እሴት-ክብሩን የጣለ፣ እምነቱ በአስመሳይነት የሸቀጠ፣ እውነቱን ማላገጫ ያደረገ ማኅበረሰብ፤ አስተምሮ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ባደረጋቸው አድርባይ ልጆቹ ለባርነት ቢሸጥ ቢለወጥ፤ አባወራነት ተከሶ ጃንደርባነትም ሲወደስ አይደነቅ!
ሲ.ኤስ. ሉዊስ The Abolition of Man በተሰኘው መጽሐፉ ላይ፦ “We laugh at honour, and are shocked to find traitors in our midst.” ይላል።
እኛ ግን ከዚያም አልፈናል፤ እሴታችንን ባረከስንበት አደባባይ፣ አድርባይነት እንደ ትልቅ ስኬት ሲቀደስና ሲወደስ ማየታችን የውድቀታችን ማህተም ነው።
የአባወራነትን ክብርና የቤተሰብን ቅዱስ ሥርዓት፣ ቅጡን ወጉን በ”ዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት” ስም ካረከስን፣ ካኮሰስንና ካንቋሸሽን በኋላ፣ ዛሬ በየመድረኩና በየመንበሩ “አድርባይነት” ነግሦ ስናይ መደንገጣችን ራስን ማታለል ነው።
ክብር (Honour) የአንድ ወንድ፣ በተለይም የአባወራው ትልቁ መከላከያ ጋሻ፣ መጠበቂያ ግንብ ነው። ይህ ጋሻ ሲወድቅ፣ ሲናቅና ሲቃለል ወንዱ ለሆዱ ያደረ፣ ለባዕዳን ትረካ የተመቸና ለጥቅም ሲል ማንነቱን የሚሸጥ “አድርባይ” ይኾናል።
አባትነትን “በዳይ” አድርገን ካሳነስን በኋላ፣ ልጆቻችን ለአባት የማይታዘዙና ለባዕዳን አጀንዳ አጎብዳጅ ሲሆኑ “ለምን?” ብለን መገረም የለብንም።
ያስከበረን፣ ማኅበረሰብ ተጠብቆበት የኖረን እሴታችንን በእግራችን ረግጠን ያስተማርናቸው ምሁራኑ የጠላት ቅጥረኛ ኾነው ሲገኙ ማየት የዘራነው ክህደት ፍሬ ማፍራቱ ነው።
ማኅበረሰቡ ራሱ እምነቱን በአስመሳይነት ሲሸቅጥ፤ ቤተሰብ የሚመሠረትበትን ትውልድ የሚታነጽበት አባወራነት እሴቱ ሲኮነን፣ እውነትን ደግሞ በፌዝና በማላገጫ ሲለውጣት፣ የፈጠረው ውጤት “አድርባይ ምንደኞችን” ነው።
እነዚህ አስተምሮና መርቆ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ያደረጋቸው ግለሰቦች፣ ዛሬ ትውልዱንና አገሩን ለባዕዳን መሰሪ ጽንሰሃሳብ ሲሸጡና ሲለውጡ ለምን ይደነቃል?
መሠረቱ የላላ፣ እሴቱን የጠላ ማኅበረሰብ፣ ትውልድ-ፍሬው የሚጸናበት፣ የሚታነጽበት፣ የሚበየንበትም ማንነት አጥቶ አድርባይ መኾኑ አይቀርም።
በራሱ ላይ ያልሠለጠነ፣ እሴቱን የናቀና ለዶላር ያደረ ምሁር፣ ሊቅ ሊቀ-ሊቃውንት “አርአያ” ተደርጎ ሲቀደስ፣ ሲወደስ ሲመላለስ፤ ውጤቱ በመካከላችን በክህደት የሚኖሩና የሀገርን የጀርባ አጥንት የሚሰብሩ ከዳተኞች ባንዳዎች መብዛት ነው።
እሴታችንን አርክሰን በአድርባይነት መብዛት ከመገረም የምንወጣው፣ ወደ ቀደመው የአባወራነት “የስልጠና” ሥርዓት ስንመለስ ብቻ ነው።
☀️ ወንዱ ሊሠራው ካለው ጽድቅ በፊት ራሱ ላይ እንዲሠለጥን፣
☀️ ክብር (Honour) ከቁሳዊ ጥቅም በላይ መኾኑን እንዲረዳ፣
☀️ የቤቱ፣ የቤተ-መንግሥቱ “መቅደስ ጠባቂ” እንጂ የባዕዳን አጀንዳ ተላላኪ፣ ሆድ አምላኪ እንዳይሆን ማስተማር ግድ ይለናል።
አጥሩን አፍርሰን ጅብ ገባ ብለን አንጩህ። ወንድነት መክሊቱን፣ አባወራነት ክብሩን በስብከትና በቅድመጋብቻ ትምህርት በሆዳደሮች አስመሳይ ነጋዴዎች እንዲጥል የተማረ የጣለ ማኅበረሰብ በምንደኞች ሲነገድበት መገረም የለበትም።
እሴታችንን ባረከስንበት አደባባይ አድርባይነት ሲቀደስ እያየን ዝምታን ከመረጥን፣ ከዳተኞች በመካከላችን መፈልፈላቸው፣ ትውልዳችን በባንዳነት መሰማራታቸው፣ ልጆቻችን የእናት ጡት ነካሽ መኾናቸው የማይቀረው የክህደታችን ውጤት ነው።
ትውልድን ጠባቂ ቀራጩ፣ መከታ አናጺው አባወራና ክብሩ ይመለሳል!
0 Comments