ፍቅር በጸብም ይገለጣል!



ክርስትናን ከእውነቱ ነጥለው፣ ከትውፊቱ ለይተው፣ ከባህሉ አርቀው በፍቅር ስም ሸቅጠው ያልጮች፣ የጃንደርቦች እንዲኾን ባፍጢም የወደቁት ያስተምራሉ!

ጸብ “የክፋት መሣሪያ ብቻ ነው!” የሚሉ “ሊቃውንት” ትውልዱን ለባርነት ያጩ፣ በዚያም ድርጎ የሚከፈላቸው የጠላት ቅጥረኞች ናቸው።

እነርሱ ክርስትና “ከፍቅር ጋር እንጂ ከጸብ ጋር ምንም ሕብረት የለውም” ሲሉ ለትውፊታችን ዐዲስ የኾነ “ያልጮች ክርስትና” ደርሰው ይተርካሉ!

በዚያም ባርነትን የወደደ፣ የመረጠ፣ የፈቀደ፣ ያጸደቀ፣ በእርሱም የተመጻደቀ፣ የታበየ፣ የወጣለትና የተዋጣለት ወዶገብ ባርያ፤ አባቶቹንም ፍጹም የማይመስል አልጫም ትውልድ ያፈራሉ!

ትውልዱ ከትውልዱም ወንዱ ከወንዱም በተለይ አባወራው ቤቱን፣ ቤተሰቡን፣ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ማኅበረሰቡን፣ እምነቱን፣ እውነቱን፣ ማንነቱን፣ ወጉን፣ ባህሉን፣ እሴቱን፣ ክብሩን፣ ድንበሩን፣ ሀገሩን ሊያጠቃ፣ ሊቀማ ከመጣ ጠላት የሚታደግበትን ተዋጊ ድለኛነቱን፣ ወኔውን ይሰልቡት ዘንድ ይህንን የመንፈሳዊነት መጀመሪያ፣ የቅድስናም መደምደሚያ እንደኾነ ያስተምራሉ።

ለመኾኑ ሚስታቸውን ለሚቀማ እህታቸውን፣ እናታቸውን ለሚደፍር ሴት ልጃቸውን ጨምረው ይሰጣሉን? ወይንስ ወንጀለኛን በጸብ የሚያስታግስ ፖሊስ ይጠራሉን? ወይንስ ራሳቸው እስከ ሞት ይተናነቃሉን?

ትውልዱ ከደረሰበት የእንከፍነት፣ ከንክር ምስኪንነት፣ ከስልብ ጃንደርብነት ይበልጥ ምን እንዲኾንላቸው እንዲህ ያለ የባንዳ ትምህርት እንደሚዘሩ መርምሩ!

እነዚህ “መምህራን” ነን ባዮች ትውልዱን ከተቀበለው ትውፊት፣ ከወጣበት ባህል፣ ከታወቀበት ማንነትና ከኖረበት ወግ ነጥለው በባዕዳን ሸፍጥ ይበርዙታል። “መንፈሳዊነት” በሚል ካባ፣ እርሱን አልጫና ወኔ-ቢስ ለማድረግ ቆርጠውም ተነስተዋል።

ኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ክርስትናን እምነት ብቻ ሳይኾን ሕይወት፣ ባህል፣ ወግ፣ ጥበብ፣ ኑሮና ታሪክ፣ ጌጥም አድርጋ ትውልዷን ስታንጽበት ኖራለች አጊጣበታለችም!

አሁን ግን የዘመናችን “ሊቃውንት” “ፍቅርን” ከትውልዱ ተሰውሮ የቆየና እነርሱ ብቻ “በምሁር ዶማቸው” ቁፋሮ፣ “ባፍጢም በሆዳቸው ሲደፉ፣ ሲጭሩ፣ ሲቆፍሩ፣” ያገኙት “ዐዲስ ግኝት” ይመስል በስሙ ይነግዱበታል።

🌟 ወይ ኢትዮጵያን አያውቋትም!

🌟 ወይ ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ ደግሞም በዐዲሱ ኪዳን የተቀባበለችውን ትውፊት አያውቁም!

🚨 አለበለዚያ ግን እነዚህን ሁሉ በማወቃቸው ትውልዱን ከተመሠረተበት የእውነት መሠረት በሌላ በማይጸናበት ዐዲስ የአሸዋ መሠረት ላይ እንዲተክሉ የተመለመሉ የተላኩ ምንደኞች ናቸው!

እነዚህ “ሊቃውንት”ትውልዱ አባቶቹ የኖሩበት ክርስትና ለጽድቅ የሚያስጨክን፣ ለሐቅ የሚጋደል፣ ለፍትሕ የሚታገል መኾኑን ያውቃሉና፤

🌟 ለዚህም እንኳ የቅርብ ጊዜ ማስረጃው የአድዋ ድል አለና፤ ምንደኛ ኾነው ላደሩለት ጠላት ምርኮን ያስገኝላቸው ዘንድ ይህንን ኮንነው ያስተምራሉ።

ስለኾነም የትውልዱን ወኔ ለመስለብ፣ የአባቶቹን ዳና ለማጥፋት፣ ከእነርሱም ፈለግ ለማራቅ ሲሉ በየመድረኩ ጠላትን ከሚረታበት፣ በራሱ ላይ ሠልጥኖ ትውልዱን ከሚታደግበት ባላጋራ ወዶና ፈልጎ ካመጣው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትም ካላወገዙት፦

🚨 ጸብ ራቁ”፣

🚨 ድምጻቸውን አለስልሰው፣ ዓይናቸውንም አስለምልመው “ፍቅር... ፍቅር...” ይላሉ፤

🚨 ቃላቸውን አንቆርቁረው በእንባ “ተሰውሮ ኖሮ ስላገኙት ፍቅር” ያስተምራሉ፤

አባታችን እግዚአብሔር “ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው” ተብሎ መጻፉን ኢትዮጵያውያን ነገሥታቱም ጠፍቷቸው ነበርን?

ከጠላት ጋር ተናንቀው፣ በሕይወታቸው ተወራርደው ሀገርን፣ ቤተክርስትያንን፣ ድንበርን፣ እምነትንና እሴትን የጠበቁት “ፍቅር” ስለሌላቸው፣ ስላልገባቸው፣ ያልገባቸውም “ጸብ ያለሽ በዳቦ” ነበሩን? በፍጹም!

ቅዱስ ሚካኤልና ሰራዊቱ ከአመጸኛው ጋር መዋጋታቸው የተረጋገጠ እውነት ኾኖ ሕዝቡም ይህንን ሲሰማ አድጎ ሳለ፣ ዛሬ ግን ትውልዱ፦

👉 በአስመሳዮች ሸፍጥ የሚደለል እንከፍ፤

👉 “ቢጭኑት አህያ፣ ቢለጉሙት ፈረስ “እንዲኾን፤

👉 ለጠላት የተመቸ ወዶገብ ባርያ እንዲወጣው፤

👉 ለጌቶቻቸው ጃንደርባና፦ስልብ ታማኝ አገልጋይ፤ ይኾን ዘንድ ይሰበካል!

እኛ ጸብ የምንገጥመው ክፋት ከሰለጠነባቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሳይኾን፣ በተለይ እነርሱን ፈረስና አጋሰስ ካደረጓቸው ይበልጡንም አጋንንት ጋር ጭምር ነው።

በፍቅር ስም የሚደረግ ያልጮች ስብከት ትውልድን አይታደግም። “አይታደግም” ብቻ ሳይኾን ትውልዱን ለባርነት ይገራዋል እንጂ።

ክርስትና ለጽድቅ የሚያስጨክን፣ ከእውነት ጎን የሚቆም፣ ስለፍትሕ የሚጮህ ጠላትንም በኃይል የሚጋፈጥ እውነት ነው። ይህም ደግሞ ስለሚወዷቸው፣ ስለሚወዱት፣ ስለቆሙለት እውነት ጸብን ካመጣው ጋር በጸቡ በመግጠምም ጭምር ይገለጣል።

ልጆቻችንን ከእንዲህ ያሉት ባፍጢም ከተደፉ ሆዳደርና ባንዳ “ሊቃውንትና ትምህርታቸው” መጠበቅ ትውልዱንና ተስፋውን ከጥፋት መታደግ ነው።

💪 አድዋ ጸብን ጭሮ ላመጣው ጸበኛ ጠላት፣ ቋንቋው በኾነው ጸቡ፣ ልክና ተገቢው መልስ የተሰጠበት ፍቅር-ክርስትናን በሕይወት የኖሩ ኢትዮጵያውያን በተግባር የሀገር፣ የእምነት፣ ፍቅራቸውን በደምና ባጥንታቸው የጻፉትበ ድል ነው!

በእነዚያ ምንደኛ ሆዳደር “ሊቃውንት” ስሌት መሰረት ቁጡ፣ ቆራጥ፣ ቆፍጣና፣ ተዋጊ ድለኛም የነበሩትን አርበኞቻችን “ፍቅር የማያውቁ ጸበኞች” መኾናቸው ነው።

ለዚያም ነው ለእኛ አቅመቢስነት፣ ጎስቋላነት፣ እንከፍነት፣ ወኔቢስነት፣ አላዛኝነት፣ ነፍራቃነት፣ ፈዛዛነት፣ ስልብነት፣ ጃንደርባነት፣ ባርነት እንደ የመንፈሳዊነት ከፍታ የጽድቅ ጥግም ተድርገው የሚሸጡልን!


Post a Comment

0 Comments