በጠሉት ራስ ምታቱን ይታገሷል!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ትውልዱ ተፈጥሮውን፣ እሴቱን ማንነቱን እንዲጠላ ሲደረግ ልቡ ጠፍቶ(ልብአልባ) ኾኖ፤ ምን ቢማር ራሱንም ኾነ ሀገሩን በማጥፋት ሲጠመድ አይድነቅ!

ይህ የኾነው ያለ ምክንያት አይደለም። ተፈጥሮአዊውን፣ የመጣበትን፣ የበዛበትን፣ የሰፋበትንና የጠነከረበት፣ በስብዕና የተገነባበትን አባታዊ ሥርዓት ኮንነውበት፣ በጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት ብሶትና ሮሮ ሲጋት የኖረ ትውልድ ራሱንም ኾነ ዘሩን አምክኖ ማጥፋቱ የሚጠበቅ ነው።

ማርክሳዊው የጨቋኝና የተጨቋኝ ትርክት መቼም ማቆሚያና መቋጫ የሌለው የብሶት ሰንሰሰለት፣ የጥፋት ሰደድ እሳት፣ ሀገር አፍኣሽም አውሎ ንፋስ ነው።

በዚህ መርዝ የተበከሉ ምዕራባውያን በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም ጠፍተዋል፤ ቤታቸው ባዶ ኾኗል፣ መንደራቸው በባዕዳን ተወሯል፣ ትውልዳቸውም መክኗል።

ይሁን እንጂ “ሀገሬን ተይ ስሚ፣ የአበራሽን ጠባሳ እዪ፣ ተይ ተመከሪ” ብላት እንቢ አለችኝ! የሌሎችን ውድቀት እያየች ነገር ግን “ሥልጣኔ ነው” እያለች ወደ መጥፊያዋ ገደል ትገሰግሳለች።

አንድ ሰው ራሱን ማንነቱን፣ ትውፊቱን፣ እሴቱን፣ እምነቱን፣ የመጣበቱን መንዱን ጠልቶ በተሰማራበት ባዕድ መንገድ ጥፋት ውድቀቱ ቢከተለው፣ ቢያሳድደውና ቢደፋው የኾነበትን ይቀበል።፡

እኛም የአባቶቻችንን አባወራነት፣ እምነትና እሴት እንደ “ኋላ ቀርነት” እንደ “አንባገነንነትም” ቆጥረን ጠላነው። በምትኩ በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ሰበብ የተከልነው የባዕዳን “ልብ-አልባ” የሚያደርገን፣ በእብሪት ታጅረንም የጠፋንበት እውቀት ግን ዛሬ ትዳርን እያፈረሰ፣ ቤተሰብን እየበተነ፣ ትውልድን እያጠፋ፣ ማኅበረሰብን እያመከነ ይገኛል።

🚨 ማን ይሰማ? ጆሮ ያለው!

🚨🚨 ማን ያስተውል? ልብ ያለው!

🚨🚨🚨 ከሁለቱም ያልኾነ ይለፈው!

ታዲያ አሁን ምን ብለው ስሞታ ያቀርባሉ! በጠሉት ራስ፣ ራስ ምታቱን ታግሰው ይቀመጧል እንጂ! የጥፋቱን መንገድ በፈቃዳቸው መርጠው፣ የጥፋቱን ውጤት ሲያዩ ማማረር፣ ማሃዘንና መነፋረቅ ትርጉም የለውም!

የገዛ ማንነቱን የናቀና የባዕድ አምላኪ የኾነ ትውልድ፣ የውድቀቱ መዘዝ ራሱ የናቀው ማንነቱ ያስከተለበት ቅጣት ነውና “እሰይ ይበለኝ!” ይበል።

ይህ መልእክት ለእውነት ምስክር እንዲሆን ተጻፈ። ተፈጥሮአዊውን ሥርዓት አፍርሰው፣ ትውልዱን ለባርነትና ለሞት ለሚያጣድፉ ሁሉ ማስጠንቀቂያ ነው።

ለእነርሱ ብቻ አይደለም! ምን እየተሠራ እንደኾነ እያወቁ በምንቸገረኝነትም ኾነ በግዴለሽነት በዝምታ ለተወዘቱ፣ ዝምታቸውን አጽድቀውም ለታጀሩቱ ጭምር ነው።

ነገ የጥፋቱ ማዕበል ሁሉንም ሲጠርግ “አላወቅንም” እንዳይሉ፣ ዛሬ የአባወራው ድምፅ እውነትን በግልጽ አስቀምጧል።

ከዚህ “ራስ ምታቱ” ለመዳን ብቸኛው መንገድ የጠላነውን ማንነት፦ ወንድነት፣ ሴትነት ተፈጥሮ ጸጋችንን፣መልሰን ሚና ግዴታችንን፤ ማክበርና ወደ ተፈጥሮአዊው አባታዊ ሥርዓት መመለስ ብቻ ነው።

ወንድምዓለም! ይህ የጥፋት ማዕበል መጀመሪያ የሚመታው ቤተሰብህን ነው። ስለዚህ፦

🌟 የአባቶቻችንን እሴት አታጥፋ! እምነትህ፣ ባህልህና ማንነትህ የማኅበረሰቡ መሠረት ናቸው። እነርሱን አጥብቀህ ያዝ!

🌟 ትውልድን አታምክን! ልጆችህ የአንተ ቀጣይነት ናቸው። ቤተሰብን በሚያፈርሱ የባዕዳን ትረካዎች አታፍርሳቸው።

🌟 ከፍርሃት ውጣ! ለጽድቅ የሚጨክን ልብና ለእውነት የሚቆም ወኔ ይኑርህ!

ከዚያ ውጪ በጥጋባችንም ቢሉ በእብሪታችን ወጥተን በኾነብን ጸጥ፣ ዋጥ፣ ስልቅጥ!

Post a Comment

0 Comments