✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ከፈሩበት ማማ፣ ከሚንቀጠቀጡበት ቆጥ ላይ በስጋት ሰፍረው ትውልድን አይታደጉም! ይልቁንስ ጽድቅ ይፈጽሙበት በተሰጠው ጸጋ ሠልጥነው፣ በሚናው በልበሙሉነት ቆመው እንጂ!
የአባወራ ንቅናቄ “ደስ ሲል፣ ሲመቸኝ” ብለው የሚሰለፉበት የትርፍ ጊዜ መዝናኛ አይደለም! አንድም ደግሞ “እንዲህ ኾንን፣ ልንኾን ነው፣ ሊኾንብን ነው፣ ኾነብን፣ ሳይኾንብን አይቀርም፣ ቢኾንብንስ፣ ኾኖብን ቢኾንስ...” ሲሉ ከሸቃላ ዩቲዩበርና ቲክታከር ጋር በማላዘን፣ በመነፋረቅና በመንቀጥቀጥ የሚማገዱበት የሰለባዎች መድረክ አይደለም።
ይህ ንቅናቄ ከፍርሃት ማማ ላይ ኾነው “ወዮልን” የሚሉበት ሳይኾን፣ በቁርጥ ሕሊና፣ ለጽድቅ በሠለጠነ እና በጨከነ ልቦና፣ በማይደፈርና በማይካድ ጽኑዕ ስብዕና የሚዘምቱበት የሕይወት ዘመቻ ነው!
ትውልድን መታደግ የሚቻለው በልመናና በልቅሶ፣ በማላዘንና በመነፋረቅ አይደለም! ዛሬ በየማኅበራዊ ሚዲያውና በየመድረኩ የሚሰማው የ”ምስኪንነት” ስብከት ትውልዱን ለባርነት የሚያዘጋጀው ነው።
የአባወራ ንቅናቄ ግን ይህንን አልጮችን “በብዛትና በጥራት የሚየሠፈራ” አልጫነት አጥብቆ ይጸየፋል፤ ይቃወማልም! አባወራነት በተሰጠው ጸጋ ሠልጥኖ፣ በቤቱና በሀገሩ ላይ በልበሙሉነት ቆሞ ጽድቅን የመፈጸም ግዴታ ነው።
ፍርሃት በነገሠበት ቆጥ ላይ ተቀምጦ “ወየው! ወቸው” ማለት ራስን ማታለል ነው፤ ትውልድን ለመታደግ መጀመሪያ ከፈሩበት ማማ ወርዶ በቆራጥነት መቆም ይገባል!
በአባቶቻችን መንገድ ሄደን ትውልድ ቀድሞ የታነጸበትን የጀግንነትና የጽናት መሠረት ዳግም እንገነባለን። ዛሬ ዛሬ በአፍጢማቸው በተደፉ፣ ለጥቂት ምንዳ በታወሩ ሆዳደር ሊቃውንት ስብከት የጠፋውን እምነት፣ የረከሰውን እሴትና የተሰረዘውን እውነት ዳግም እናንጸዋለን!
ሊቃውንቱ የፈሩትን እውነት እኛ እንናገራለን፤ እነርሱ የማይጠቅም፣ የማይረባ፣ በባርነትም የሚያሳድር ሲሉ የሸጡትን እሴት እኛ ለዚሁ የጽድቅ ዘመቻ ባሠለጥንነውና በሠለጠንንበት የአባታችን ጸጋ እንመልሰዋለን።
ይህ ንቅናቄ ለአልጮች ቦታ የለውም! ለጽድቅ የሚጨክን፣ ለሐቅ የሚዋደቅና ለቤተሰቡ፣ ለማኅበረሰቡ ክብር እሴት የማይደራደር አባወራ ብቻ የሚቆምበት ግንባር ነው።
እርሱም እውነተኛ ስጦታውን የታጠቀና የሠለጠነበትም መኾኑን ለዐለም እናሳያለን። አባቶቻችን ለልጅ ልጆቻቸው ባርነትን ላለማውረስ በጨከነ ልቦና እንደዘመቱ፣ እኛም አድዋን በምንዘክርበት ሰሞን፤
ዛሬ በመብትና በነፃነት ስም የመጣውን የትውልድ ጥፋት የማኅበረሰብ ምክነትን ለመመከት፦
💪 በቁርጥ ሕሊና፣
💪 ለጽድቅ በሠለጠነ እና በጨከነ ልቦና፣
💪 በማይደፈርና በማይካድ ጽኑዕ ስብዕናም እንነሳለን!
አነተስ! አለህ ግን?
0 Comments