ጥላቻን ይዘሯል ጋብቻን አጥፍተው ፍቺን ጥፋትንም ይከምሯል!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ባፍጢም የተደፉት ልሂቃኑና ሊቃውንቱ በወንድና በሴቷ መካከል የዘሩት ጥላቻ አፍርቶ ፍቺ ሰደድ ኾነ፣ ጋብቻም ጠፍቶ ከሰመ፤ ለትውልዱ መጥፋት፣ ለማኅበረሰቡ መምከን ለሀገሪቷም መፍረስ ተጠያቂ ናቸው!

ዛሬ የምናየው የትዳር መፍረስና የቤተሰብ መበተን በድንገት የመጣ መቅሰፍት አይደለም። ይልቁንም “የመብትና የነፃነት” ካባ የለበሱ፣ ከማርክሳውያንና ከምዕራባውያን አስተሳሰብ የተዘገኑ መርዞች በትውልዱ ልብ ውስጥ የዘሩት መራራ ፍሬ እንጂ።

እነዚህ የጥፋት መልዕክትኞች መጀመሪያ “የአንደኛው ዓለም” የሚባሉትን ሀገራት በፍቺ እሳት አቃጠሉ፤ በቀጣይም ጭራሹኑ የሚጋባ፣ የሚወልድና የሚተካ ትውልድ አጥተው የሞት መንገዳቸውን አመጡ!

ትላንት የምዕራቡና የምሥራቁ ዓለም “መብትና ነፃነት” በሚል ማራኪ ስም፣ ከማርክሳውያን የጥላቻ ክምር የዘገኑትን ዘር በትውልዳቸው መካከል ዘሩ።

ውጤቱም ታወቀ፦ በመጀመሪያ ፍቺ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ትዳርን በላው፣ ቤትን አፈረሰ፣ ልጆችን ያለ አባት አደረሰ፤ ቆይቶ ግን ጭርሱን የሚያገባ፣ የሚጋባና የሚወልድ ትውልድ ጠፋ፤ በዚያም ትውልድ እየጠፋ፣ ማኅበረሰብ እየመከነ ሲሄድ በጆሮአችን ሰማን።

ምዕራባውያንና ምስራቃውያን የአንደኛ ዓለም ሀገራት የራሳቸውን ማኅበራዊ መዋቅር ያፈረሱበትን የጥላቻ ፖለቲካ በ”እኩልነት” ስም ወደ እኛ አጋብተዋል።

የሚገርመው ግን ይህንን የጥፋት መንገድ ቀድመው ተገንዝበው መከላከል ሲገባቸው፣ ከቤተ-መንግሥት እስከ ቤተ-ክህነት ያሉት “ልሂቃንና ሊቃውንት” ግን ማሳለጣቸው ነው።

ስለኾነም እኛም ያንኑ የጥፋት ጎዳና እናውቃለን ብለን በታጀርንበት እብሪታችን የጥፋት መንገዱን ቀዳጅና መሪ የኾኑትን “ባፍጢም የተደፉ” ልሂቃንና ሊቃውን እየተከተልን ተያይዘነዋል።

እነዚህ አካላት በትውልዱ ልብ ውስጥ በወንድና በሴት በተለይም በአባወራውና በቤት እመቤቷ መካከል ያለውን የሚና ልዩነት ያለውን በጥርጣሬና በጠላትነት ተክተው አስተምረውታል እያስተማሩትም ይገኛሉ።

በወንድና በሴት መካከል መተማመንን ሳይኾን ጥርጣሬን፣ መተሳሰብን ሳይኾን ፉክክርን፣ ፍቅርን ሳይኾን ጥላቻን እየዘሩ ቤተሰብን የጦር አውድማ አድርገውታል።

የእነርሱ “ሥልጣኔ” መጨረሻው የቀደሙትን በጥፋት መምሰልና ሀገርን ያለ መሠረት ማስቀረት፣ ትውልድ አልባ መኾን፣ ማኅበረሰባዊ ምክነትና የሀገር መፍረስ ነው።

አንድ ሀገር የሚቆመው በጠንካራ የቤተሰብ መዋቅር ላይ ነው። ትዳር ሲጠፋ ትውልድ ይመክናል፤ ትውልድ ሲመክን ደግሞ ሀገር ትፈርሳለች።

ዛሬ ጋብቻ የከሰመውና ፍቺ እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለው፣ እነዚህ ልሂቃን የአባቶቻችንን ወርቅ የኾኑ እሴቶች ጥለው የባዕዳንን ጠጠር-ፍርፋሪ በመልቀማቸው ነው።

ለዚህ ታሪካዊ ዝቅጠትና ለማኅበረሰባዊ ውድቀት ተጠያቂዎቹ የትውልዱን ልብ በባዕድ ትርክት ሰልበው ልብአልባ ያደረጉት ሊቃውንት ናቸው።

ነገር ግን በዚህ ጨለማ ውስጥ ተስፋ አለ! እውነትን፣ እምነትንና እሴትን ዳግም በትውልዱ ልብ ውስጥ እየዘራ ያለው የአባወራው ንቅናቄ ይህንን የጥፋት ማዕበል ለመቀልበስ ተነሥቷል።

እኛ ባዕዳን ለጠፉበት፣ ማኅበረሰባቸው ለመከነበት ትረካ አንበረከክም፤ ለሆዳደር ልሂቃን ትርክትም አንገዛም። የአባቶቻችንን የአባወራነት ግርማና የእናቶቻችንን የቤት እመቤትነትን ክብር ዳግም እናድሳለን።

በጥላቻ ምትክ ፍቅርን፣ በፍቺ ምትክ ጽኑ ጋብቻን፣ በመከነው ምትክ ብርቱ ትውልድን እንገነባለን። በልበ-ሙሉነትና በእውነት ክንድ የፈረሰውን እንጠግናለን፤ የጠፋውን እንመልሳለን።

የአባወራው ንቅናቄ!

ይህ ንቅናቄ በቁጭት የታጠቀ፣ በተስፋ የደመቀና በልበ ሙሉነት የሚራመድ የልባሞች የለውጥ ሞገድ ነው። ልሂቃኑም ኾኑ ሊቃውንቱ በዘሩት የጥላቻ አረም ፋንታ፣ እኛ እውነትን፣ እምነትንና እሴቶቻችንን በወጣቱ ልብ ውስጥ ዳግም እንዘራለን።

💪 ቤተሰብ የሀገር መሠረት መሆኑን እናጸናለን!

💪 የአባወራነትን ክብርና ኃላፊነት ወደ ቦታው እንመልሳለን!

💪 በትውልድ መካከል የገባውን የባዕድ አስተሳሰብ ሰብረን፣ የትዳርንና የቤተሰብን ቅድስና ዳግም እንገነባለን።

ልባም አባወራዎች ሲነሱ፣ እነዚያ “ባፍጢም የተደፉ” ልሂቃን የገነቡት የሐሰት ግንብ ይናዳል። እኛ የታሪክ ተመልካች ብቻ ሳንኾን፣ የጠፋውን ማንነት መልሰን የምንገነባ፣ ቤታችንን ከፍቺ ሰደድ የምናድንና ትውልዱን ለልማት እንጂ ለጥፋት የማናስረክብ ባለቤቶች ነን።

የጥፋት አርክቴክቶች ፍቺን ቢከምሩትም፣ እኛ በእውነት በእምነትም መዶሻ እንንድዋለን። ነገ የፍቺ ሰደድ የሚጠፋበት፣ ጋብቻ የሚከበርበትና ብርቱ ትውልድ የሚታነጽበት ቀን ሩቅ አይኾንም።

መድረሻ መጨረሻችን የቀደሙትን፣ የጠፉ የመከኑትን ሀገራት መምሰል ሳይኾን፣ በአባቶቻችን ጽኑዕ እሴት ላይ ተመስርተን ኢትዮጵያዊውን አባወራነትና እውነተኛውን የቤተሰብ ክብር ዳግም መመለስ ነው!

Post a Comment

0 Comments