ለንግሥና እንጂ ለጉስቁልና አልተፈጠርክም!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ለንግሥና የተፈጠረው ወገኔ ጉስቁልና ጸድቆለት፣ በባርነት መነዳት ከብሮለት፣ ጃንደርቅነት ባርነቱ ተቆለጳጵሶለት በሀገሩ፣ በመሬቱ፣ በሰውነቱ ባይተዋር ኾኖ ይኖራል።

ለንግሥና የተፈጠረው ወገኔ፣ ዛሬ ጉስቁልና ጸድቆለትና በጃንደርብነት በባርነት መነዳት ከብሮለት ወደ ግዞቱ “በደስታና በእልልታ” ሲፋጠን ይታያል።

ያ ያባቶቹ የነፃነት ወኔ ርቆት፣ ጃንደርባነትና አድርባይነት እንደ ጌጥ ተቆልጳጵሰውለት፣ በገዛ ሀገሩ፣ በገዛ መሬቱና በገዛ ሰውነቱ ላይ ባይተዋር ኾኖ ይኖራል።

ታናሼ! ንጉሥ ማለት ሀገርና መሬቱን፣ ድንበርና ክልሉን፣ ሕዝብና ወገኑን፣ ባህልና እምነቱን፣ ወግና እሴቱን የሚያቀና፣ የሚያለማ፣ የሚያበለጽግና የሚያሰፋ ኃያል ነው።

ይህንኑ ክብር ለሚተካው ትውልድ አሳስቦና አውርሶ ያልፋል። ንጉሥ ይህን ሁሉ ሲሠራ መንገዱ አልጋ ባልጋ እንዳልኾነ ያውቃል። ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከሚመጣበት ተቃውሞና ጦርነት ጋር ይጋፈጣል፤ የእርሱ የኾኑትን ሁሉ በነፍሱ ተወራርዶ ይጠብቃል፣ ያስጠብቃልም።

ላንተም ሰውነትህ የምትሰለጥንበትና የምትነግሥበት መሬትህ ነው! ልትጠብቀው የሚገባህ ድንበርህ፣ ልታሳድገውና ልትገነባው የሚገባህ ርስትህ ነው። ንጉሥ በገዛ ሀገሩና በመንደሩ ካላየለና ካልከበረ የትም ሄዶ ሊከበር እንደማይችል ሁሉ፤ አንተም በሰውነትህ ላይ ካላየልክበትና ካልከበርክበት በማንም ላይ አትከብርም። ሰውነትህ ከማንምና ከምንም በፊት ልትሰለጥንበት የሚገባህ ብቸኛ ሀገርህ ነው! ልታውቀው፣ ልትገዛው፣ ልታሳድገውና ወደ ጽድቅ ልትመራው የተገባህም አንተው ነህ!

ነገር ግን ዛሬ የምናየው ተገላቢጦሹን ነው። ብዙዎች ሰውነታቸውን ንቀውታል፣ ጠልተውታል፣ ለባዕድ ርዕዮተ-ዓለምና ለዝቅጠት አሳልፈው ሰጥተውታል። አንተ ያልከበርክበትንና ያልገዛኸውን የሰውነትህን ሜዳ ማንም በባርነት ቢገዛው፣ ቢነዳው ቢያዝበት አንተ መዋረድህ እንጂ መክበርህ አይደለም።

ይህንን የመሰለ ድንቅ፣ ብርቅና ጥንቅቅ ያለ ውብ ሰውነት ለሰጠህ አምላክ ፊት ስጦታውን ንቆ መጣል ትልቅ ውርደት ክህደትም ነው።

በዚህም መኔገድ በሀገር-ሰውነታቸው ላይ ነግሠው ጽድቅን ሊፈጽሙ ሲገባ፣ ራሳቸውን አግሳቁለውና አምክነው የሚያጠፉ ምስኪን ወገኖቻችን ግን ተበራክተዋል።

ተፈጥሮአዊ ወኔያቸውን ለምስኪንነት፣ ንግሥናቸውን ለባርነት፣ ግርማቸውን ለውርደት አሳልፈው ሰጥተዋል። በገዛ ማንነታቸው፣ ተፈጥሮአቸው፣ ሰውነታቸው፣ ወንድነታቸው ላይ ባይተዋር ኾነው፣ የባዕዳን ትርክትና የውሸት ማዕድ መርጠው አላፊና አሳላፊ ለመኾን መምረጣቸው የሞት ሞት ነው!

ሰውነትህን ልትንቀው፣ ልትጠላውና ልትጠየፈው የፈቀድክ ዕለት፣ ንጉሥ የገዛ ሀገሩን ከመጠበቅና ከማስጠበቅ ትቶ የተሰደደ’ለት ሀገሩ የሚኾነውን አስብ!

የገዛ ግዛቱን አሳልፎ እንደሚሰጥ አንተም ለስሜትህ ባርነት ተላልፈህ ትሰጣለህ። አንተ ያልከበርክበትን ሜዳና ድንበር ማንም በባርነት ቢገዛው አይገርምም፤ አንተም ተጎሳቁለህ፣ ተሸማቀህ፣ ተሳቀህ ትዋረድበታለህ እንጂ አትከብርበትም!

🚨 ማን ነህ አንተ እግዚአብሄር ከእንሰሳት አክብሮ፣ ከፍጥረታት ለይቶ፣ በራሱ አምሳያ ቀርጾ በሰጠህ ሰውነት ተፈጥሮህን ተመጻድቀህ የምትጥለው?

ታናሼ! ንግሥ በሀገሩ ለመንገሥ መጀመሪያ የእኔ ብሎ ሊጠራው፣ ሊወደው፣ ሊቀበለው ይገባል። የሚነግሥበት ደግሞ ተበጃጅቶ ሲያልቅ ሳይኾን እንደው አበጃጅቶ ሊጸድቅ ነው እንጂ።

ንግሥናህ የሚጀምረው ከውስጥህ ነው፤ በስሜትህ፣ በአእምሮህና በወኔህ፣ በጡንቻህ፣ በብልቶችህ ላይ ስትነግሥ፤ ያንጊዜም ብቻ ነው ለውጭው ዓለም የምትተርፈው።

ዛሬ ግን ትውልዱ ራሱን መግዛት አቅቶት፣ ተፈጥሮውን እንደ ጠላት እየፈረጀ በገዛ እጁ ማንነቱን ሲያፈርስ፤ ይባስ ብሎም በመንፈሳዊነት ሲመጻደቅ እጅግ ያሳዝናል።

🚨 አባቶቹ ያልሄዱበትን መንገድ ጠላት አስቶ አሳይቶታል!

አንተ ለንግሥና የተፈጠርክ እንጂ ለጉስቁልና የታጨህ አይደለህምና፤ በአባቶችህ እሴትና በእውነትና እምነቱ በጽኑ መሠረት ላይ ቆመህ፣ በሀገር-ሰውነትህ ላይ ንገሥ።

የፈጣሪህን ስጦታ አክብር፤ ወንድነት መክሊትህን፣ አባወራነት ግዴታህን ለጽድቅ የምትሠማራበት መስክ፣ መሬት፣ ግዛት አድርገው።

በባርነት ከሚያጠናቅቅህ ደፈጃንደርብነትና ምስኪንነት ቀንበር ወጥተህ፣ ታሪክህንና ርስትህን የምታቀና ንጉሥ የንጉሥ ልጅ፣ ባለሥልጣንም ኹን!💪

አለበለዚያ ግን በገዛ መሬትህ ላይ ባይተዋር ኾነህ፤ በባርነት ልታድር በዚያም በብሶትና በለቅሶ፣ በምሬትና በሮሮ ማለቅህ አይቀሬ ነው።

ወንድምዓለም! እስቲ ራስህን አንዴ ተመልከት የተሰጠህን ድንቅ፣ ብርቅና ጥንቅቅ ያለ ውብ ማንነት ምን አደረግከው?

👉 “እውቀት መንፈሳዊነት” ብለህ በታበይክበት እብሪትህ አድቅቀህ አጎሳቆልከውን? ወይንስ አውቀህ ሠለጠንክበትን?

👉 ወይንስ “ደስታውን ልስጠው” ብለህ በአልኮልና በሌላም አጠፋኸው አመከንከውን?

🌟 አንተን ለክብር እንጂ ለውርደት፣ ለንግሥና እንጂ ለጉስቁልና ላልፈጠረህ አምላክ ክብር ስትል፣ በሀገር-ሰውነትህ ላይ ንገሥ፤ እንደ ንጉሥ ሥርዓትም ተመላለስ! ለንግሥና እንጂ ለጉስቁልና አልተፈጠርክምና!

🌟 የአባቶችህን መንገድ ፈልግ፣ ፈለጋቸውም ላይ ውጣ፤ ንጉሥ ኾነው እንዳለፉት ላንተም ንግሥናህ ይኾንልሃልና!

Post a Comment

0 Comments