✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
በ"ኪነ-ጥበብ" ስም ልቡ የጠፋውን ትውልድ አማናዊው ከያኒ፣ የሰማይ አባቱ ወደ ልቡ ይመልሰው እንጂ ከሚጠፋበት "ጥበቡ" "ልታደግህ" የሚለው ሁሉ ጥበብን ያልተረዳ "መሃይም" ይመስለዋል።
ዘመናዊው “ኪነጥበብ” በሀገራችን “አብቦ ያፈራበት” ወቅትና በዘመናዊነት ሰበብ በራስ ጠልነት ተጠርንፈው በታሰሩት ልባልባዎች “ለጭቁኑ ማኅበረሰብ” የመጣው ማርክሳዊነት የደረሰበት ወቅት አንድ ኾነ!
በራስ-ጠልነት የተለከፉና በምዕራባውያን አስተሳሰብ የተጠመቁ “ሊቃውንት”፣ ኪነ-ጥበብን የእውነትና የውበት መግለጫ ማድረጉን ትተው የርዕዮተ-ዓለም ማስፈጸሚያ አደረጉት። በዚህም ኪነ-ጥበብ ትውልድን የሚያንጽ ሳይኾን፣ ልቡን የሚያጠፋና ከማንነቱ የሚያፋታ መርዝ ኾነ።
በዚያም ኪነ-ጥበብ መልካም፣ ልክ፣ ተገቢና ውቡ አልተገለጠበትም ይልቁንስ የሰውን ልብ የሚጠፋበት መሣሪያ ኾኖ አገለገለ።
የዘመኑ ኪነ-ጥበብ በተለይም በዜማና በግጥም ወንዶችን የሰለበበት መንገድ እጅግ ረቂቅ ነው። “አርቲስት” ተብዬዎቹ በፈጠሩት ትርክት፣ ወንድ ልጅ ለሴት ልጅ የሚገዛ፣ ለፍቅር ሲል ክብሩን የሚያርድና ማንነቱን አሳልፎ የሚሰጥ “ስሜታዊ ባሪያ” እንዲሆን ተሰብኳል።
“አንቺ ከሌለሽ እሞታለሁ፣ ያላንቺ መኖር አልችልም” የሚሉ የሽንፈት ዜማዎች፣ የወንድ ልጅን አባወራነትና መሪነት ወኔውንም ሲሰልቡት ኖረዋል።
ወንዱ የቤተሰብ ጠባቂና የሀገር ምሰሶ መሆኑ ቀርቶ፣ የሴት ውበት አምላኪና ለስሜቱ ተገዥ እንዲኾን በ”ጥበብ” ስም ተደግሶለታል።
ይህም ወንድነቱን አምክኖት በግርማ ፈንታ ምስኪንነትን፣ በጽናት ፈንታ ልምሾነትን እንዲላበስ ተደርጎ በአልኮል ናላው እየዞረ፣ በዘፈን ልቡን እያናወዘ የሚያላዝን ከንቱ ተደርጓል።
በሌላ በኩል፣ ኪነ-ጥበቡ ሴቶችን ከአባታቸውና ከባላቸው እቅፍ ለማውጣት “መብትና ነፃነት” የሚሉ ማራኪ ቃላትን ተጠቅሟል። በልብወለድ ድርሰቶችና በፊልሞች፣ ትዳር እንደ እስር ቤት፣ ቤተሰብ ደግሞ እንደ ጭቆና ተቋም ተደርጎ ተስሏል።
ሴቶች “ራሳቸውን እንዲችሉ” በሚል ሰበብ ከጥበቃ ማማቸው (ከቤታቸው) እንዲወጡና “በኪነ-ጥበብ” ስም በብቸኝነት ጎዳና ላይ እንዲወድቁ ተገፋፉ።
ውጤቱም ከትዳር ርቀውና ቀርተው የማንም ሳይኾኑ፣ የትም ከማንም ወድቀው በብቸኝነት እንዲማቅቁ ለጠላት ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችን ማፍራት ኾነ።
🚨 ይህ “ኪነ-ጥበብ” ሴቷን ለክብሯ ሳይኾን ለገበያና ለፖለቲካ ትርፍ፣ በመብትና በነፃነት ስም የማንም መጫወቻ አድርጎ አሳልፎ የሰጠ የሸፍጥ መሣሪያ ነው።
ዛሬ “አርቲስት” የምንላቸው ብዙዎቹ፣ ትውልዱን ወደ ጥልቁ የጥፋት አዘቅት የሚመሩ የጥፋት መለከት የሚነፉ ኾነዋል።
እነርሱ የሚዘፍኑት “ፍቅርን ነው” ቢሉንም፣ ሕይወታቸው ግን በፍጡር አምልኮና በዝሙት የተሞላ ነው። እነርሱ ስለ “ነፃነት” ቢሰብኩም፣ ራሳቸው ግን ለጥፋት አጀንዳ ባሪያዎች ናቸው።
ትውልዱ በእነዚህ አስመሳዮች ልቡ ስለጠፋ፣ እውነተኛውን የጥበብ ምንጭ(አምላካችንን) እና የአባቶቹን እሴት መለየት ተስኖታል።
🌟 ታናሼ! ጆሮህ የሚሰማውንና ዓይንህ የሚያየውን ጥበብ መርምር። የልጆችህን ልብ የሚሰልብ ዜማና ድርሰት ከቤትህ አስወጣ፤ አርቅ። ጉዳት ጥፋቱንም አውቀህ አሳውቃቸው!
እውነተኛው ኪነ-ጥበብ፦
🎯 እውነት ተፈጥሮን የሚገልጥ፣
🎯 እምነት በኃይልና ራስን በመግዛት የሚገለጥ፣
🎯 ወንድን በአባወራነት ግርማ የሚያጸና፣
🎯 ሴትን ደግሞ በክብሯና በጥበቃ ማማዋ የሚያኖር፣
🎯 ከአባታችን የተማርነው፣ አባቶቻችንም የኖሩበት፣ ትውልድም የታነጸበት መኾኑን አረጋግጥ!
0 Comments