በውድቀቱ የሚሸቅልበት ይከርምበት!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ቁስል ሕመም ከመኾን ይልቅ የገቢ ምንጭ ሲኾን፤ ስብራት ጉዳት ከመኾን ይልቅ ራት ሲኾን፣ ዋይታ ሐዘን ከመኾን ይልቅ ሀብት ሲኾን ድኅነቱን የሚፈልጋት አይኖርም!

ዛሬ ዛሬ በዐዲስ አበባችን እንዲህ ኮሪደር ተነጥፎ ባለመኪናዎቹን እስክናስቀና፣ ከቤት ያሉትንም በጨለማ እስክናስወጣ ድረስ በሳይክልና በእግር ከመንፈላሰሳችን በፊት የነበሩ መንገዶቻችን ጠባብ ነበሩ።

ይህ ብቻም አይደለም! ታስታውሱ እንደኾነ በእነዚያው ጠባብ መንገዶች ላይ እንደዛሬው ታድነው ከመጥፋታቸው በፊት የሚሰቀጥጥ ትዕይንት “በኔቢጤዎች” ነበር፤ በተለይም በሥራ መውጪያና መግቢያ፣ ሕዝብ በሚበዛበቸው ቤተክርስትያንና ገበያ አካባቢ!

ለእነዚያ የእኔ ቢጤዎች ጉዳት ቁስላቸውን፣ ስብራት እንከናቸውን፣ እጦት ሕመማቸውን፣ ዋይታ ሐዘናቸውን ለመንገደኛው እስኪሰቀጥጠው፣ እንዲሰቀጥጠው ድረስ እያሳዩ ገንዘብ ይጠይቁበት ነበር።

በዚያም ጤነኛ ኾነው በቀን ገቢ ከሚሠሩት በእጅጉ መሰብሰብ ይቻላቸዋልና ድኅነት፣ ጤንነት ሰጥቶ ከገቢ ምንጫቸው የሚለያቸውን ከመፈለግ ይታቀባሉ፤ አንድም በድኅነት ደኅንነታቸው ተስፋ ቆርጠው ይቀራሉ!

ያኔ ያየነው ግለሰባዊ ውድቀት፣ ዛሬ በሰፋና በዘመነ መልኩ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችንና መገናኛ ብዙኃን ተሻግሯል። ውድቀትን እንደ ገቢ ማግኛ ምርት፣ ሕመምን እንደ ጥሪት የመቁጠር አባዜ ትውልዱን ወደ ጥፋት ጥልቁ እያሰጠመው ይገኛል።

ለእነዚያ “የኔቢጤዎች” ቁስላቸው ሕመም ሳይኾን “ማስታወቂያ” ነበር። ስብራታቸው ጉዳት ሳይኾን ወደ ጥሬ ብር የሚቀይሩት “ጥሪት” ነበር። በእርግጥ መንገደኛው እስኪሰቀጥጠው ድረስ እንከናቸውን የሚያሳዩት፣ ጉዳታቸውን ሸጠው የዕለት ገቢ ለማግኘት ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ ትልቅ ሥነ-ልቦናዊ አደጋ አለ፦ ገቢ የሚያስገኝ ቁስል እንዲድን አይፈለግም። በቀን ሥራ ገቢ የሚያገኙት ጤነኞች በላይ ገንዘብ የሚያስገኝ ሕመም፣ ባለቤቱን ከፈውስ ይልቅ ከሕመሙ ጋር እንዲወዳጅ፣ እንዲከርም ያደርገዋል።

ጤንነቱም ከገቢ ምንጩ የሚለየው ጠላት ኾኖ ይታየዋል። ይህ “በውድቀት የመሸቀል” አባዜ፣ ድኅነትን እንደ ቋሚ ማንነት አጽድቆ፣ “የግዴታ ውዴታም” አድርጎ ያስቀራል።

ዛሬ ደግሞ ቁስላችንን አደባባይ አውጥተን የምንነፋረቅበት “ዲጂታል መንደር” ተፈጥሯል። በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ገጾች ላይ ወጥቶ ማላዘን፣ ይበልጥ አዝኖና አሳዝኖ ታይታንና ገንዘብን መሰብሰብ ትልቅ ሥራ ሆኗል።

ታይታ፣ ይኹንታና “አይዞህ” የሚል ስጦታ በምናገኝበት፤ ከውድቀቱ ለመውጣት ከመጣር ይልቅ ውድቀቱን ተንከባክበን በእርሱ ተወስነን እንኖራለን።

👉 “ወድጄ እኮ አይደለም! ተገፍቼ፣ ተሰድጄ፣ ተፈትቼ፣ ተጎድቼ ነው፣ እዩኝ፤ አላሳዝንም ወይ! እዬዬዬ!”

ጉዳትን ይዞ መነገድ ለጊዜው ገንዘብ ሊያስገኝ ይችላል፤ እንደ ግለሰብ ግን ለከፋ የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ እንደ ማኅበረሰብም ለታላቅ ማኅበራዊ ውድቀት ይዳርጋል።

👉 “እኛ የተገፋን፣ የተደፋን ለዘመናት የተረገጥን የተጨቆንን፣ የተገለልን...የሙት ልጆች ነን”

ጉዳት መገፋት፣ ቁስለት ደግሞ መታመም መኾኑ ቀርቶ “ራት” ሲኾን፣ ሰውነታችን ይከስማል። በሐዘን ተነፋርቀን በሰበሰብነው ገንዘብና ታይታ ልክ፣ ክብራችንና የማገገም አቅማችን ይሞታል።

ማኅበረሰቡም በሥራና በጥረት፣ በሥልጣኔና በእድገት ከሚገኝ ብልጽግናና ስኬት ይልቅ፣ በለቅሶና በዋይታ የሚገኝ “ቸርነትን” ወይም “በረከት” እንደ አማራጭ እንዲያይ ይገፋፋል።

ወንድምዓለም! ውድቀትህን አትሸጠው፤ ቁስልህን የገቢ ምንጭ አታድርገው፣ እጦትህን ገበያ አታውጣው፣ ስብራትህንም አትውደደው።

🌟🌟🌟 የአንድ ወቅት ሕመምህ ሊታከም የሚገባው እንጂ፣ የምትኖርበት፣ የምትሰነብትበት፣ የምትከርምበት የሚከፋው ደግሞ የምትታወቅበትና የምትታወስበት፣ የምታወርሰውም ቤት ሊኾን አይገባም።

በውድቀቱ የሚሸቅል፣ ውድቀቱ የዘላለም ቤቱ ኾኖ እርሱም ምን ሀብትና ሥልጣን ቢጨብጥ ለከፋ የሥነ-ልቦና ውድቀት ተላለፎ ይቀራል።

ከታይታና ይኹንታ፣ ከእላቂ ጨርቅና ከስባሪ ሳንቲም ይልቅ፣ የሰውነትህን ድኅነትንና ክብርን አስቀድም! የአንድ ሰሞን ቁስልህን እንዲድን ሳይኾን እንዲታይና ጥቅም እንዲያስገኝ የምትከባከበው ከኾነ፣ መቼም ቢኾን አትፈወስም!

ይልቁንስ እርሱን በሚያስከነዳና በሚያስረሳ፣ በሚጋርድም ጠንካራ ስብዕናና ጥረት ጽድቅን መፈጸም ወደሚችል ማንነት ራስክን አንሳ ስቀልም እንጂ!

ይህ አባወራነት ነው!💪

Post a Comment

0 Comments