✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ብሶትን እየተጋተ ላደገው፤ አባወራው ያልበዘበዘው፣ ያልጨቆነው ማንም የለም! ብሶት ቁርስ ራቱ፣ ትራስ ልብሱ፣ መጠጥ ጉርሱ ለኾነለት ሁሉ፦ አየር ንብረትም በአባወራው ተበድሏል እንጂ!
ትውልድ የመጣበትን እሴት በተለይም ተፈጥሮአዊውንና መጽሐፋዊውን አባታዊ ሥርዓት ለማጥፋት የሚፈልጉቱ አባወራውን በዝባዥ፣ ጨቋኝ፣ በዳይ ብለው መክሰስ ዋናው ተልዕኳቸው ነው።
እነርሱ በትውልዱ ልብ ውስጥ የአባትነትን ክብር ለመናድና መጽሐፋዊውን ሥርዓት ለማጥፋት የሚላኩ የ”ጥናት” ወረቀቶች ዛሬ ቤታችንን እያንኳኩ ነው።
አባወራውን “በዝባዥና ግፈኛ” አድርጎ መሳል ዋና ተልዕኳቸው ያደረጉት እንደ አክት አልያንስ (ACT Alliance) ያሉ “ለጋሽ” ተቋማት፣ ተፈጥሮአዊውን የአየር ንብረት መዛባት እንኳ ከአባወራው “አንባገነንነት” ጋር አቆላልፈው የጥላቻ መርዝ ይረጫሉ።
እነዚህ አካላት Gender Justice እና Climate Justice የሚሉትን “የብሶት ሐረጋት” እንደ ጦር መሣሪያ ይጠቀማሉ። ትውልዱ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ወላጅ አባቱን እንዲጠላ፣ ወንድነትን በዚያም አባትነትን፣ የሰማይ አባቱንም እንዲጠላ፣ እሴቱን እንዲንቅና የራሱን ተፈጥሮ እንዲጠየፍ ለማድረግ አየር ንብረትን ሰበብ ያደርጋሉ።
“ኢትዮጵያ የአባታዊ ሥርዓት (Patriarchal society) ሰለባ ናት... የአየር ንብረት ቀውስና የሥርዓተ-ጾታ ፍትሕ በእርግጥም የማይነጣጠሉ ናቸው” ይላሉ።
ይህ ለሆዱ ያደረና ብሶትን ቁርስ ራቱ ላደረገ ትውልድ የሚሰጥ መርዘኛ ስብከት ነው። ዓላማው አባወራው ለቤተሰቡ የሚከፍለውን ዋጋ ከምንም ሳይቆጥሩ፣ ሴቶችንና ልጃገረዶችን “ለዘላለም የተበደሉ” አድርጎ በመሳል በቤተሰብ ውስጥ የጥላቻ ግንብ መገንባት ነው።
እውቀት እያላቸው ለጽድቅ የሚጨክን ልብ ያጡት እነዚህ ልሂቃንና ሊቃውንት፣ ከባዕዳን የተላከላቸውን አጀንዳ ለሕዝቡ “እንተርጉምላችሁ” ይላሉ።
“እኛ ወንድ የበላይ የኾነበት፣ አባወራዊ ሥርዓትን በሚከተል ማኅበረሰብ ውስጥ እንኖራለን፤ ሰዎች ‘የችግሮቻቸው ዋነኛ ምንጭ የኾነውን’ እነዚህን ጉዳዮች አይረዱም” የሚለው “ምሁራዉ ትንታኔያቸው”፣ አባወራውን እንደ አላዋቂና እንደ የጭካኔ ተምሳሌት የመቁጠር ትዕቢት ነው።
እነዚህ ልብአልባ ሰዎች የኾኑ ሊቃውንት፣ የአየር ንብረት ለውጥን እንኳ “የአባወራ ግፍ” አድርገው በማቅረብ፣ ትውልዱንም በመጋት፦ ለሀገሪቱ መፍረስና ለማኅበረሰቡ መምከን ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳሉ።
ይኹን እንጂ ይህ በ”መብትና ነፃነት” ስም የሚነገድ፣ ልጆቻችንን በጥላቻ ለጥፋት የሚማግድ፣ ማኅበረሰባችንን አምክኖ የሚንድ የብሶት ትርክት፣ እውነትና እምነትን በልቡ በያዘው፣ እሴትንም በእጁ በጨበጠው በአባወራው ንቅናቄ ይገለበጣል።
አባወራነት የጭቆና መዋቅር ሳይኾን፣ ራስን አሳልፎ የመስጠትና የመስዋዕትነት መሠረት መኾኑን ዳግም እናጸናለን።
አየር ንብረትን የፖለቲካ መሸቀጫና የጥላቻ ማሳለጫ የሚያደርጉትን NGOዎች ሸፍጥ እናጋልጣለን። በተለይም ደግሞ ከኢኦተቤ የልማት ክንፍ ጋር በትብብር የሚሠራው ይህን የአየር ንብረት ለውጥ የጾታ እኩልነትና ፍትሕ ማጣት እንደኾነ በቀዳሚነት በሀገራችን የሚሠራውን የACT Alliance ሸፍጥ ጭምር።
አባታዊው ሥርዓት ሲቃጠል ዐለም እፎይ ትላለች
when patriarchy burns-the planet breathes
እንዲል የOxfam መፈክር
ወንድምዓለም! አየር ንብረትም ሆነ ማንኛውም ዓለም አቀፋዊ ቀውስ አባወራውን ለመክሰሻነት እየዋለ ነው። ዋናው የጠላት አጀንዳ ትውልዱን በተለይም ወጣቱን፣ ይበልጡንም ሴቷን በአባትነት በወንድነትም ላይ ጥላቻ እንዲያድርባት ማድረግ ነው።
በዚያም ያለ ጠባቂና መከታ ሲያገኟት በእርሷ በኩል አድርገው ትውልዷን በባርነት ለመንዳት ካልኾነም ለማጥፋት ይመቻቸው ዘንድ።
እንዲህ ያለ ብሶትን እየተጋተ ያደገ ትውልድ ደግሞ መጨረሻው መጥፋት ነው፤ እኛ ግን በእውነት የታነጸ፣ አባቱንና እሴቱን የሚያከብር ልባም ትውልድ እንገነባለን።
0 Comments