✍ ሚካኤል ዘኢትዮጵ
የጎዳና ላይ ምግብን ወይም በዐደባባይ መመገብን በተመለከተ በእስልምና አስተምህሮ (በሐዲስ) የተቀመጡ ገደቦችን መሐመድ በንግግሮቹና ከእስልምና ሥነምግባር (አዳብ) አንጻር የሚከተሉትን አስተምሯል።
መሐመድ ሙስሊሞች በመንገድ ላይ ወይም በዐደባባይ እንዳይቀመጡ በግልጽ አስጠንቅቋል። በቡኻሪና ሙስሊም በተዘገበ ሐዲስ ላይ እንዲህ ይላል፦ "በመንገዶች ላይ ከመቀመጥ ተጠንቀቁ!" አሉ። ሰሃባዎችም "የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኛ እኮ የምንመካከርበት የግድ መቀመጥ ያለብን ቦታችን ነው" አሏቸው። እርሳቸውም "መቀመጥ ካለባችሁ ለመንገዱ መብቱን ስጡት" አሉ። "የመንገዱ መብት ምንድን ነው?" ተብለው ሲጠየቁ፦ "አይንን ሰበር ማድረግ (ያልተፈቀደን ነገር አለማየት)፣ ሰዎችን የሚያውኩ ነገሮችን ማስወገድ፣ ሰላምታ መመለስ እና በመልካም ማዘዝ ከመጥፎ መከልከል ነው" (ሳሂህ አል-ቡኻሪ፡ 2465፣ ሳሂህ ሙስሊም፡ 2121) አሉ።
ይህ ሐዲስ እንደሚያሳየው፣ መንገዶች ለተላላፊዎች እንጂ ለስብሰባና ለምግብ ግብዣ ተብለው ለአገልግሎት እንደማይውሉ ነው። አሁን እየተደረገ ያለው የጎዳና ላይ ኢፍጣር ግን መንገዶችን በመዝጋትና የሰዎችን እንቅስቃሴ በማወክ ለሐዲሱ ተቃራኒ ሆኖ ይገኛል (ፈትዋ አል-ላጅናህ አል-ዳኢማህ፡ ቁጥር 2/127)።
ሌላው በእስልምና የሕግ መርሆዎች (ፊቅህ) ውስጥ "ሙሩዓህ" የሚባል ጽንሰ-ሀሳብ አለ። ይህም የአንድን ሰው ክብርና ሥነምግባር የሚለካበት ነው። ጥንታዊ የእስልምና ሊቃውንት (ለምሳሌ ኢማም አል-ጋዛሊና ሌሎችም) እንደሚገልጹት፦ በመንገድ ላይ መመገብ (አል-አክሉ ፊ-ሱቅ)፦እንደ መጥፎ ሥነምግባርና የሰውን ክብር እንደሚያሳንስ ይታያል (ኢማም አል-ጋዛሊ፣ ኢሕያ ኡሉሙዲን፡ ጥራዝ 2፣ ገጽ 11)። በአደባባይና በሰው ፊት መመገብ በአንዳንድ የፊቅህ ትርጓሜዎች "የአንድን ሰው ምስክርነት (ሸሃዳ) ውድቅ ሊያደርግ የሚችል ተግባር ተደርጎ ይቆጠር ነበር (አል-ማውሱዓህ አል-ፊቅሂያህ፡ ጥራዝ 17፣ ገጽ 132)። ምክንያቱም ሥነምግባር የጎደለው ተግባር ተደርጎ ስለሚወሰድ ነው።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ወሃብያዎች የሚፈጽሙት ግን ለፖለቲካዊ መገለጫነትና ለኃይል ማሳያነት የሚውል መሆኑን እያየን ነው። ይኸውም የሌሎችን እምነት ተከታዮች መብት (የመንገድ አጠቃቀም) የሚጋፋ መሆኑ፣ ከእውነተኛው የእምነቱ ትዕዛዝ ያፈነገጠ ያደርገዋል (ሱረቱ አል-በቀራህ፡ 188 — የሌሎችን መብት ያለአግባብ ስለመጋፋት የሚከለክል አንቀጽ)።
ስለዚህ መሐመድ "መንገድ ላይ መቀመጥን" መከልከሉና የእስልምና ሊቃውንት በዐደባባይ መመገብን እንደ ነውር መቁጠራቸው እየተከናወነ ያለው "የጎዳና ላይ ኢፍጣር" ከእምነት ይዘቱ ይልቅ ፖለቲካዊና የታሪክ ባለቤትነትን የመቀማት (እንደ መስቀል አደባባይ ያሉ ስፍራዎችን) ዓላማ ያነገበ መሆኑን ያረጋግጣል።
0 Comments