ራስን በማምከን ከወንድ “እኩል” ለመኾን


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

“የጾታ እኩልነት” በአባወራው ስም ይሳበብ እንጂ “ሴቶችን በድሏል” የተባለውን መልካሙን፣ ውቡን ተፈጥሮአቸውን ጠልቶና አስጠልቶ አስቀርቶም ወንዱን “ለመኾን”፣ ሲቀጥልም ጾታን ለመሻር የመጣ ነው!

ይህ “እኩልነት” የተባለ መርዝ ሴቶቻችን ከወንድ ጋር እኩል እንዲኾኑ በሚል፣ ወንድን እንዲመስሉና የገዛ ሴትነታቸውን እንዲጠሉ የሚገፋፋ ባዕድ ፍልስፍና ነው።

እህቶቻችን “ከወንድ እኩል ናችሁ” በሚል የሐሰት ተስፋ እየተደለሉ፣ እንደ ወንዱ ወጥቶ ለመግባትና በውጭው ዓለም ስኬታማ ለመኾን ተፈጥሮአዊው ማንነታቸው እንደ እንቅፋት ተደርጎ ተሰብኮላቸዋል።

በትምህርትና በሥራ ለመትጋት እንቅፋት ነው ተብሎ የተነገራቸው ያ ታላቅ የእንክብካቤ፣ የመግቦትና የሕይወት ምንጭነት ሚናቸው፣ ለእርሱም የተሰጣቸውን ጸጋ ነው። ይህንኑ ሚና ይወጡበት ዘንድ የተሰጣቸውን የሴትነት ጸጋ ሁሉ ክደው ለማጥፋትና ራሳቸውን ለማምከን ሌት ተቀን ይደክማሉ።

የገዛ ተፈጥሮን የመጥላትና የማጥፋት ዘመቻው የሚጀምረው ከማኅፀን ነው። እርግዝናን ለማስቀረት በየቀኑ መድኃኒት ከመዋጥ ጀምሮ፣ ተፈጥሮአዊውን የዘር ፍሬ ማምረቻ ማኅፀንን ያስራሉ።

እርግዝና በድንገት ቢፈጠር እንኳ፣ ያንን በማኅፀን ውስጥ የተጠነሰሰ ሕይወት በመርዝ በጣጥሶ፣ በመቀስ ቆራርጦና እንደ ቆሻሻ ጠርጎ በማስወገድ “ነፃነትን” ፍለጋ ይባዝናሉ።

ሕፃናት ቢመጡም እንኳ፣ ያንን ተፈጥሮአዊ የኾነውን የምጥ ጣርና በዚያ ውስጥ የሚገኘውን የእናትነት ቁርኝት ሽሽት፣ በራስ ፈቃድ በመቀስ ተሰንጥቆ መውለድን እንደ ሥልጣኔ ቆጥረውታል።

የትውልድ ቀጣይ የኾኑትን ሕፃናት ደግሞ ገና ሳያድጉ ከሕፃናት መቆያ በመጣል፣ እናትነትን በማምከንና ጭርሱን እንዲጠፋና ከትውልዱ እንዲረሳ ያደርጋሉ።

ይህ ሁሉ የጥፋት እርምጃ የራስን ተፈጥሮ ክዶና ንቆ፣ ወንዱ “በአባቱ በአድልዎ ሰጥቶታል” ብለው ከሚያስቡት ወንድነት ለመድረስ የሚደረግ ከንቱ ሩጫ ነው።

ሴትነትን በማጥፋት ወንድን ለመምሰል መሞከር ተፈጥሮን መቃወም ብቻ ሳይኾን፣ ፈጣሪ በጥንቃቄ የሰፋውን የማንነት ልብስ መቀደድ ነው።

ዛሬ እህቶቻችን ሴትነት ተፈጥሮአቸውንና በዚያ ውስጥ ያለውን ታላቅ ሚናቸውን እንዲጠሉ፣ በምትኩም ትምህርትና ሥራን እንደ ብቸኛ የክብር ምንጭ እንዲያመልኩ እየተነገራቸው ያድጋሉ። ትምህርትና ሥራ ለሴት ልጅ ተፈጥሮዋን የምታጠናክርበት ሊኾናት ሲገባ፣ ዛሬ ግን ተፈጥሮዋን የምታመክንበትና ራሷን የምትክድበት፣ ትውልድንም የምታጠፋበት መሣሪያ ኾኖባታል።

አባወራነትና እመቤትነት ተደጋጋፊና ተመካካሪ የቤትና የሀገር አውታሮች ነበሩ። ዛሬ ግን ሴትነትን በማጥፋት የሚመጣ “እኩልነት” ትውልዱን እናት-አልባ፣ ቤቱን ደግሞ መግቦትና ርኅራኄ የራቀው ባዶ ቤት እያደረገው ነው።

ራስን በማምከን የሚገኝ እኩልነት የለም፤ ይልቁንስ ራስን አጥፍቶ በባዕድና በማይስማማ ማንነት ውስጥ ለመኖር መሞከር የሞት ሞት ነው። ሴትነትን ማክበር ማለት ተፈጥሮዋን፣ ፈጣሪዋንም ማክበር ነው፤ ራስን በመድኃኒት በማምከን፣ የሕጻናት ነፍስን በማጥፋት ወንድ ለመኾን መሞከር ግን የራስን ማንነት ክዶና ጠልቶ መጥፋት ነው።

Post a Comment

0 Comments