የእኩልነት፣ መብትና ነፃነቱ መንገድ በብቸኝነት ይጠናቀቅ!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ተፈጥሮአዊ ጸጋን፣ በእርሱም የምንወጣው ሚናን እንደ ጨቋኝና በዳይ አባወራዊ ሥርዓት አይተው ለጠሉት፤ መጥፋት መምከኑንና በብቸኝነት መማቀቁን ይቀበሏል!

በዘመናዊው ዓለም “መብትና ነፃነት” የሚባሉት ቃላት ትርጉማቸው ተለውጦ፣ ተፈጥሮአዊውን ሥርዓት መቃወሚያ መሣሪያ ኾነዋል።

አባወራነትን እንደ “ጨቋኝ ሥርዓት”፣ እናትነትን ደግሞ እንደ “የነፃነት ጠላት” አድርገው ለፈረጁት ወገኖች የሚጠብቃቸው ሽልማት ብቸኝነትና የዘር መጥፋት ብቻ ነው።

ተኩላው (ዓለም አቀፉ ርዕዮተ-ዓለም) በኢኮኖሚና በውሸት ሥልጣኔ ስም ትውልዱን ሲያምክነው፣ “ነፃነት አገኘሁ” ብሎ ለሚዘፍነው መጨረሻው በገዛ ቤቱ ውስጥ እንደ ብቻውን ተቆራምዶ መጥፋት ነው።

ይሄ በሩቅ የምዕራባውያን አሁናዊ ክስተት ቢኾንም በሀገራችንም በተለይም በመዲናችን ዐዲስ አበባችን እየተዘወተረ የመጣ የቁም ሞት ነው። ኮንደሚኒየሞች ጥቂት የማይባሉ ተቀባይ፣ ጧሪ ደጋፊ ያጡ አረጋውያን “ማጎሪያ” እየኾነ ነው። አስተውላችኋል?

ከዚህ በፊት በላኩላችሁ ጦማር ጃፓናዊ አረጋውያን ብቻቸውን ተቆራምደው፣ ያለ ታዛቢ ቀርተው፣ አልጋቸው ላይ በስብሰው ከቀናትና ከወራት በኋላ የሚገኙ፤ አንዳንዶችም ይህንን የቁም ሞት ከሚያዩ ተንፏቀው ወጥተው ከመኖሪያ ሕንጻቸው ላይ የሚወረወሩና ራሳቸውን የሚያጠፉ መኾናቸውን ዓይተናል።

በዚያ ጸጥታ በሰፈነበት ቤት ውስጥ ኾነህ ወደ ኋላ ስትመለከት፣ ያሳደድከው “ነፃነት” ለብቸኝነት አሳልፎ እንደሰጠህ ትረዳለህ።

በጉልበትህ ጊዜ የናቅኸው ተፈጥሮአዊ ጸጋና አባወራዊ ሚና፣ የእናትነት ጸጋ በስተርጅናህ ጊዜ የሚጦርህና የሚተካህ ትውልድ እንዳይኖር አድርጎሃል።

የራስህን የዘር ሐረግ “በመብትና ነፃነት” ስም እንድታጠፋ የተደረገው፣ ነገ አንተ ስትደክም የሚንከባከብህ፣ ሥርዓቱን የሚያስቀጥልና የአንተን ማንነት የሚወርስ ሕይወት እንዳይኖር ነው።

ማርክሳዊውና “የጾታ እኩልነት” ትርክቱ፣ አባወራውንና ተፈጥሮአዊውን የቤተሰብ መዋቅር እንደ ጠላት ፈርጆታል። ይህ መዋቅር ሲፈርስ ግን ትውልድ ጠፍቶ ማኅበረሰብ መክኖ ይቀራል።

ዛሬ ልጆቻችን ላለመውለድ የሚቀርቡት የ”ኢኮኖሚ” ሰበቦችና የ”ነፃነት” ጥያቄዎች፣ መጨረሻቸው በገዛ ፈቃዳቸው መጥፋት ነው።

በእርግጥ በአሁኑ ጊዜና ዘመን የኢኮኖሚው ቀንበር ያልከበደበት የዓለም ጥግ አለ ለማለት ይከብዳል። ይኹን እንጂ ትውልዱ አስቀድሞ ካልሠለጠነበትና ከተጣባውም የሸማችነት (consumerism) አባዜ ፍላጎቱና አምሮቱም እያደገ ከገንዘብ ማግኘቱ ከሀብት ማጋበሱ እኩል እያደገ ኖሮትም በስስት እና በችጋር ከሚያየው ኑሮው የተነሳ የመውለዴ ወኔው ይሰለባል።

ከኑሮ ውድነት የተነሳ በቁጠባ መኖር በልክ መኖርን አያስተምርም። ይልቁንስ በተሰጠን ጸጋ ላይ ሠልጥኖ ጽድቁን ለመፈጸም የሚደረግ ልምምድ ብቻ እንጂ። ከኑሮ ውድነት የተነሳ ቆጥቦ፣ ሰስቶ፣ ተሳቆ የሚኖረው የማይጠረቃ ፍላጎቱን ማስፈጸሚያ እንዳያጣ እንጂ ሠልጥኖባቸው አይደለም።

እርሱም ዘወትር “ኑሮ ተወደደብኝ፣ አይበቃኝም፣ ያንሰኛል...” እያለ ቢያዝን ቢያላዝን እንጂ “ይበቃልኛል፣ ተመስገን...” ማለት የተሳነው፣ ቢልም ከልቡ ሳይኾን ለአፉ ልማድ፣ ለወሬ ድምቀት፣ በተለይም አጥብቆ ለሚሻት ታይታ ይኾናል።

አስቀድሞ ስለ መውለድ ቢያስብ ኖሮ ከእጅ ወደ አፍ ከኾነ ኑሮው ላይ የማይጠረቃ አምሮት ፍላጎቱን ቆልሎ ራሱን እስኪሰልብ፣ ያለዘርም እስኪቀር ድረስ ባላከበደው ነበር። አሁን ግን እንኳን መውለድ ማሳደግ ቀርቶ በቅጡ መተንፈስ እስኪያቅተው ድረስ ራሱን አስጨንቋል።

የትም ሂዱ፣ ማንንም ጠይቁ “ውይ ወይ እጅግ ከባድ ነው፣ በጣም ከባድ ነው፣ በዚህ ኑሮ አይቻልም” የሚላችሁ ሰው እኖርበታለሁ ያለው የኑሮ መደብ(ደረጃ) በራሱ ሰቅሎ፣ እርሱም አንቆ ያስቀመጠው እንደኾነ ምልክት አታጡም።

ዕድሜው እየገፋ ለሚሄደው አረጋዊ ጧሪ ቀባሪ “መቄዶንያ” መኾን የለበትም፤ ሁሉንምም አይችልም። አንድም እናት አባቶቹን ከመጦሪያ ማጎሪያ የሚጥል ትውልድ እርሱ በራሱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ተስፋ የሚቆርጥ ይኾናል።

አያ።ፈት ቅድማያቶች በሌሉበት፣ እነርሱ ለጧሪ ቀባሪ ተቋም የተጣሉበት ማኅበረሰብ ሳይኾን በትንሽ ኑሮ በጥቂትም ጥሪት ተሰባስበው የሚገኙት ማኅበረሰብ ብቻ ነው የመውለድና የመገንባት ተስፋ የሚያጭረው።

የቤተሰብ እምነትና እሴት ከወላጆች ወደ ልጆች እንዲተላለፍ ልጆም በዚያ ልባም ኾነው እንዲያድጉ እንጂ እነዚያን በማጣት በልባልባነት እንዳይጠፉ፤ ይህንን ነባር ሥርዓት የምናስቀጥልበትን መንገድ መፈለግ ጥቅሙ ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብና ለሀገርም ነው።

ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም እንደሚባለው፤ ዛሬ ከልብ ብናስብበት መውጪያውን አናጣም። አለበለዚያ እንደምዕራባውያኑ ሰርገኛው ደርሶባቸው በርበሬ ቅንጠሳ እንደገቡቱ በጥፋታችን ዋዜማ ላይ ኾነው መደናበር ይኾናል።

Post a Comment

0 Comments