✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
አባትን ከቤቱ ራስነት፣ ከልጆቹ ጠባቂነት፣ ከሥርዓትና ቅጥ አስተማሪነት፣ ከልባምና ልበሙሉነት ተምሳሌትነቱ በጨቋኝነት ስም አባሮ፤ ትውልዱ ሲጠፋ “እንታደገው” ብሎ መዳከር አለማወቅ ሳይኾን ኾን ተብሎ የሚፈጸም የጠላትና የምንደኞች ሸፍጥ ነው!
ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ፈተና የድህነት ሳይኾን የሸፍጥ ነው፤ የድንቁርና ሳይኾን የክህደት ነው። ይህም ሆዳደሮችና ጠላት የተስማሙበት ነው!
እነርሱ ትውልዱን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት የተስማሙበት፣ የተቀጠሩበት መንገዱ አባወራውን ከቤት አብሮ፣ ትውልዱን ወደ ጠላት ጎሬ አባሮ፣ አልጨው በባርነት እንዲጋዙ ማድረግ ነው።
የሕይወት ክህሎት ትምህርቱ (SRHR) ሥልጠናው ይህንኑ የሚያሳይ ነው። ሥነ-ምግባርና ንጽሕናን ከልጆቹ የሚፈልገውን፣ ለልጆቹ ሕይወት ራሱን የሰዋውን አባት “አንባገነን፣ በዳይና ጨቋኝ” ብለው ከቤቱ አሳደው ሲያበቁ፣ መልሰው “ልጆቹን የሕይወት ክህሎት እናስተምራችሁ” እያሉ መምጣታቸው ሰዶ ማሳደድ ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል?
የሚወዳቸው፣ የሚወልዳቸውና የሚያንጻቸው አባት የሕይወት ልምዱን እንዳያካፍላቸው፣ የአባታቸው ምክር “ጭቆና” መስሎ እንዲታያቸው በልጆቹ ልብ ውስጥ ጥላቻን ስለው ሲያበቁ፤
በምትኩ “በግብረሰናይ” ተቋማት NGOዎች በኩል “የሕይወት ክህሎት” (Life Skills) ብለው መርዝ ይግቷቸዋል። የአባት ምክርና ተግሳጽ የሌለው ትውልድ ደግሞ ለጠላት የባርነት ግዞት የተመቸ “አልጫ” ነው።
ያለ ወላጅ ፈቃድና እውቅና፣ ከሃይማኖትና ከባህል አጥር ውጪ የሚሰጠው ይህ የሥነ-ተዋልዶ ጤና (SRHR) ትምህርት ስሙን ቀይሮ የመጣው የትውልድ ማምከኛ ነው።
አባት ልጁን ከውርደትና ከልቅነት ሲጠብቅ “ኋላቀር ባህል፣ አንባገነን እሴት፣ መብት ረጋጭ ሥርዓት” ይሉታል፤ NGOዎቹ ግን ልጆች ያለ ወላጅ ቁጥጥር ስለ ልቅ ወሲብ፣ እርግዝና እንዳይፈጠርም ስለ ወሊድ መከላከያ፣ ስለ ውርጃና ስለ ልቅነት ሲማሩ “የሕይወት ክህሎት” ይሉታል።
ይህ መርዛማ ትምህርት ትውልዱን በስብዕናው እንዲከሳ፣ ማንነቱን እንዲረሳና ለባዕዳን አጀንዳ የሚመች ስልብ እንዲኾን የሚያደርግ ነው።
አባትን አርክሶ፣ የአባወኣውን ግርማ አኮስሶ፣ በ NGOዎች ክህሎት የሚመራ ትውልድ አባወራ ሳይኾን የባዕዳን “መሣሪያ፣ ዘር አልባ ጃንደርባም ይኾናል።
🌟 ለዚህ ሁሉ ጥፋት ግንባር ቀደሞቹ በዶላር የተገዙት የራሳችን “ሊቃውንት” ናቸው። እነዚህ ምሁራን አባታዊውን ሥርዓት በማፍረስ ሂደት መርጃና መራጃ ኾነው ያገለግላሉ።
እንዳትሞግቷቸው የተማሩ፣ እንዳትወቅሷቸው በሕግ ማዕቀፍ የተከለሉ ኾነው እነርሱ በከፈቱት “የግብረሰናይ ተቋም (ግብር የማይከፍል ሱቅ) ትውልዱን በጅምላና በችርቻሮ ለጠላት ይሸጡታል።
አባት “አይኾንም” የሚለው ከጥፋት ሊታደገን መኾኑን እያወቁ፣ አባወራዊውን ሥርዓት “አባታዊ ጭቆና” እያሉ በወጣቱ ልብ ውስጥ ጥላቻ ይዘራሉ፤
ቤተሰብ ሲበተንና ልጆች አባት አልባ ሲሆኑ የሚደርሰውን ማኅበረሰባዊ ኪሳራ መመርመር ሳያቅታቸው፣ እርሱኑ ለጠላት ሪፖርት እያቀረቡ በትውልዱ ላይ ይነግዳሉ።
አባትን “ጨቋኝ” ብለው ከትውልዱ ልብ ካወጡት፣ ነገ ከጠላት ተኩላ የሚከላከለው ጋሻ አይኖረውም። ልቡንም አባቶቹ በመጡበት፣ ሰውነቱ በሚበየንበት እውነት የሚያንጽለት አያገኝምና ለእነዚሁ “ባለሱቆች” “የጥፋት ሸቀጥ” ማራገፊያ ይኾናል።
የSRHR ትምህርት ምንም እንኳ የሕይወት ክህሎት ትምህርት ቢባልም ቅሉ ትውልዱ ግን በእርሱ ራሱ ስሜቱ ላይ ሠልጥኖ ለጽድቅና ለፍትሕ አይቆምበትም።
ከዚያ ይልቅ ምን ቢማርና ማስትሬትና ዶክትሬት ቢኖረው በአጉል “ትምህርት” ልቡን ማጣት፣ በልቅነት መዳራት፣ ከትዳር ውጪ ልጆችን ማምጣት፣ ባይፈለጉም በመርዝና በመቀስ በጣጥሶ ማውጣት እንደሚቻል ይህም “ሰብአዊ መብት (Human Right)” እንደኾነ ይማርበታል እንጂ።
0 Comments