበት ጠንካራ ምሳሌ ያጣሉ፤ ተፈጥሮአቸውን ለጊዜው አባታቸውንና አምላካቸውንም ለዘለቄታው ይጠላሉ።
ይህ ክፍተት ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ እና ባልተገቡ የጎዳና ጎጂ ልምዶች እንዲጠለፉ ከማድረጉም ባለፈ፣ ሴት ልጆችም ከአባታቸው ማግኘት ያለባቸውን ፍቅርና ጥበ፣ እንዲሁም የአባወራ አርአያ አጥተው ያንን ክፍተት ባልተገባ ቦታና በማይኾን ወንድ ለመሙላት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።
አባታዊ መመሪያና ቁጥጥር በሌለባቸው ቤቶች ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ለተለያዩ ሱሶች እንዲሁም ለወንጀል ተግባራት የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ እንደኾነ በርካታ ጥናቶች ጠቁመዋል።
አባወራነትን መኮነን ማለት እነዚህን ልጆች ያለ መሪና ያለ ጠባቂ ለዓለም ተኩላዎች፣ ለሆዳደርም ልሂቃንና ሊቃውንት አሳልፎ መስጠት እንደማለት ይቆጠራል።
በተጨማሪም ቤተሰብ የማህበረሰብ መሠረት በመኾኑ፣ አባወራው የኾነውን ምሰሶ “አያስፈልግም” ብሎ መናድ ቤቱን ማፍረስ፣ መሠረቱንም መነቅነቅ ነው።
ይህም ወደ ፍቺ መብዛት እና በነጠላ የማሳደግ(Single Mom) ሸክም እንዲበራከት በማድረግ በማህበረሰቡ ላይ የኢኮኖሚ፣ በተለይና ይበልጥ ግን የሥነ-ልቦና ጫና ይፈጥራል።
ይኹን እንጂ ይህ ሁሉ ቀውስ እየታየ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ ችግሩን የገቢ ምንጭ የሚያደርጉ “ግብር የማይከፍሉ ሱቆች” ግብረሰናይ ድርጅቶች ተቋማትና ግለሰቦች መብዛታቸው ነገሩን ይበልጥ ያከፋዋል።
ማህበራዊ ቀውሱን እንደ ፕሮጀክት በመቅረጽ የገንዘብ ድጋፍ ማግኛ የሚያደርጉ፣ ችግሩን በማባባስ ለራሳቸው ህልውና መንገድ የሚጠርጉ “ሆዳደሮች” ለማህበረሰቡ መድኃኒት ፈላጊ ሳይኾኑ ቁስሉን እያከኩ የሚያስደስቱት በሽተኛ አድርገውታል።
አባወራነትን መኮነን የወደፊቱን ትውልድ የሚረከቡ ወንዶችን ተስፋ ያስቆርጣል። ኃላፊነትን ከመሸከም ይልቅ መሸሽን እንዲመርጡ በማድረግ እሴትን፣ ባህልን እና ታሪክን ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያሻግር መሪ እንዳይኖር በማድረግ ማህበረሰባዊ መሃንነትን ያስከትላል።
የአባወራነትን ሚና ማክበር ማለት ተፈጥሯዊውን የቤተሰብ ሚዛን መጠበቅ ሲኾን፣ ማህበረሰቡ ወደ ጥንካሬው እንዲመለስ ከተፈለገ የአባትነት ክብርና ኃላፊነት ወደ ነበረበት መመለስ ይኖርበታል።
የአባወራው ንቅናቄም ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ይንቀሳቀሳል!💪
0 Comments