እንኳን በጨለማ በብርሃንም ለመመላለስ ድፍረት ይጠይቃል!


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ዓለምን መመርመሪያ ብርሃን-እውቀቱ በሌለበት ጨለማ-መሃይምነት ፍርሃት ቢነግሥ አይገርምም፤ ብርሃን-እውቀቱ በፈነጠቀበት ለሚሰጋው ግን ልብ-አልባነቱ ይገለጥበታል!

ትውልዱ ለጽድቅ መጨከን የማይችል ወኔ-ቢስ ኾኖ መጥፋቱ የተሰበከለት ክርስትና “ያልጮች” በመኾኑ ነው። እንከፍነት፣ ምስኪንነት፣ አስመሳይነትና አድርባይነት፣ ጃንደርብነትም እንደ መንፈሳዊነት፤ አልጫነትም እንደ ጽድቅ ተግቷል። “ዋነኞቹም” እንዲያ እየኖሩና እያሳዩት ስለኾነ፣ ያወቀውን እውነት ለመኖር የሚያስችል ልብ፣ ወኔ፣ ጭካኔ አጥቷል።

በተገላቢጦሽ ትርጉም “ትሕትና” የተባለው እንከፍነት፣ ትውልዱን ለክፉ ነገር ምላሽ የማይሰጥ ሽባ ሲያደርገው ካለዐውዱ አውጥተው የሚተረጉሙትን “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ሲጨምሩበትማ ባርነቱ ይታተማል።

ለጥፋት የማይቆጣ፣ ክፋትን የማይቀጣ፣ ለቤተሰቡ መሠረት የማይቀና፣ በእሴቱ የማይኮራ “ምስኪንነቱን” እንደ ጽድቅ የቆጠረ ትውልድ፣ የጠላት ምርጥ መሣሪያ ነው። “የጠላት ምርጥ መሣሪያ ነው” ስል ጠላት ሊያጠፋ አልያም በባርነት ሊነዳ የፈለገውን ይሄንኑ ትውልድ አስቀድሞ በጠፋበት በራሱ ልብ ተጠቅሞ ያጠፋዋል ስል ነው።

ይህ ካስመሳይነት ርቆ፣ ያባቶቹን ፈለግ ጠብቆ ያልተገኘው ክርስትና፣ ወጣቱን ለጽድቅ የሚጨክን ወኔ ሳይኾን፣ ለባርነት የሚመች አድርባይነት አጎብዳጅነትን አውርሶታል።

ክርስትና በመሠረቱ ሰውን ጽኑ ያደርጋል፣፤ እውነትን እንዲይዝ ያስተምራል፤ ክፋትን እንዲቃወም ያነሳሳል፣ በሰውነት ያሠለጥናል ከዚያም ለጽድቅ አስጨክኖ እስከመስዋዕትነት ልኩ፣ ጥጉ፣ ማማው ያደርሳል። ነገር ግን በብዙ መድረኮች የሚነገረው፣ የሚታየውም ይህ አይደለም።

👉 እንከፍነት እንደ ትሕትና ተቀርቧል፤

👉 ምስኪንነት እንደ መንፈሳዊነት ተገልጧል፤

👉 አስመሳይነትና አድርባይነት እንደ ጥበብ ቀርበዋል፤

👉 አልጫነትም እንደ ጽድቅ ተሰብኳል፤

👉 ጃንደርብነትም እንዲሁ!

👉 እውነትን በድፍረት መናገር እንደ ክፋት፤

👉 ክፋትን መቃወም እንደ ግጭት፤

👉 በጽድቅ ላይ መጨከን እንደ ጭካኔ ተቆጥሯል።

እነዚህ ለዘመናት በስብከትና በመዝሙር ከትውልዱ ልብ የአባቶቹን ፈለግ አጥፍተውበታል፤ አንድም የትውልዱን ልብ ከአባቶቹ ዳና አርቆት ወኔውን አጥፍቶታል። ለእውነት መቆም የሚያስፈልገውን ጭካኔ ከልቡ ደምስሶታል።

🚨🚨🚨 ከዚህም የከፋው፣ የሚከፋውና ክፋቱንም በተጨባጭ ያየን የመሰከርነው ነገር ዋነኞቹ ራሳቸው እንዲህ እየኖሩ መታየታቸው፣ ማሳየታቸው ለአልጫነቱም አርአያ መኾናቸው ነው።

🎯 እውነትን ያውቃሉ ግን አይናገሩም፤

🎯 ክፋትን ያያሉ ግን አይቃወሙም፤

🎯 ትውልድ እየተበላ ሲሄድ ዝም ብለው ይመለከታሉ።

እውቀትን ይዞ፣ እውነት ላይ ደርሶ በዚያ ለመኖር ግን ድፍረቱን ላጣው “ሊቅ” ለትውልዱ መጥፊያ ምክንያት ብቻ አይደለም የሚኾነው፤ የጥፋቱንም ዘር በልቡ ይዘራበታልም እንጂ።

ራሱን እንደ ሊቅ ቢቆጥርም፣ ቢኾንም፣ ነውም፤ ለጽድቅ የጨከነ ልባም ግን አይደለምና የማሰማሪውን በጎች ልብአልባ፣ ወኔቢስ፣ ስልብ፣ ድልብ፣ ሙክት አድርጎ ለጥፋታቸው ያሰባቸዋል።

እውነትን ለጥቅም መሸጥ መለወጥ፣ ለጥፋት ሸፍጥ ዐይንን መጨፈን፣ እንደ “መንፈሳዊ ብልሃት” ተቆጥሮ በተስፋፋበት ባርነት ሲመጣ አደግድገው ይቀበሏል እንጂ አያዝኑም፣ አያለቅሱም፤ የእጅ ፍሬ ነውና!

“ዋነኞቹ” የተባሉት እረኞች በእውነት ላይ ጨክነው መቆም ሲያቅታቸው፣ ተከታዩም “የተማረ ፈሪ፣ ምሁር አልጫ፣ የፍየል ሙክት” ኾኖ ጽድቅ ባልሠራበት እውቀት-ብልሃቱ መሰለቡ ለጥፋት ለውድቀቱ መስባቱ እርግጥ ነው!።

ዓለምን መመርመሪያ ብርሃን እውቀቱ በሌለበት ድቅድቁ ጨለማ-መሃይምነት ፍርሃት ቢነግሥ አይገርምም፤ ብርሃን-እውቀቱ በፈነጠቀበት ለሚሰጋው ግን ልብ-አልባነቱን ይገልጣል።

እውቀት የዓይን ብርሃን ነው፤ እውነት ግን የልብ! መረጃው እያለው፣ አሠራሩ ተገልጦለት እያለ የሚሰጋና የሚሸሽ “የተማረ ትውልድ”፣ እውቀቱ ለባርነት ያመቻቸው፣ በልቡም በእውነት የተመሰለ ውሸት የተዘራበት፣ አእምሮው ብቻ የተሳለ “ሊቅ” ነው።

አባቶቻችን በተሰጣቸው ጸጋ ላይ ሠልጥነው፣ በእውነት ላይ ተተክለው በሄዱበት መንገድ ለትውልዱ መውረጃ ጅረት ነበሩ።

ይህንን የተረዱ፣ ያመኑ፣ የተከተሏቸውም ልጆቻቸው ፈለጋቸውን ይዘው፣ ዳናቸውን ተከትለው ከደረሱበት ደርሰው፣ ካረፉበት አርፈው፣ የበረከታቸው ተካፋይ ኾነዋል።

ይኹን እንጂ ያንን እሴት፣ እምነትና እውነት ንቆ፣ እርሱንም ለቆ፣ በባዕድ መንገድ ርቆ ለሄደው የዘመኔ ትውልድ ምን ቢማር ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንትም ቢኾን ለጽድቅ መጨከን የማይችል፣ ልባልባ፣ ወኔቢስ፣ አልጫ፣ አስመሳይ፣ አድርባይ ኾኖ በባርነት መጠናቀቁ፣ መጥፋት መምከኑም ጭምር የማይቀር ነው።

አንድም የዛሬው ትውልድ የቱንም ያህል ሊቅና ሊቀ-ለቃውንት ቢባል፣ ለጽድቅ መጨከን የማይችል ልበ-አልባ ወኔቢስ ኾኗል።

ለምን?

ጽድቅ የሚሠራበትን ድፍረት፣ ጭካኔ፣ ወኔ፤ የሚሰጠው ልብ-ብልቱ(organ) አባቶቹ ቀድመው በሄዱበት፣ ውጤታማ በኾኑበት፣ ማንነታቸው በተበየነበት እውነት፣ እምነት፣ እሴት አልታረሰም፣ አልተኮተኮተም፣ አልታረመምና!

በሰሙት እውነት፣ በእምነት ለመኖር ድፍረት እንጂ ሊቅነት አይጠይቅም፤ እውነትን ይዞ በፍርሃት ተሸብቦ መደበቅ ግን ካለማወቅ የከፋ ጥፋት አጥፊነትም እንጂ ነው!

የአባወራው ንቅናቄ ይህን የትውልዱ ሰውነት ልማት ብልጽግናው የሚበየንበትን እውነት፣ እምነትና እሴት በወሬ ሳይኾን በተግባር እየዘራ፣ የባርነትንም ሠንሰለት እየበጣጠሰ ወንዱን ወደ ልቡ አባወራውን ወደ ክብሩ ይመልሳል!‼💪


Post a Comment

0 Comments