ከመቅደሱ የተለየ ካህን፣ ከቤቷ የራቀች እመቤት


ማኅበረሰብን ለማፈራረሱ ሰይፍና ጦር አይመዙም፤ ይልቁንስ ትውልድ በሥነ-ሥርዓትና ሥነ-ምግባርና የሚታነጽበትን ቤተሰብ የምትሠራውን “ሴት” በእኩልነት ሰበብ ከቤቷ ያርቋል እንጂ!

ማኅበረሰብን ለማፈራረስ የግድ የጥይት ፉጨትና የመድፍ ግጭት አያስፈልግም፤ ቤቷን በመሥራት የምትታወቀውን “ሴት” ከቤቷ ማፈናቀል ብቻ በቂ ነው።

ትውልዷ የቆመው በእርሷ ትከሻ ላይ ነውና እርሷን ከመቅደሷ (ከቤቷና ከቤተሰቧ) ማውጣት፣ ማኅበረሰቡን ስርአልባ እንደማድረግ ይቆጠራል።

ከመቅደሱ የተለየ ካህን ክህነቱን፦ አገልግሎቱን፣ መስዕዋቱን የሚፈጸምበት ቦታ፣ አድራሻ ከሌለ እንደሚመክን ሁሉ፤ ከቤቷ የራቀች እመቤትም ማኅበረሰቡን ትውልድን ከምታንጽበት፣ ማኅበረሰብ ከምትገነባበት ቦታዋ የለችምና ለውድቀት ትዳርጋለች።

ሴትን ልጅ ከቤቷ ለማውጣትና መቅደሷን እንድትንቅ፣ እንድትለቅና እንድትርቅ የሚሰነዘረው ዋነኛው ስልት “በእኩልነት” ሰበብ የሚመጣው የማታለያ መርዝ ነው።

🚨 “ተበድለሻል፣ ተገፍተሻል፣ ተጨቁነሻል” ብሎ በማሳመን፣ የቤተሰብ ካህንነቷንና ለትውልድ የምታበረክተውን ቅዱስ ሚና እንደ “ባርነት” እንዲታይ ይደረጋል።

🚨 እመቤትነቷን ዝቅ አድርጋ እንደ ባርነት እንድታይ፣ መቅደሷንም እንደ እስር ቤት እንድትቆጥረው በምዕራባውያን ትረካ፣ ሆዳደር በኾኑ የሀገሯ ልጆች ጉትጎታ ትመታለች።

በዚህም ሴቷ ከቤተሰቧ ጋር ያላት ቁርኝት ይላላል፤ ትውፊታዊ ማንነቷም ቀልጦ ለማይወዳት፣ ለሚጠላት ጌታ ገባሪ ትኾናለች።

እመቤቷ ከቤቷ ስትለይና ከልጆቿ አስተዳደግ ስትነጠል፣ ትውልድ በሥነ-ሥርዓትና በሥነ-ምግባር የሚታነጽበት “የቤት ትምህርት ቤት” ይዘጋል።

ልጆቿ ለክፉ ምኞትና ለከንቱ ርዕዮተ-ዓለማት ሲጋለጡ “ቀላጭ” ትውልድ ይፈጠራል። እናት በሌለችበት ቤት የሚበቅል ትውልድ ማንነቱ የሚገነባበትን የፍቅር መሠረት በማጣት ይቸገራል። ከመቅደሱ የተለየ ካህን ትውልዱን ማጥመቅ እንደማይችል ሁሉ፣ ከቤቷ የራቀች እናትም ትውልዱን መቅረጽ አትችልም።

ሴትን ልጅ በጅምላ ወደ ገበያው መግፋት ሌላኛው ምስጢራዊ ስልት ነው። ይህ ስልት የሥራ ክፍያን ዝቅ እንዲል በማድረግ አባወራው ቤቱን የሚተዳደርበትን አቅም ያሳጣዋል።

ውጤቱም ሥራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና ማኅበረሰባዊ ውጥንቅጥ ነው። ቤተሰብን በማፍረስ ኢኮኖሚን ማናጋትና ማኅበረሰቡን ለውድመት ማዘጋጀት ደግሞ የጥፋት ኃይሎች ዋነኛ ግብ ነው።

ይህንን የጥፋት ስልት ለመመከት የትውልዱን፣ የማኅበረሰቡን፣ የቤተሰቡን፣ የሚስቱን፣ የልጆቹን ጠባቂ አባወራውን ማጽናት የግድ ነው። አባወራው ቤቱንና ባለቤቱን ከባዕዳን ሸፍጥ የመጠበቅ “ተከላካይነት” ሚናውን ሊወጣ ይገባል።

ሴት ልጅ በቤቷና በቤተሰቧ ዘንድ ያላትን የከበረን ቦታ (መቅደሷን) መልሶ ማክበርና ለልጆቿ የምትሰጠውን ትምህርት፣ ትውልድ በማነጽ ማኅበረሰቡን የምትገነባበትን ሥራ ማገዝ።

ትውልዱ ከትውልዱም በተለይ ሴቷ ከእናቷ እቅፍ ሳትወጣ የቤቷ(የቤተመቅደሷ) እመቤት (ካህን) መኾኗን ወዳና ፈቅዳ እንድትቀበለው፤ በዚያም ትውልዷን የማስቀጠሉን፣ የማነጹንና ትውፊቷን በማቀበሉ ሂደት ማኅበረሰቧን ከምክነት ትውልዷንም ከጥፋት እንድትታደግ ማበረታታት።

“እኩልነት” በሚል ስም ሴትን ከመቅደሷ ማስወጣት፣ እርሷንም ኾነ ትውልዷን ለባዕዳን አጥፊ ትርክት ማጋለጥ ነው። ማኅበረሰባችንን ከውድቀት ለመታደግ ቤተሰብንም ለማጽናት የአባወራውን ወደ ጠባቂነቱ ሚና መመለስ ብቸኛው መፍትሔ ነው!


Post a Comment

0 Comments