"ሀገር ማለት ሰው አይደለም'!


✍️ ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር 

የሰው ልጅ መገኛውንና መቆሚያውን ለይቶ ለማወቅ በሚያደርገው ረቂቅ የሕሊና ጉዞ ውስጥ፣ “ሀገር” የምትባለውን ግዙፍና ምስጢራዊ አካል ከራሱ ውስንነት ጋር አያይዞ የመተርጎም ልማድ አለው። ብዙዎች “ሀገር ማለት ሰው ነው” በሚል ስሜታዊ ብይን የሰውን ልጅ ክብር ከፍ ለማድረግ ቢሞክሩም፣ ይህ እይታ ግን የሀገርን ዘላለማዊነትና መለኮታዊ ግርማ ወደ ሟቹና አላፊው የሰው ልጅ ባሕርይ ዝቅ የሚያደርግ ጥልቀት የሌለው ፍልስፍና ነው። እውነተኛውና የማንጋፋው ሀቅ የሚነግረን ግን ሀገር ከሰው ልጅ እስትንፋስ ቀድማ የተገኘች፣ የሰው ልጅ የተበጀበት አፈርና መመለሻ ማሕፀን መሆኗን ነው።

​በመለኮታዊው ቃል “ትሁን” ተብላ የተፈጠረችው ምድር፣ የሰው ልጅ እንዲቆምባት የተዘረጋች ታላቅ መድረክ እንጂ በሰዎች ስብስብ የምትፈጠር ተራ ድርጅት አይደለችም። “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ተብሎ የተፈረደበት የሰው ልጅ፣ በምንም መመዘኛ የሀገር አምሳያ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ሀገር ማለት ያ የማይሞተው መለኮታዊ ቃል ያረፈባት፣ የሺህ ዓመታት ትውልድን አፈርነት በሆዷ የምታስተናግድና የሕይወትን ምስጢር ከምድር አፈር ጋር አዋህዳ የያዘች ረቂቅ ኃይል ናት። 

ይህ ፍልስፍና የሚጀምረው ከፍጥረት ተዋረድ ነው። ምድር በመለኮት ቃል ትዕዛዝ ካልሆነ ከምንም ተገኝታ ጸንታ ስትቆም፣ ሰው ግን የተበጀው ከዚሁ ከምድር አፈርና ከመለኮት እስትንፋስ ጥምረት ነው። ይህ ታላቅ እውነት የሚነግረን ሰው የሀገር ውጤት እንጂ ሀገር የሰው ውጤት እንዳልሆነች ነው። አፈር የሰው ልጅ ቁሳዊ ማንነት መሰረት እንደመሆኑ፣ ሀገር ማለት ያ የተባረከ አፈር፣ ያ የተቀደሰ መሬትና ያ መለኮታዊ ትእዛዝ ያረፈበት ስፍራ እንጂ ያ አፈር ለጊዜው ነፍስ ዘርቶ የሚንቀሳቀስበት "ሰው" አይደለም። 

ሰው ከሀገር አፈር ተበጅቶ፣ በሀገር አየር ተንፍሶ፣ በሀገር ውሃ ታጥቦና በሀገር በረከት አድጎ መልሶ ወደ ሀገር አፈርነት የሚቀየር "እንግዳ" ነው። ሀገር ግን ያንን ሁሉ የሰው ልጅ ዑደት የምታስተናግድ፣ የማይሞትና የማይለወጥ የታሪክ መዝገብ ናት። ሀገርን "ሰው ነው" ብሎ መበየን፣ ልክ አንድን ሸክላ "ሸክላ ሰሪው ነው" እንደማለት ይቆጠራል። ሸክላ ሰሪው በሸክላው ላይ አሻራውን ሊያሳርፍ ይችላል እንጂ ሸክላው ራሱ ሊሆን አይችልም።

​ሰው አላፊና ጠፊ ነው፤ ሀገር ግን ከመለኮታዊው ቃል ጋር የተቆራኘች፣ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ረቂቅ መንፈስ ያላት "ምድራዊት ሰማይ" ናት። የሰው ልጅ እትብት ከምድር ጋር መታሰሩ፣ ህልውናው ከእርሷ የተቆራኘ መሆኑን ለማሳየት እንጂ እርሷን ለመተካት አይደለም። እትብት የተመጋቢነትና የጥገኝነት ምልክት ነው። ፅንስ በማሕፀን ውስጥ እንዳለ ሁሉ፣ የሰው ልጅም በሀገር ማሕፀን ውስጥ ነው። ከምድሪቱ በሚገኝ ምግብ ይገነባል፣ በአየሯ ይተነፍሳል፣ በውሃዋ ይረካል። ይህ ሁሉ ጥገኝነት የሚያሳየው ሀገር "ሰጪ" ሰው ደግሞ "ተቀባይ" መሆኑን ነው። ሰጪና ተቀባይ ደግሞ አንድ ሊሆኑ አይችሉም። ሰው ወደ አፈር ሲመለስ ሀገር አትሞትም፤ ይልቁንም ያንን የሰው ልጅ ቅሪት ተቀብላ አዲስ ሕይወት የምታበቅልባት፣ ታሪክን የምታድስባትና መለኮታዊውን ዑደት የምታስቀጥልባት የማይጠፋ እቶን ናት።

​በመሆኑም ሀገርን በሰው ልጅ ሟችነትና አፈርነት መለካት ትልቅ ስህተት ነው። ሰው የሀገር ተገዢ እንጂ አምሳያ አይደለም። የሰው ልጅ ክብር የሚመነጨው ሀገር ከምትባለው ታላቅና ቅዱስ ስፍራ በተቆነጠረ አፈር በመፈጠሩና የመለኮት እስትንፋስ በማደሩ ብቻ ነው። ይህ እስትንፋስ ሲለይ ግን የቀረው አፈር ወደ ቀደመችው ሀገር እናቱ ይመለሳል። ሀገር ግን ያ የሰው ልጅ "አፈር ነኝ" የሚል ምስክርነት የታተመባት፣ በሺህ የሚቆጠሩ አፈር የሆኑ ትውልዶችን በሆዷ የያዘችና ገና ለሚመጡትም አፈር ለሚሆኑት መቆያ የምትሆን ሰፊና ጥልቅ ምስጢር ናት። 

ሀገር ማለት ሰው ሊሆን የማይችልበት ምክንያትም ይኸው ነው—ሰው ያልፋል፣ ሀገር ግን የአላፊዎች ሁሉ ማረፊያና የማይሞተው መለኮታዊ ቃል አሻራ ሆና ትቀጥላለች። 

ሀገር ማለት ሰው ሳይሆን፣ ሰው እንዲሆን የተፈቀደለት ቅዱስ አውድ ነው። ሰው በሀገር ውስጥ ሲኖር የራሱን ማንነት የሚያገኘው ከምድሪቱ ጋር ባለው ጥልቅ ቁርኝት ነው። ያ ምድር የሌለበት ሰው፣ መለኮታዊው አፈር የተነጠቀ ባዶ እስትንፋስ ብቻ ይሆናል። ሀገር ማለት ትላንት አባቶቻችን በደማቸው የቀደሱት፣ ዛሬ እኛ የምንረግጠውና ነገ ልጆቻችን የሚወርሱት የማይናወጥ ቃል-ኪዳን ነው። ይህ ቃል-ኪዳን ደግሞ ከግለሰቦች ፍላጎትና ከሕዝቦች ስብስብ በላይ የሆነ፣ የራሱ ህልውና ያለውና በራሱ የሚቆም መለኮታዊ ተቋም ነው። ሀገር በሰው ልብ ውስጥ ሳይሆን፣ ሰው በሀገር ሰፊ ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ የሚኖርባት፣ የመኖሩ ትርጉም የሚገኝባትና የሞቱ ክብር የሚረጋገጥባት የዘላለም ቤት ናት።

የዚህ ሙግት ማሳረጊያ የሚሆነው ታላቁ እውነት ሀገርን ከሰው ልጅ "ባለቤትነት" አውጥቶ ወደ "ምስክርነት" ከፍ ማድረግ ነው። ሀገር ማለት ሰው አይደለም ስል፣ ሰው በጊዜ ሂደት የሚለዋወጥ፣ የሚከዳና የሚጠፋ "ኩነት" ሲሆን፤ ሀገር ግን የማይለወጥና የማይታለል "ህሊና" በመሆኗ ነው። ሰው በምድሪቱ ላይ ሲመላለስ የራሱን ታሪክ የሚጽፍ ቢመስለውም፣ እውነታው ግን ምድሪቱ በሰውየው ላይ ታሪኳን መጻፏ ነው። "አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ" የሚለው ቃል የሰውን ልጅ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን የሀገርን ዘላለማዊ ድል የሚናገር ነው። ሰው ወደ አፈር ሲመለስ ሀገር አትሞትም፤ ይልቁንም ያ ሰው በምድሪቱ ላይ የኖረውን የጽድቅና የኃጢአት ታሪክ የሰማይ ብልጭታ እስኪያገኘው በአፈሯ ውስጥ አፍና ትይዛለች።

​በመሆኑም ሀገር ማለት በሰው ልጆች ስብስብ የምትፈጠር "ስምምነት" ሳትሆን፣ ሰዎችን ለፍርድና ለምስክርነት የምታበቃ "መለኮታዊ ሚዛን" ናት። የሰው ልጅ ከሀገር አፈር ተነስቶ ወደ ሀገር አፈር መመለሱ፣ ሀገር የሰው ልጅ የህልውና አልፋና ኦሜጋ (መጀመሪያና መጨረሻ) መሆኗን ያረጋግጣል። ሰው በሀገር ላይ የሚያሳርፈው የእግር ኮቴ ይጠፋል፤ ሀገር ግን ያንን ኮቴ ያሳረፈውን አፈር መልሳ በመዋጥ ማንነቱን ታከማቻለች። ስለዚህ ሀገር ማለት ሰው ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሰው ተመራማሪ ነው፣ ሀገር ግን ምርምር ናት፤ ሰው ተጓዥ ነው፣ ሀገር ግን መንገዱም መድረሻውም ናት። ሀገር የሰው ልጅ አፈርነት የሚከበርባት፣ መለኮታዊው እስትንፋስ ከሥጋ ሲለይ የቀረው ቁስ አካል በክብር የሚያርፍባት "የዝምታ ቤተ-መቅደስ" ናት።

​በአጭሩ፣ ሀገር ማለት ሰው ያልሆነችው ሰው ሊሆናት ከሚችለው በላይ ስለሆነች ነው። እርሷ የአላፊያን መጠለያና የዘላለማዊነት አምሳያ በመሆኗ፣ በሰው ልጅ ሟችነትና አፈርነት ውስጥ የማይገኝ "የማይናወጥ ቃል-ኪዳን" ሆና በቃሉ እንደ ተፈጠረች በቃሉ እስክ ትጠቀለል ትኖራለች።

Post a Comment

0 Comments