✍ ናትናኤል ሰሎሞን | በማለዳ ንቁ | ኢትዮጵያ አውታር
ለግለሰብ ዕድሜ ያልነው በትውልድ አንቀጽ ሲኾን ዘመን ይባላል፤ ዘመን የትውልድ ዕድሜ ነው፡፡
ያው በነጠላም ዕድሜ ያልነው በስብስብም ዘመን ያልነው፣ ያው ጊዜ የሚባለውን ነው፡፡
ስለዚህ ጊዜ ራሱ ምንድነው? .. ጊዜ የፍጥረት ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ሁሉ የተፈጠረው ነገር ሁሉ በጊዜ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በነርሱ ውስጥም ጊዜ ይገኛል፡፡
በፈጣሪና በፍጥረት መካከል ያለው አንዱና ዋናው ድንበር ጊዜ ነው፡፡ ማለት ሁሉ የተፈጠረው ነገር ሁሉ በጊዜ ውስጥ ሲኖር፣ ፈጣሪ ከጊዜም ውጪ ሁኖ ይገኛል፡፡ እንደውም ለራሱ ለጊዜ መኖሪያ ዓለሙ እሱ ነው፡፡
ፍጥረት ሁሉ ግን በጊዜ ሥር ይኖራል፡፡ እዚህ ጋራ 'ጊዜ' ስንል፣ በፀሐይ በጨረቃ በከዋክብት ዑደት የምናሰላውን የቁጥር ዕውቀት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ እሱ ዕውቀት የተመሠረበት በተፈጥሮ ውስጥ ያለ፣ ከፍጥረታት ጀርባ የሂደትና ለውጥ ሕግ የኾነ መስመር አለ፡፡ እሱን ነው ጊዜ የምንለው እዚህ፡፡
መጽሐፍ ይላል፡፡ ቦ ጊዜ ለኩሉ፡፡ ለኹሉ የራሱ የኾነ ጊዜ አለው፡፡ ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ " መክ 3:2፡፡ ኹሉ በጊዜ ውስጥ ይኾናል፤ እየኾነም ነው፡፡
ሰውም በጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ጊዜም በሰው ውስጥ አለ፡፡ ስለዚህ ጊዜን ማወቅ ራስን ማወቅም ነው፡፡ የኾነ ከኛ ተነጥሎ ያለን ሩቅ ሀሳብ ማወቅ ማለት አይደለም፡፡ ተፈጥሮን ማወቅ ነው፡፡ ብቻ አይደለም፤ በተፈጥሮና በሥርዓቷ ውስጥ እንዴት እንደምንኖር ማወቅም ነው፡፡ የዚህ ነገር ክብደቱ ይታየን ይኹን?
ጊዜ በእኛ ውስጥ ስላለ ነው የአካልና የአእምሮ ለውጦችን የምናከናውነው፡፡ በኛ ውስጥ ካለው የጊዜ እውነት የተነሳ ነው ሥጋዊውም ኾነ ሥነ ልቡናዊ ለውጦች በእኛ የሚታዩት፡፡ ለምሳሌ ሁላችንም በተፈጥሮ በኩል ተጉዘን ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን እንደርሳለን፡፡ ይሄ በኛ ውስጥ የተቀመጠ ጊዜ ስላለ ያከናወንነው ለውጥ ነው፡፡ እንዲሁ ከላይ መጽሐፍ እንዳለው ለመወለዳችን፣ ለማደጋችን፣ ለማርጀታችን የተሰጠ ራሱን የቻለ የየራሳችን ጊዜ አለን፡፡ እሱ መኖሪያ ዓለማችንም እኮ ነው፡፡ በወንጌል "ብርሃን ሳለላችኹ ተመላለሱ" የተባለው አንድም ይህን የየራሳችንን ጊዜ/ዕድሜ ሲናገረው ነው ይላሉ አበው፤ እውነት ነው፡፡ (ዮሐ. 12፡35)
ይሔ ወደ አንድ ልናስተውለው ወደሚያስፈልግ ሀሳብ ቀጥሎ ይመራናል፡፡ ይሔውም ዕድሜ የየራሳችን ዓለም የኾነልን ጊዜ ከኾነ፣ በዚህ የጊዜ መስመር ላይ ተቸርችረው የተቀመጡ በራሳቸው ያሉ አንጓ ሀሳቦችና ሥርዓቶች አሉ የሚለውን ሀሳብ ነው፡፡
እነዚህ በጊዜ ውስጥ ተይዘው የተቀመጡ ሀሳቦች ስላሉ ነው በሂደት እየደርስን ስናገኛቸው የምናስባቸው፣ የምንኖርባቸው፡፡ ለምሳሌ በልጅነት ጊዜ ሳለን የልጅነትን ሀሳብ እናስባለን፡፡ ልብ እናድርግ፡፡ እንደ ልጅነት እናስብ ብለን ተዘጋጅተን አይደለም፤ ራሱ ሀሳቡና አኗኗሩ የሚያገኘን ካለንበት የልጅነት ጊዜ የተነሳ ነው እንጂ፡፡
በአጭሩ እንደ ልጅነት ማሰብንና መኖርን የሰጠን ራሱ የልጅነት ጊዜው ነው፡፡ ከዚያ እንደገና ተጉዘን የወጣትነት ጊዜ ላይ ስንደርስ፣ እንደ ወጣት ማሰብን በራሱ እናገኛለን፡፡ ለዚህ ነው ግሩም ሰው ጳውሎስ "ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።" (1ኛ ቆሮ. 13:11) የሚለው፡፡
ነጥቡ ምንድነው እዚህ ጋ? ጊዜ በራሱ የሚሰጠን ሀሳብ አለ ነው ነጥቡ፤ ወይም በጊዜ ውስጥ ተይዞ የተቀመጠ ሀሳብ አለ ነው፡፡ በሽምግልና ጊዜ ያለውን ሀሳብና ሥርዓቱን ለማግኘት በዛ ዕድሜ ውስጥ ሰተት ብለን በተፈጥሮ መግባት አለብን፡፡ እንጂ ልጅ ወይም ጎልማሳ ኹነን ሳለ ስለ አዛውንትነት መጽሐፍት ብናነብ፣ መረጃ ብንሰበሰብ፣ እንዴት እንደሚኖሩ ብንለማመድ፣ ... አናመጣውም፡፡ ጊዜው ራሱ ካልሰጠን፣ ውስጡ ያለው የመኾን ሀሳብና ሥርዓት አይመጣም አያችሁት፡፡
ይሄ አሁን በዕድሜ በልጅነት መስለን ስናወራው ቀላል ነገር ይመስላል፡፡ ግን እያንዳንዱ ሀሳባችን፣ የመኖር ሥርዓታችን በዚህ የተያዘ ነው፡፡ በትውልድም ማዕቀፍ ስንናየው፣ ዘመን በራሱ ለትውልዱ የሚሰጠውን ሀሳብ ትውልዱ ካላገኘው፣ ሲቃወስ ነው የሚኖረው፡፡ በማይበቅልበት ቦታ ሲዘራ ነው የሚውለው፡፡ ዝምታንም አይሰማም፤ ንግግርንም አይሰማም፡፡ ዘመኑ በራሱ የተሸከመውን ያላገኘ ትውልድ፣ ከራሱ ተጣልቶ እንደመኖር ነው የሚኾነው፡፡ ልክ በግለሰብ ደረጃ እንዳልነው አንድ ሽማግሌ ሽምግልናው የሰጠውን ሀሳብና ሥርዓት ትቶ በልጅነት ሀሳብ ቢመላለስ፣ አስቀድሞ የተጣላው ከራሱ እንደኾነው ማለት ነው፡፡
በወንጌል አንድ የክርስቶስ ድምፅ እንዲህ ይላል፦ "ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?" (ማቴ. 16:3)
ይህ በወቅቱ የተነገረባቸው ትውልዶች፣ ዘመኑን ለይተውትስ ቢኾን ኑሮ ከፊታቸው ቁሞ ያለውን ክርስቶስ ባወቁት ነበረ፡፡ እነርሱ ግን ሊያዘንብ ያለውን ሰማይ ባኮረፈው ደመና በኩል ያውቁታል እንጂ የዘመኑን ገጽ ማንበብ አልተቻላቸውም፡፡ ዛሬም እኛ እንዲኹ ነን፡፡
ዘመኑን ማወቅ በግለሰብ የሥጋ ሀሳቦች ተጠርንቆ ለሚኖር ሰው፣ ሚዛን የማይደፋ ነገር ይመስለዋል፡፡ ይኹንና ግን ኹሉ ነገር በጊዜ ውስጥ ነው ያለውና የሚኾነው፡፡ ትውልድም በራሱ ዘመን ውስጥ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ዘመኑን አላወቀም ማለት ራሱንም አላወቀም እንደማለትምም ነው፡፡
ትውልድ ለዘመኑ ያለውን ሀሳብ መፈለግ አለበት፡፡ እግዚአብሔርንም ተናገር ማለት አለበት ከዕለት ተዕለት የኑሮው ጥያቄዎች ከፍ አድርጎ፡፡
በዚኹ በኩል እንደገና ወደ አንድ ጉዳይ እንሂድ፡፡
ለመኾኑ ይሄ ዘመን ምን ይመስላል? ምንስ ይታይበታል? ብለን እንጠይቅ፡፡
እኛ እስከዛሬ የመጣነውን እንደኾንን ኹሉ፣ የዓለም ታሪክም እስከዛሬ የመጣውን ኹሉ ነው፡፡ የአኹኑን ዘመን፣ የእስከዛሬው ትውልድ ዘመናት ሲቀባበል አድርሶታል፡፡ ነገሩን መጽሐፍ እንደማንበብ እንውሰደው፡፡
አንድን መጽሐፍ እስከ ገጽ 20 አንብበነው ከኾነ፣ ለኛ መጽሐፉ ማለት እዛ ድረስ ያለውን ነው ማለት ነው፡፡ ደረሰን እያነበብነው ያለው ገጽ፣ ካለፉት ገጾች ተነጥሎ የቆመ አይደለም፤ በራሱ ገጽ ላይ የተጻፈበት እንዳለ ሁኖ፣ ከነበሩት 19 ገጾች ጋራ የተያያዘም ነው፡፡ ተረድታችሁታል?
ያለንበት ዘመን እስከዛሬ የመጡት ዘመናት ሁሉ ቅጣይ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች እስከዛሬ ሲፈስ የመጣው ታሪካችን ውጤት ነን፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ከኾነ፣ ስለ ዓለም የሰው ልጆች ታሪክ በቅጡ ማወቅ፣ በአንድም በሌላም ዛሬ በዙሪያችን ከብቦን ስላለው ነገር ሁሉ ማወቅ ነው፡፡
አሁንም ወደ ክርስቶስ ለማሳያ መለስ እንበልና ነገሩን እንጨብጠው፡፡ በአንድ ንግግሩ ደሞ በዘመኑ የተገለጠበትን የአይሁድ ትውልድ እንዲህ ሲናገረው እንሰማለን ፦ "የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ።" (ዮሐ. 8:37)
ሰዎቹ የአብርሃም ዘሮች ነን ይላሉ፡፡ ናቸውምም፡፡ ግን በሥጋ ነው፡፡ በነፍስ አያውቁትም፡፡ በሌላ አባባል የአብርሃም ዘሩ እንጂ ሀሳቡ (ሥራው) የላቻቸውም፡፡ እንዲሁ በተገኙበት ገጸ ዘመን ያሉ ትውልዶች እንጂ የመጡበትን የዘመናት እውነታዎች አያውቁትም፡፡ ዛሬም ኢትዮጰያውያን እንዲሁ ይመስላሉ፡፡ የአባቶቻችን ልጆች ነን እንላለን፤ የአባቶቻችን ሥራ ግን ከኛ ጋር የለም፡፡
በሌላ አነጋገር፣ በዚህ ዘመን የተገኘን ትውልዶች ብንኾንም፣ ባለፉት ዘመናት የነበሩትን ተቀባብለው እዚህ ያደረሱንን ትውልዶች አናውቃቸውም፡፡ በሥጋ አይደለም፡፡ ነገሩ በሥጋ እንወቅ ብንልስ እንዴት እንችላለን? ሀሳቦቻቸውን ነው የምንለው፡፡ ግን ቀድሞውኑ ፍላጎቱስ ከልብ አለን ይሁን?
ለማንኛውም ወደ መጽሐፉ እንመለስና በአብርሃም የነበረቺው ሀሳቡ፣ በኋላ ከፊታቸው በሥጋ ቆሞ የሚያናግራቸው የእውነት ቃልም ነው፡፡ ለዚህ ነው ቃሌ በእናንተ ስለሌለ የአብርሃም ዘር እንጂ ሥራው የላችሁም ይላቸው የነበረው፡፡
ወደ ነጥባችን ዘወር ስንል፣ ይሄ ዘመን ያለፉት ዘመናት ስብስብ ነው፡፡ ተከታትሎ ያለንበት ጋ መጥተናል፡፡ ስለዚህ በዙሪያችን በተለያየ ዘርፍና መልክ የምናያቸው ብዙ ነገሮች የእስከዛሬ ትውልዶች ድምር ውጤቶችም ናቸው፡፡
ያ ብቻ አይደለም ደግሞ፡፡ ስለዘመናት ስናወራ ስለ ሥልጣኔዎች አለማውራት አንችልም፡፡ ምክንያቱም የየዘመናቱ መልኮች እነሱ ስለኾኑ፡፡ ሥልጣኔ ግን ምንድነው?
ለአንድ ሰው ዕድሜ ለትውልድ ዘመን እንዳልነው አካሄድ፣ ለአንድ ሰው መክሊት የምንለው በሕዝብ ደረጃ ሲገለጽ ሥልጣኔ ይሰኛል፡፡ ሥልጣኔ የሕዝቦች መክሊት ነው፡፡ ከዚህም የሚጨመሩ ዝርዝር ፍቺዎችም፣ መገለጫዎችም ስላሉት መሻቱ ያላችሁ ልትፈላልጉበት ትችላላችሁ፡፡
እንዳይረዝም ነገሩን እናሳጥረውና፣ አኹን ያለንበት የዘመኑ ሥልጣኔ ሥርዓቱ ዓለም አቀፋዊ መኾኑ እስከዛሬ ከነበሩት በዋናነት ይለየዋል፡፡ ጥንስሱን ከምዕራቡ የዓለም ክፍል ያደረገው፣ ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ የተወለደው የዚህ ዘመን ሥልጣኔ፣ ዓለምን (ሀገራትን ቢሉም) በሀሳቡና በሥርዓቱ አጥምቆ ወደ አንድ መልክ አካትቷል፡፡ የቴክሎኖጂ አብዮት ዋነኛው መገለጫው ነው፡፡ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በሥነ መንግሥታት ውስጥ የራሱን መልኮች በተለያየ ጎዳና አሥርጿል፡፡
እና ቦ ጊዜ ለኩሉ ብለንም የለ? ሥልጣኔም ያው ከጊዜ በታች ነው፡፡ ማለት፡ አንድ ሥልጣኔ የሚጀምርበት፣ የሚፋፋበት፣ ከዚያ የሚወድቅበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡
እዚህ ለማለት የምንሞክረው አኹን ታዲያ፣ ከላይ የጠቀስነው በዘመኑ ውስጥ ሰፍኖና ገኖ ያለው አውሮጳ መራሹ ሥልጣኔ ጊዜውን ጨርሷል ነው፡፡ ሰለዚህ እየወደቀ ነው፡፡ በመፍረሱ ዑደት ላይ ነው፡፡ የዚህ ጊዜው ላይ ስለመኾኑ የሚናገሩ ብዙ ከግለሰብ እስከ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነቶችና ተቋማት ድረስ የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነሱን ቀጣይ በሚኖረው ፕሮግራም እናወራቸዋለን፡፡ ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ እየፈረሰ ባለ የሥልጣኔ ሥርዓት ውስጥ ሳለን፣ እንዴት እንለፍ የሚለውንም በአቅማችን ለመጨዋወት እንሞክራለን፡፡ ከጠቀመ፡፡ እስቲ ያቆየን፡፡
0 Comments