ስለ ሥላሴ በተዋሕዶ የተነቀሱ ጥቂት ሐሳቦች


በአማን ነጸረ

ጸሐፊው (መሠረት ስብሐት ለአብ) በቤተ ክርስቲያን አድግው በቅጡ ተምረው በኋላ ቤተ ሃይማኖት የቀየሩ ናቸው፡፡ ከሌሎች ልውጦች የሚለዩት ምርመራውን ለሙሉ ጊዜ የነቀፋና የማነወሪያ፣ የኋላ ታሪክን ጨለማ በማስመሰል ለአዲስ ጌታ መገበሪያ ለማዋል መፋጠን ላይ ረገብ ይላሉ፡፡ እንጂ በቤተ ፕሮቴስታንት (መካነ ኢየሱስ) ኖረው ነው ያለፉ፡፡

ሥላሴ በተዋሕዶ የተሰኘው መጽሐፋቸው በግሌ ያበሳጨኛል፣ ያሳዝነኛልም፡፡ በብዙ መልኩ መውጣት ካለበት ቤት አይደለም የወጣው፡፡ ለነሩበት ቤት ተደራሲ መጻፉንም እጠራጠራለሁ፡፡ በመጽሐፉ መቅድም ለኢኦተቤክ ፍቅርና አክብሮት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡ ግን ፍቅራቸው ባለችበትና በፀናችበት ሳይሆን እሳቸው ‹‹መሆን አለባት›› በሚሉት መንገድ ነውና የመስመር ልዩነት ይኖረናል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያሏቸውን የሚያዋቅሱ ነጥቦች ከዲ/ያረጋል መድሎተ ጽድቅ ቅጽ አንድ ማየት ይቻላል፡፡ አያይዘን ጥቂት ጥንቃቄና አዛማጅ ንባብ የሚጠይቁ ሐሳቦችን ከመጽሐፉ - ከሥላሴ በተዋሕዶ - እንጠቁም፡፡

ጥቂት የሚነቀሱም፣ የሚያዋቅሱም ሐሳቦች ከሥላሴ በተዋሕዶ፡-

1. መሠረት ስብሐት ለአብ ኃጢኣት የባሕርይ ናት ትወረሳለች የሚለውን አስተምህሮ ሲቀበሉት ይታያል (ገጽ 16፣42፣ 65)፡፡ በኢኦተቤክ ይህ እይታ አይደገፍም፡፡

2. በሰው ተፈጥሮ ዙሪያ ትሥልስታዊ የሚባለውን የሥጋ፣ ነፍስ፣ መንፈስ አተራረክ ይከተላሉ (ገጽ 4፣ 173)፡፡ ይህ እይታ በእኛ ጸሐፍትም ዘንድ አለ፤ አቡነ መልከ ጼዴቅና ቀሲስ መዝገቡ (በበትረ ሃይማኖት) ሐሳቡን ይጠቀሙታል፤ በግብፆችም ዘንድ ተመሳሳይ እይታ አለ፡፡ አንዳንድ ምንባባት በመጽ/ቅዱስም፣ በቅዳሴውም አሉ፡፡ እንደ ብዙኃን ሊቃውንትና ትርጓሜዎች ግን የኢኦተቤክ ሰውን በነፍስና ሥጋ መግለጥ ላይ ታተኩራለች፣ መንፍስ ሲተረጐም ብዙ ጊዜ ልቡና እየተባለ ነው፡፡ በወልታ ጽድቅም በተኀሥሦም በዚህ ዙሪያ የተጠቃቀሱ ሐሳቦች አሉ፡፡ 

3.በምሥጢረ ቊርባን ላይ ያላቸው እይታ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፣ መታሰቢያ ብቻ ከሚሉት ወገን ነው (ገጽ 49)፡፡ ይሄ በኢኦተቤክ ውጉዝ ሐሳብ ነው፡፡ በአቡነ ጴጥሮስ ግብፃዊ በወጣ ጦማር ይህን የሚያስተምሩ ፕሮቴስታንት ሚሶዮናውያን ተወግዘዋል፡፡ መዋዕያን ላይ ግዝቱን ከማብራሪያ ጋር የጠቋቆምን ይመስለናል፡፡

4. ከብቻዎች ውስጥ ‹‹ክርስቶስ ብቻ፣ ጸጋ ብቻ›› አልፎ አልፎ ብቅ ትላለች (ገጽ 47)፡፡ በዚህ ዙሪያ የዲ/ያረጋልን ሦስቱን የመድሎተ ጽድቅ ቅጾች እንደ መድኃኒት መዋጥ ያሽራል፡፡

5. የምትክ ቅጣት ቲዎሪን ብልጭ ያደርጓታል (ገጽ 7)፡፡ እንደ ላይኛው ነው - ያረጋል ይፈውሳል፡፡

6. ከካቶሊካውያን ተነሥታ በአለቃ ኪዳነ ወልድ በኩል የመጣችውን የኃጢአት ምንጭ ሥጋ፣ ዓለምና ሰይጣን ናቸው ብሂል በቁም ያጸድቋታል (ገጽ 43፣ 47)፡፡ በኢኦተቤክ ሥጋና ዓለም እንደ ኃጢአት ምንጭ አይታዩም፤ ሥጋ ክቡር ነው፣ አስተሳሰቡ (ግ)ኖስቲካዊነትም አያጣም፣ እንዲህ ያለው ሥጋን ከኃጢአት የሚያስተሳስር አስተምህሮ ውጉዝ ነው፡፡ በጽንዐ ተዋሕዶ የኢኦተቤክ የኃጢአት ምንጭ የሚሏቸውን ብልጭ ያደረግን ይመስለናል፡፡ ፈቃደ ሥጋ እንጂ ሥጋ በራሱ የኃጢአት ምንጭ አይደለም፡፤

7. ፈቃድና ሥምረት መካከል በቀጭን ልዩነት ብትኖርም እንደ ብዙኃን ጸሐፍት ይቀላቅሏታል (ገጽ 132)፡፡ ፈቃድ አንድን ነገር የመድረግ ዝንባሌ፣ ሥምረት የወደዱትን ማድረግ የምትል ማብራሪያ በጽንዐ ተዋሕዶ ስለ ፈቃድ በተብራራባቸው ክፍሎች ተቀምጧል፡፡

8. በምሥጢረ ሥላሴና በነገረ ክርስቶስ የሚነገረውን ‹‹ግብር›› በደፈናው ቀላቅለው የገለጡ መስሎ የተሰማን ጊዜም አለ (ገጽ 141)፡፡ በነገረ ድኅነት የሚነገሩትን የግብር ተኮር ነገረ ክርስቶስ (Functional Christology) ምንባባት በምሥጢረ ሥላሴ ከሚነገረው ውጫዊ ግብር (Economic Trinity) ጋር ጀምለው ያልፉታል፡፡

9. የአለቃ ኪዳነ ወልድን ክልኤ ባሕርይ አስተምህሮ ልብ ሳይሉ አለቃ ለነገረ ክርስቶስ አስተምህሮ የቀመሩትን የነገረ ክርስቶስ የባሕርይና የአካል ትንተና እንደ ቀላል ጠቅሰውና አጽቀውት ያልፋሉ (ገጽ 239):: አለቃ ኪወክ በአካልና በባሕርይ መካከል ማዕከላዊ ስም (Physis) መኖር ነበረበት፣ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አልፈውታል ይላሉ፡፡ ዋናው የአለቃ ሐሳብ ለባሕርይና ለግብር ምንታዊ ማመቻቸትን ያለመች ናት፡፡ ተኀሥሦ ላይ በመጨረሻው ምዕራፍ አለቃ ላይ ያለንን ተዐቅቦ አኑረናል፡፡ የኬልቄዶናውያኑ የ Maximus The Confessor, John of Damascusና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጸሐፍትን ሥራዎች (የከረኑ የ19ኛ ክዘ መጽሐፈ ምክር፣ የአባ አየለ፣ ተስፋዝጊ ዑቊቢት፣ በቅርቡም ገብረ ወልድ ገብረ ጻድቅ የጻፉትን የነገረ ክርስቶስ) ያየ ሰው የአለቃ ኪወክ ነገረ ክርስቶስ ትንተና ምን ያህል ኬልቄዶናዊ ተፅዕኖ እንዳለበት ይረዳል፡፡

10. መዝገበ ሃይማኖትን አንድ ጊዜ የያዕቆብ ዘእልበረዲ ድርሰት፣ ሌላ ጊዜ  በዐፄ ዘድንግል ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ድርሰት ያደርጉታል (ገጽ 130 እና 400)፡፡ መዝገበ ሃይማኖት ሀገራዊ ድርሰት ሆኖ ይታየኛል፡፡

11. የአርትዖት በአንድ ቃል ይገለጥ! ይዘገንናል! ዳግም ያሳተሙት ሰዎች ጸሐፊውን በድለዋል! የግእዝ ቃላት ጽሑፉን ልሳነ ግእዝ ለማያውቅ ሰው አስቸጋሪ፣ ለሚያውቅም ስሕተት በማረም እንዲጠመድ የሚያደርጉ ሆነው ቀርበዋል፡፡

ከላይ ያሉት ነጥቦችን በማስተዋል ይዞ፣ ማንኛውም በምሥጢረ ሥላሴ ዙሪያ ጠለቅ ያለና ዐውዱን የጠነቀቀ ንባብ የሚፈልግ ሁሉ ቢያነበው ይጠቀማል፡፡ ርእሱን ጠብቆ በሚያቀርበው ትንተና፣ በቋንቋና ምንጭ አጠቃቀሙ፣ የርሱን ክብደት ተረድቶ ዝቅ ባለና በተቻለ መጠን ከግላዊ ብይን ራቅ ባለ አቀራረቡ ካስደመሙኝ መጻሕፍት መካከል መሆኑን ሳልናገር ባልፍ ራሴን መዋሸት ይሆንብኛል፡፡ አንዳንድ መጣጥፎችና መጻሕፍት ላይ ለጸሐፊው ዕውቅና ሳይሰጥና ምንጭ ሳይጠቀስ የመጽሐፉ ሐሳብ እየተቦጨቀ መወሰዱን  ታዝበናል፡፡ መጽሐፉን ተራምዶ በመጽሐፉ የተጠቀሱትን ምንጮቸ በራስ ንባብ እንደ ተገኙ አድርጎ በቁማቸው የመውሰድ ጸያፍም አለ፣ ይሄ በቤታችን የተለመደ ጸያፍ ነው፣ በሌሎችም ቤቶች አለ፡፡

ማስታወሻ፡- የተጠቀምኩት የ2012 ዕትሙን (2ኛ ዕትም) ነው፡፡


Post a Comment

0 Comments