ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ሴቶቻችንን ሊያመክን ትውልዳችንን ሊያጠፋ የመጣው ጠላትና ግብርአበር ምንደኛ ሊቃውንቱ፤ ሴቷን ከፈጣሪዋ፣ ከተፈጥሮዋ፣ ከአባቷ፣ ከባሏና ከእሴቷ የሚለያትን መርዝ “መብትና እኩልነት” ብሎ ይመክራል!

አንድ ሰው ወይም አካል ግልጽ የኾነ፣ የታወቀ፣ የተገለጠ፣ የተረጋገጠን በደል ለመፈጸም ሲነሳ፣ ድርጊቱ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ መጀመሪያ “ምክንያት” ይፈጥራል።

አሞራ የማይበላ (ርክስ) ወፍ ኾኖ ሳለ፣ ለመብላት የፈለገው አካል ግን “ጅግራ ናት” በማለት ራሱን ያሳምናል፤ ሌላውንም ለማሳመን ይሞክራል።

እንዲህ የሚያደርጉት ግለሰቦችም ኾኑ አካላት ሲናገሩ ተሰሚነት ያላቸው፤ አንድም ተሰሚነትም ተቀባይነትም ይኖራቸው ዘንድ ዝና-ማዕረጋቸው ስማቸውን የቀደመላቸው ናቸው።

ስለኾነም አንድ ማስትሬትና ዶክትሬት የጫነ፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ተብሎ መድረክ በተሰየመበት፣ ድምጽ ማጉያ በተሰቀለበት፣ ካሜራ በተደቀነበት፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ የሚገኘው ለሰሚ ተቀባዮቹ አሞራን “ጀግራ ናት” አስብሎ ከማሳመን አልፎ በእልልታና በጭብጨባ ያጸድቀዋል።

ዛሬ ትውልዱን ሊያጠፋ፣ ማኅበረሰብን ሊያመክን፣ ቤተሰብን ሊያፈርስና ሀገርን ሊያሳጣ የመጣው ጠላትና የእርሱ ምንደኛ የኾኑት “ምሁራን” ይህንኑ እያደረጉ ነው።

🌟 ሊበሏት ያሰቧትን ሴት፣ ተውሳክ፣ ነቀርሳም በኾነ ማርክሳውያን ሸፍጥ ሊያጠፏት ያሰቧትን ሴት፦ እናቴን፣ ሚስቴን፣ እህቴን፣ ልጄን “መብትሽን እናስከብር” ይሏታል።

🌟 ሊያጠፉት ያሰቡትን ወንድ ደግሞ “ሰላማዊ፣ ዘመናዊ፣ ቻይ፣ ታጋሽ ኹን” ይሉታል።

ያቺ ምስኪን ኢትዮጵያዊት እናት፣ በችጋር ተቆራምዳ፣ በፀሐይ ነዳ፣ በሙቀት ተገርፋ፣ በእሳት ተቃጥላ ሀገርና ቤተክርስቲያን ያቀበሏትን እሴት ተሸክማ ልጇን ለወግ ማዕረግ አበቃች።

ልጇ ማስተሬትና ዶክትሬት ጭኖ፣ “ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት” ተብሎ በአደባባይ ሲቆም፣ ለእናት ሀገሩና ለቤተሰቡ ጋሻ፣ መከታ ይኾናል ተብሎ ሲጠበቅ—እርሱ ግን የእናት ጡት ነካሽ፦ባንዳ ኾነ!

ባዕዳን በሚከፍሉት “የምንደኝነት” ደሞዝ፣ የገዛ እናቱን እሴት የሚሰድብ፣ የአባቱን ሥርዓት የሚንቅ፣ ትውልዱን ለሞት አጣድፎ መቃብሩን በ”መብት” ስም የሚቆፍር ኾነ።

ሴቶቻችንን ሊያመክን የመጣው ጠላት መርዙን የጠቀለለው “በጾታ እኩልነት፣ በመብትና በነፃነት” ካባ ውስጥ ነው።

ሴቷን ከፈጣሪዋ እንድትጣላ፣ ከተፈጥሮዋ እንድትሸሽ፣ ለአባቷ እንዳትታዘዝ፣ ለባሏ እንዳትገዛና እሴቷን እንድትጸየፍ፣ ሴትነት ተፈጥሮዋንም እንድትጠላው ይገፋፏታል።

“ጸረ-ጾታዊ ጥቃት” በሚል ሰበብም በወንዱና በሴቷ መካከል የጥላቻ ግድግዳ ይገነባሉ። በዚያም መፈቃቀድ የለም፣ ቤተሰብ መመስረት፣ ማኅበረሰብ መገንባት ትውልድንም ማነጽ የለም፤ እንዲያው የትም፣ ከማንም መንጠላጠልና መዳራት ብቻ! ቢረገዝስ በመርዝ በጣጥሶ በመቀስ ቆራርጦ ማስወጣት ሲቻል!

ጠላትና ባፍጢም የተደፉት “የእኛ ምሁራን” በዚህ ትርክት ሴቷን “ነፃ አወጣናት” ይሉናል፤ በተግባር ግን ከማንነቷ አውጥተው፣ ቤተሰብ አልባ አድርገው፣ ለብቸኝነትና ለባዕድ ርዕዮተ-ዓለም ባርነት ዳረጓት እንጂ። ጅግራ የተባለችው “መብት”፣ ትውልዱን የምትበላ “አሞራ”፣ አንድም ጤና ነስታ የምታጠፋው የማትበላ ነበረች።

በሌላ በኩል፣ ወንዱን ለጥፋት የሚያዘጋጁበት መንገድ እጅግ ረቂቅ ነው።

ወንዱን፦

ቆራጥነት የሌለው፣ ለጽድቅ የማይጨክን፣ ክፋትን የማይቃወም፦ እንከፍና ንክርርርርር ያለ ምስኪን አድርገውታል።

በተጨማሪም ወንድነት መክሊቱ ጽድቅ ይሠራበት ዘንድ የተሰጠው እንደኾነ እንዲጠራጠር፣ ወኔው እንዲሰለብና አቅመ-ቢስ ጎስቋላ፣ ስልብና ጃንደርባ እንዲኾን በ”ዘመናዊነት” በተለይና በይበልጥ ግን “በመንፈሳዊነት” ስም ይግቱታል።

ከሁሉ እየከፋብን የመጣው ደግሞ እውነትን ይዞ፣ አውቆ ሳለ ለጥቅሙ የሚለዋወጥ፣ ለጠላት አጀንዳ የሚያጎበድድ “መንፈሳዊ” አስመሳይ፣ አድርባይ እንዲኾን ይህም ብልሃትና ጊዜውን መዋጀት እንደኾነ ለሚነገረው ለሚመስለውም ወንድ ለቁጥሩ ኁልቁ መሳፍርት የለውም።

ይህ “መንፈሳዊነት” የተባለው አልጫነት፣ ወንዱን የቤተሰቡ ጠባቂና የሚስቱ አለኝታ፣ የልጆቹ መከታ ከመኾን አውጥቶ፣ ለባርነት የሚመች “ሙክት፣ ድልብ” አድርጎታል።

ጠላት በራሱ እጅ አያጠፋንም፤ አስቀድሞ የትውልዱን ልብ ወኔ በማጥፋትና አልጫ በማድረግ ራሳችንን በራሳችን እንድናጠፋ ያመቻቸናል ኤንጂ።

ይህን ለማድረግ ደግሞ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ፣ ያላቸውን ከሚነግሩን እውነት ይልቅ እነርሱን የምናምናቸውን፣ ያስበለጥናቸውን ሊቃውንት ይጠቀማል።

እነርሱ ከእውነቱ፣ ከእምነቱ፣ ከእሴቱ ትውልዱን ነጥለው፦በጾታ እኩልነት ስም ሴቷን ከእናትነት ወደ ቆሞ ቀርነት፤ በመንፈሳዊነት ስም ወንዱን ከአባወራነት ወደ ጃንደርብነት ሲያጠፏቸው ማኅበረሰቡንም ሲያመክኑት ሀገርንና ቤተክርስቲያንን የሚረከባት ልብ-አልባ ትውልድ ይፈጠራል። ያን ጊዜ ለጠላት ሰርግና ምላሹ ይኾናል!!

ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ቢሏትም፣ አሞራነቷ አይቀርም። መብትና ነፃነት የተባለው መርዝም ምን ስሙ ቢያምር ውጤቱ ትውልድን ማጥፋት መኾኑን ልብ ልንል ይገባል!

“ልብ አለኝ” የሚለው ያስተውል!

አልጨረስኩም!

Post a Comment

0 Comments