የፖርኖግራፊ ሱስና መጨረሻው

ከዓመታት በፊት፣ በጥንት ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች መንደሮቻቸውን ማጥቃት የሚመጡ ተኩላዎችን እንዴት እንደሚገድሉ የሚገልጽ አንድ ታሪክ ሰምቼ በጣም ተደንቄ ነበር።

በመጀመሪያ ትልቅና እጅግ በጣም ስለታም የሆነ ቢላዋ ያዘጋጃሉ፣ የቢላዋውንም ጠርዝ፣ ልክ እንደ ምላጭ እስኪሆን ድረስ ይስሉታል። ከዚያም ያንን እጅግ ስለታም ቢላዋ ወስደው በደም ውስጥ ይነክሩታል፤ ደሙ በረዶ ሆኖ የቢላዋውን ስለት እንዲሸፍነው በከፍተኛ ቅዝቃዜ ውስጥ ይተውታል። ከዚያም ድጋሚ ይነክሩታል፤ ሁለተኛው የደም ሽፋን በቢላዋው ዙሪያ እንዲቀዘቅዝ ያደርጋሉ። ከዚያም ለሶስተኛ ጊዜ ይደግሙታል፣ ያ ሶስተኛው ሽፋን በቢላዋው ዙሪያ በረዶ እስኪይዝ ይተዉታል፤ በመጨረሻም ልክ ከደም የተሰራ ፖፕሲክል (የበረዶ ከረሜላ) የሚመስል ነገር ያገኛሉ።

ከዚያም የቢላዋውን እጀታ ወደ መሬት ውስጥ ይቀብሩታል፣ ያ የበረዶ ደም የለበሰው ስለት ወደ ላይ ብቅ ብሎ እንዲታይ አድርገው ማታ ላይ ይተውታል። ለሊት ላይ ተኩላዎቹ በሚመጡበት ጊዜ፣ እጅግ በጣም የማሽተት ችሎታ ስላላቸው፣ ስለታም ወደሆነው በደም በረዶ ወደተሸፈነው ስለት ይሳባሉ፤  ከዚያም ምንም ሳይጠረጥሩ የደሙን በረዶ መላስ ይጀምራሉ። ምላሳቸውን ወደ ላይ እና ወደ ታች በማድረግ፣ ደጋግመው ይልሱታል። ትንሽ ቆይቶ፣ ያንን የደም በረዶ ልሰው በመጨረስ እጅግ ስለታም ወደሆነው ቢላዋ ጋር ይደርሳሉ፣ ከዚያም በዚያ ስለታም ቢላዋ ላይ ምላሳቸውን ወደ ላይ እና ወደ ታች ደጋግመው ማመላለስ ይጀምራሉ። ነገር ግን አስታውሱ፣ በምላሳቸው ውስጥ ያሉት የነርቭ ሴሎች በቅዝቃዜው ምክንያት ስለደነዘዙ፣ ምንም ዓይነት ስሜት አይሰማቸውም። ስለዚህ ይህንን እጅግ ስለታም ቢላዋ ደጋግመው መላሳቸውን ይቀጥላሉ።

ምላሳቸው መድማት ሲጀምር፣ የራሳቸውን ደም ማሽተት ይጀምራሉ፣ ነገር ግን የራሳቸው ደም መሆኑን እንኳን አያውቁም። ይህ ሁኔታ ወደ እብደት ይመራቸዋል፣ እናም ይበልጥ በፍጥነት፣ በፍጥነት ይልሳሉ... ምላሳቸው በዚያ ራቁቱን በሆነ ስለታም ተቆራርጦ ያልቃል፣ በመጨረሻም ዞሮባቸውና ደማቸው ፈሶ ይሞታሉ።

ይህ ታሪክ፣ በ ፖርኖግራፊ ሱስ ለተጠመዱና፣ ራሳቸውን ለተደጋጋሚ ፍትወትና ለወሲባዊ ኃጢአት አሳልፈው ለሰጡ ሰዎች፣ የንፍሳቸው መጨረሻ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው።

«“አታመንዝር” እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል። ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከጥንቶችህ አንዲቱ ብትጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከብልቶችህ አንዱ ቢጠፋ ይሻልሃልና።» 
(ማቴዎስ 5:27–30)

ይህ ጥቅስ ስለ ኃጢአት አሳሳቢነት እና ስለ መንፈሳዊ ጥንቃቄ ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላልፋል። ኃጢአት በድርጊት ከመገለጹ በፊት በልብ ውስጥ እንደሚጀምር ያስገነዝበናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ክፍል ሲያስተምር፤ ትኩረት ያደረገው ከውጫዊ ድርጊት ይልቅ በውስጣዊ ፍላጎት ላይ ነው። ዝሙት የሚጀምረው በአይን እና በሃሳብ ነው። በምስል ወይም በሃሳብ የሚመጡ ፈተናዎችን ገና ወደ አእምሮአችን  ሲገቡ "አይሆንም" ማለት። ሃሳቡ በልባችን ውስጥ ስር እንዲሰድ ዕድል አለመስጠት ትልቅ ተግባራዊ እርምጃ እንደሆነ ያስረዳናል። "ዓይንህን አውጣ" እና "እጅህን ቁረጥ” የሚሉት (Radical Measures)  ኢየሱስ ክርስቶስ አካላዊ አካሎቻችንን እንድንጎዳ ሳይሆን፣ ኃጢአትን ለማስወገድ መወሰድ ያለብንን ቆራጥ እርምጃ ለመግለጽ የተጠቀመበት ዘይቤ ነው።

ለምሳሌ፦

የተወሰኑ ድረ-ገጾችን ወይም ማህበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀም ማቆም።

ብቻችንን ስንሆን ለፈተና የሚያጋልጠንን ስልክ ወይም ኮምፒውተር ከክፍል ውጭ ማቆየት።

ጓደኞቻችን ለዚህ ክፉ ልማድ የሚያጋልጡን ከሆነ ያንን ግንኙነት ማቋረጥ እና ሌሎች ለራሳችን የሚገቡንን መሠረታዊ እርምጃዎችን መውስድ ናቸው።

በመጨረሻም ይህ ክፍል "ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል" በማለት ጊዜያዊ ደስታ ከዘላለማዊ የንፍሳችን ጥፋት ጋር ጨርሶ እንደማይወዳደር ያስረዳል።

ፖርኖግራፊን መመልከት ትንሽ በትንሽ ሲጀመር፣ ምንም ጉዳት የሌለው፣ ጊዜያዊ የወሲብ ስሜትን ማምለጫ  ልምምድ ብቻ ይመስላል፣ ነገር ግን ቀስ በቀስ ሳይታወቅ ያደነዝዛል፣ ደስ በሚል መነሳሳት ስሜት ውስጥ ሆናችሁ ነገር ግን ነፍሳችሁን ቆራርጦ ወደ ዘላለም ሞት ከሚወስዳችሁ ክፉ ልማድ ተመለሱ። 

Post a Comment

0 Comments