✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
አባቶቻችን ካስተማሩን፣ ካወረሱን ከእሴታችን ውጪ ክርስትናችን ያልጮች እንዲኾን፤ አንድም “ያልጮች የኾነን ክርስትናን “ የሚግቱን እነርሱ ማንም ቢኾኑ የጠላት መሣሪያ ምንደኞችም ናቸው!
የአባቶቻችን ክርስትና በሰይፍና በደም የተረጋገጠ፣ ንግሥናን ከቅስና አጣምሮ የያዘ የጀግኖችና የባለ ግርማዎች ርስት ነበር። ይህ ርስት ግን አሁን በምንደኞች እጅ ወድቆ፣ ትውልዱን ለባርነት የሚያመቻች “ያልጫ ክርስትና” ኾኖ ቀርቧል።
እምነታችን ጣዕሙን አጥቶ “አልጫ” እንዲኾን፣ ክርስትናችንም “ያልጮች” እንዲባል የሚያደርጉት እነዚህ “ባፍጢም የተደፉ” ምንደኞች፣ ትውልዱን ከማምከንና አባወራነትን እንደ ወንጀል ከማስቆጠር ውጪ ሌላ ተልዕኮ የሌላቸው የጥፋት መላእክተኞች ናቸው።
ይህ በዘመናችን ባሉት ምንደኞች የሚነገረው ክህደት ከአባታችንና ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ፍቅርን ከኃይል ጋር አጣምሮ የያዘውን የጀግኖችን እምነት አርክሶ፤ ጠላት እሴትህን ሰርዞ ትውልድን ሲያጠፋ “ዝም በል፣ ታገስ፣ አንገትህን ስጥ” የሚል የባርነት ቀንበር መጫኑ ነው።
ለእውነት መቆምን እንደ “ትዕቢት”፣ ለሀገርና ለቤተሰብ ክብር መጨከንን እንደ “ዓለማዊነት” በመሳል፣ ትውልዱን ማንኛውም ባዕድ ርዕዮተ-ዓለም እየረገጠው፣ እየሸቀጠው፣ እያጠፋውም እንዲያልፍ አመቻችተውለታል።
ይህ ከእኛ ማንነትና ትውፊት የወጣ ስብከት ትውልዱን “ልብ-አልባ” እና ወኔ-ቢስ አድርጎታል። አባቶቻችን በፈጣሪ ፊት ትሑታን፣ በዐመፅና በክህደት፣ በሐሰትና በኢፍትሐዊነት ፊት ግን እንደ አንበሳ ግርማ ያላቸው ነበሩ።
የዛሬው ትውልድ ግን በዚህ “ባልጮች ያልጮች” ስብከት ተለክፎ፣ የአባቶቹን የአባቱንም ግርማ ጥሎ፣ የማርክሳውያንን ሸፍጠኛ የ”ብሶት” ትርክት ተቀብሎ ለባርነት ይስማማል።
ለጽድቅ የሚጨክን ልብ ስለሌለው፤ አንድም ለጽድቅ የሚጨክን ወኔ እንዳይኖረው ስለተሰለበ በስሜትና በጩኸት፣ በለቅሶና በመነፋረቅ እንጂ በእውነትና በጽናት አይመራም።
ይህ ትውልድ አካሉ እንጂ ወኔዉ የሌለው፣ ለቤተሰቡና ለክብሩ ጋሻ መኾን የማይችል “ጃንደርባ” ኾኖም ከባርነት ወዲያ እንዳይጠቅም እንዳይረባም ተሰልቦ እንዲቀር ተፈርዶበታል።
ይህን ወኔ-ሰላቢና ልብአጥፊ ትምህርት የሚግቱን አካላት፣ የኢትዮጵያን የማኅበራዊ መሠረት ለመናድና ትውልዱ ለምዕራባውያን ስብከቶች ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ “ስልብ” እንዲኾን የሚተጉ ምንደኞች ናቸው እንጂ እንዲህ ዓይነት እሴት የለንም፣ አልነበረንም፣ አባቶቻችንም አላሳዩንም።
ወንድምዓለም! አባቶችህ ያስረከቡህ ክርስትና የኃይል፣ የግርማና የመስዋዕትነትም እንጂ የአቅመቢስነት፣ የአላዝኝ፣ የነፍራቃ፣ የአስመሳይነትና የጃንደርባነትም አይደለም።
“ያልጮች” የኾነውን፣ ወኔህን የሚሰልበውንና አንገትህን የሚያስደፋውን፤ የምንደኞች ስብከት አውግዘህ ትፋው! ወደ ቀደመው የአባወራነት የአባቶችህም ግርማና ክብር ተመለስ! አለበለዚያ ግን ሲገፉህና ሲደፉህ፣ ሲረግጡህና ሲያጠፉህ፣ ትውልድህ ሲጠፋና ማኅበረሰብህም ሲመክን “ጸጥ፣ ዋጥ፣ ስልቅጥ”!
ትውልድ የሚድነው ጽድቅን መፈጸም በማያስችለው፣ ለባርነት በሚያመቻቸው፣ ይህንንም አጽድቆ በሚግተው “ያልጮች ክርስትና” ሳይኾን እንደ አባቶቹ በእምነቱና በእሴቱ ላይ በእውነት ጸንቶ የሚቆም ልባም በሚያደርገው ብቻ ነው።
አልጫ አትኹን፤ ጨው እንጂ!
ጃንደርባም አትኹን፤ አባወራ እንጂ!
ልብ አልባም አትኹን፤ ልባም፣ ሰው፣ የሰው ልክም እንጂ!
0 Comments