መንግሥት ምን ታላቅ ቢኾን ቤተሰብን አይተካም!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

የወላጆችን ሚና፣ የቤተሰብን ድርሻ በየትኛውም አሳማኝ በሚመስል መልኩ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ትውልድን ከእሴቱ ቢያጠፋ፣ ሀገርንም ቢያፈርስ እንጂ አይታደግም!

የትኛውም የምገባ መርሐ-ግብር፣ የሕፃናት ማቆያና ትምህርት ቤት ዓላማው ልጆችን ከወላጆቻቸው ጉያ ለመንጠቅና በባዕድ አስተሳሰብ ለመቅረጽ ከኾነ፣ ያ ተቋም የትውልድ ማጥፊያ እንጂ የዕውቀት ማከማቻ አይኾንም።

ዛሬ “መንግሥት ያበላል፣ መንግሥት ያሳድጋል፣ መንግሥት ያስተምራል” በሚል ድንዛዜ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ተፈጥሮአዊ ኃላፊነት አሳልፈው እንዲሰጡ “ደመወዝ ከማይከፈልበት የቤት ውስጥ ሥራና እንክብካቤ” ሴቷን “ነፃ ማውጣት” በሚል እየተገፉ ነው። ይህ ግን ትውልዱን መረን የሚያወጣ፣ ሥር-አልባ፣ ትውፊት አልባ የሚያደርግና የሀገርን መሠረት የሚንድ አደገኛ አካሄድ ነው።

ምገባና እንክብካቤ ሰብአዊነት ቢመስሉም፣ ከወላጅ ፍቅርና ከቤት ማዕድ የተለየ ማንኛውም ግብረ-ሰናይነት ትውልዱን ለባርነት የሚያመቻች “ማደንዘዣ” ነው።

ልጅ ከእናቱ ጡት፣ ከአባቱ ምክርና ከቤተሰቡ እሴት ተነጥሎ በሕፃናት ማቆያ ውስጥ ሲታጎር፣ የሚያድገው እንደ ሰው ሳይኾን እንደ ማሽን ልብአልባ ኾኖ ነው።

ለዚህ ደግሞ ትልቁ ማሳያ “ሠለጠኑ” የሚባሉትና ልጆቻቸውን በሕፃናት ማቆያና በመንግሥት ተቋማት ያሳደጉት ምዕራባውያን ሀገራት ዛሬ የደረሱበት ቀውስ ነው።

እነዚህ ሀገራት ልጆቻቸውን ገና በለጋነታቸው ከቤት ማዕድና ከወላጅ ርኅራኄ ነጥለው፣ አምራች ዜጋ እንዲኾኑ ለባርነት የተመቹ አድርገው በተቋማት ውስጥ አሳድገዋል።

ውጤቱ ግን ዛሬ በግልጽ እንደሚታየው ትውልዳቸው እየጠፋ፣ ማኅበረሰባቸው ደግሞ እየመከነ መምጣቱ ነው። ከእውነትና ከእምነት፣ ከቤተሰብ እሴትና ከማንነት ተነጥሎ ያደገ ትውልዳቸው “ልብ-አልባ” ኾኗል። ለወላጆቹ የማይራራ፣ ለሀገሩ ግድ የሌለውና ለባህሉ ባይተዋር የኾነ ትውልድም አፍርተዋል።

እነዚህ ሀገራት ዛሬ የቤተሰብ መፍረስ፣ የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ የባዶነት ስሜትና የማንነት መጥፋት ሰለባ ኾነዋል። ልጆቻቸውን ለመንግሥት አሳልፈው የሰጡ ወላጆች፣ መንግሥት ልጆቻቸውን ወደ ታታሪ ማሽንነት ቀይሮባቸው፤ ዛሬ በእርጅና ዘመናቸው የሚጦር የሚንከባከባቸው አጥተው በብቸኝነትና በጭንቀት ይማቅቃሉ።

ትውልዱም ቢኾን የሚይዘውና የሚጨብጠው እሴት ስለሌለው፣ ለማንኛውም ሐሰተኛ ፍልስፍናና ለጠላት አጀንዳ ተገዥ ኾኗል። ይህ የማኅበረሰብ መምከን የሚጀምረው ልጆችን ከቤት ማዕድ ነጥሎ ለተቋማት አሳልፎ ከመስጠት ነው።

ቤተሰብ የማይገነባው ማንነት፣ በየትኛውም የትምህርት ሥርዓትና በመንግሥት ድጎማ ሊገነባ አይችልም። መንግሥት ሆድ ሊሞላ ይችል ይኾናል፤ የልጅን ነፍስና ማንነት፣ ስብዕናም ግን የሚሞላው ቤተሰብ ብቻ ነው።

ዛሬ በምዕራባውያን ጫና በራሳችንም ሆዳደር ልሂቃንና ሊቃውንት ትምህርት ቤቶችና ማቆያዎች የወላጆችን ቦታ ተክተው ሕፃናትን በባዕድ ፍልስፍና ሲበክሉ ዝም ሊባሉ አይገባም።

ወላጅ የልጁ ቀዳሚ መምህር፣ ጠባቂና መጋቢ መኾኑ ሲቀር፣ ትውልዱ ለመንግሥት አድርባይና ለባዕዳን ትርክት ተገዥ ይኾናል። ይህ ደግሞ መረን የወጣ፣ ለባህሉ ባይተዋር የሆነና የሞራል ልጓም የሌለው ትውልድ ያፈርሳል። ሀገር የምትቆመው በጠንካራ ቤተሰብ እንጂ በመንግሥት የሕፃናት ማጎሪያዎች አይደለም።

ስለዚህ! መንግሥት የቱንም ያህል ቢበለጽግና ቢገዝፍ፣ የቤተሰብን ድርሻ ሊጋፋ አይገባውም። ሲኾን ልጆች ከወላጆች ጋር የሚኖሩበትን፣ ተጨማሪ ጊዜ የሚያሳልፉበትን ማመቻቸት አለበት እንጂ።

ወላጆችም የልጆቻቸውን ነፍስና ሥጋ ለተቋማት አሳልፈው በመስጠት የታሪክ ተጠያቂ መኾን የለባቸውም። ልጆቻችሁን ከቤታችሁ ማዕድ፣ ከእምነታችሁና ከእሴታችሁ አታርቋቸው። መንግሥት የቤተሰብ አገልጋይ እንጂ የቤተሰብ ምትክ ሊኾን አይችልም፤ ሊኾንም አይገባም!

Post a Comment

0 Comments