✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
እውነት በኾነው ወንድነት፣ እምነትን፣ እሴትንም በያዘው አባወራነት ለማደግ ዋጋ መክፈሉን የሰሰቱት አስመሳይ አድርባዮች፤ ውሸት ደግሳ በዘረጋችው ማዕድ ላይ አሳላፊ ኾነው ይሰየማሉና ተጠንቀቋቸው!
ከመሪና ከእውነት ዕጥረት ይልቅ፣ በእውነት ስም የሚነግዱ አስመሳዮች መብዛት ትውልዱን ለከፋ አደጋ አጋልጦታል። “የበግ ለምድ ለብሰው ይመጣሉ” እንደሚለው፣ እነዚህ ግለሰቦች የወንድነትን ግርማ፣ የአባወራነትን ኃላፊነትና የእምነትን ቅድስና እንደ ጭንብል በመጠቀም በማይኖሩት አውሬተው ለመጠቀም የገዛ ፍላጎታቸውን ያሳድዱበታል።
ለእውነት መቆም፣ በእውነት መኖር ዋጋ ያስከፍላል፤ እነርሱ ግን ያንን ዋጋ መክፈል አይፈልጉም። ይልቁንስ ውሸት ባዘጋጀችው ማዕድ ላይ ተቀምጠው፣ ትውልዱን ባስመሳይነት ያታልላሉ።
እውነተኛ ወንድነትና አባወራነት በትጋት፣ በጽናት፣ በራስ ላይ በሥልጣኔ፣ በመሥዋዕትነትና በእምነት የሚገነባ ልዕልና ነው። ይህ ማንነት የሚጸናው በመከራና በፈተና ውስጥ አልፎ ነው። እነዚህ አስመሳዮች ግን ይህንን የመከራ መንገድ አይፈልጉትም።
በቀላሉ የሚገኝ ዝና፣ ታይታና ይኹንታ፣ ሥልጣንና ጥቅሙም ያማልላቸዋል። የሚያውቁትን በተለይም የሚኖሩትን እውነት ብቻ መመስከርና ማለፍ ሲገባቸው፣ ውሸት የዘረጋችውን የአስመሳዮች ማዕድ ለማድመቅ ይመርጣሉ። በዚያ ማዕድ ላይ እነርሱ የመከራ ተካፋይ ሳይኾኑ፣ የውሸት “አሳላፊዎችና” አስፈጻሚዎች ኾነው በታይታና ዝናው ቀብጠው ይሰየማሉ።
የእነዚህ ሰዎች ትልቁ አደጋ የማይኖሩትን እውነት መስበካቸው ነው። በቃላቸው ስለ ጽናት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ እምነትና ስለ ሀገር ክብር ያወራሉ፤ በተግባራቸው ግን የገዛ ሆዳቸውንና ስማቸውን ብቻ ያመልካሉ።
ለትውልዱ “እውነት ይህ ነው” ብለው የሚያሳዩት፣ እነርሱ ራሳቸው በመከራ ውስጥ ያልፈተኑበትን፣ ከባዕዳን ፍልስፍና በተጨለፈ ትርክት የጠገኑትን “ሐሰት” ነው። እነርሱ እውነተኛ ወንድነትንና አባወራነትን አያውቁትም፤ ምክንያቱም ዋጋ አልከፈሉበትምና፣ አይከፍሉበትምና ሊከፍሉበትም አይፈልጉምና። “ዋጋ ያልተከፈለበት እውነት” ደግሞ ፍሬ እንደማታፈራዋ፣ ገበሬዋን ተስፋ እንደምታስቆርጠዋ የበለስ ዛፍ ያለ ነው።
ይኹን እንጂ እነዚህን ሰዎች ዐለም ትውልዱን በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም ደልላና አታላ ታጠፋበት ዘንድ ምሳቸው የኾነ ታይታና ይዉንታ የሚያገኙበትን መድረክ እየሰጠች መልዕክታቸውን ታሰራጫለች።
ለእነዚህ ግለሰቦች ለእውነት መቆም ሞኝነት ነው፦ ኧረ! ዝምብለህ ሰው እንደሚኖረው ኑር፣ አንተ አርፈህ ልጆችህን አታሳድግም እንዴ፣ ምን አንተ የለየህ ነህ እንዴ፣ ምንም አታመጣም፤ ደግሞካፋቸው የሚለይ መጽናኛቸው ነው።
በጠንካራ የአባወራው ስብዕና ባልታነጹት በእነርሱ ዘንድ አድርባይነትና አስመሳይነት እንደ “ጥበብና ብልሃት” ይቆጠራል። በማንኛውም ሥርዓትና አጀንዳ ሥር ራሳቸውን በማመቻቸት፣ በአዋቂነት በመሰለፍ፣ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚሮጡ “እንከፍ” ናቸው።
ተፈጥሯዊ እውነት፣ እምነትና እሴት የኾነ ጽድቅ መፈጸሚያ የወንድነት ወኔአቸውን ለአድርባይነት አሳልፈው ሰጥተዋል። ለቤተሰባቸውና ለማኅበረሰቡ መቆሚያ፣ መደገፊያ፣ መጠለያም መኾን ሲገባቸው፣ ራሳቸው ያልቻሉ ደካሞች ኾነው መጠለያ ፍለጋ ከወደቁት የባዕዳን ፍልስፍናዎች ሥር ይደበቃሉ።
ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው፣ ይህ አስመሳይነታቸውና አድርባይነታቸው፣ ታይታና ተቀባይነትን ካፈራው ምስኪንነታቸው ጋር አብሮ ትውልዱን ወደ ጥፋት እየመራው መኾኑ ነው።
ትውልዱ እውነተኛ የእምነትና የእሴት ባለቤት የኾኑ አባቶችንና መሪዎችን መመልከት ሲገባው፣ የሚያየው እነዚህን በውሸት ማዕድ ላይ የተሰየሙትን አስመሳይ አድርባዮችን ነው።
የእነርሱን ሐሰተኛ “እውነት” በመስማት፣ ወንድነቱ፣ አባወራነቱና እምነቱ ይሰለባል። እውነተኛ የወንድነት ግርማን ሳይኾን፣ ለባርነት የተመቸ ምስኪንነትን ይማራል።
በእውነት መንገድ ላይ መሄድ መከራ መስሎ ስለሚታየው፣ እንደ አሳሳቾቹ አስመሳይና አድርባይ መኾንን እንደ አማራጭ፣ እንደ ብልሃት፣ እንደዘመናዊነትና መንፈሳዊነትም ይወስዳል።
“እውነት” እያሉ ከማይኖሩት፣ “ዋጋ ክፈሉ” እያሉ ከማይነኩት ለሆዳቸውና ለዝናቸው ከሚሮጡ አስመሳዮች ተጠንቀቁ። የሚናገሩትና የሚኖሩት አንድ ካልኾነ፣ እነርሱ አደግዳጊ የውሸት አሳላፊዎች ናቸው።
በእውነት መንገድ ላይ አልፈው ፈተናዎችን በጽናት ካልተጋፈጡ፣ ስለ ወንድነት ሊያስተምሩ አይችሉም። ከአስመሳዮች ተለይታችሁ፣ በእውነት መንገድ ላይ ዋጋ ለመክፈል ጨክኑ።
እውነተኛ ወንድነትና አባወራነት የሚጸናው፣ ሲነገር ሲወራም ከልብ የሚደርሰው፣ በእውቀት ከተራቀቀቡት፣ ከለፈፉበትና ከጻፉበት ይልቅ ዋጋ ሲከፈልበት ብቻ ነው!
ከአስመሳዮች ራቁ! ትውልዱን ለባርነት በጃንደርባነት ለመማረክ ልብስ እየቀያየሩ ከሚመጡት ተጠበቁ! ለዚሁ ዓላማ ሲባል መድአክና ወንበር ይሰጣቸዋልና!
0 Comments