ዛሬን ለወለደው እንጂ ለሚያልመው ነገ አይሰጠውም!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

በውሸት ልቡ ጠፍቶ፣ ስጋትና ብሶት ተግቶ፣ ባልጫነት ተሞልቶ በምኞት ሕልሙን ለሚጠባበቀው፤ ከሕልሙ ሳይወጣ፣ ዘሩም ባክኖ ሲቀር፤ በእውነት፣ እምነትና እሴቱ ታምኖ፣ በልበሙሉነት ለዘራው ግን ነገ የእርሱ ምርት ናት!

ልጆች ጀርባችንን የምናይባቸው፣ ዛሬያችንን የምንሰጣቸው፣ ነጋችንን የምንኖርባቸው ናቸው። እነርሱ ራሳችንን፣ ማንነታችንን፣ ተፈጥሮአችንን የወደድንበት፣ ከራሳችን ሞልቶ የተትረፈረፈ እውነተኛ ፍቅር መግለጫ መገለጫዎች ናቸው።

ኾኖም ግን ልጆች ይወለዱ ዘንድ፦ አባትና እናት ያስፈልጋሉ፤ አባትና እናት ይባሉ ዘንድ በባልና ሚስትነት ባንድነት መዋሃድ ይቀድማሉ፤ ባልና ሚስት ለመኾን ደግሞ መፈቃቀድ ይፈልጋሉ።

ይህ ትውልድ የሚቀጥልበት ተፈጥሮአዊ ሕግ፣ ሥርዓት ዛሬ ባጋጣሚ አይደለም፤ ኾን ተብሎ በማርክሳውያን፣ በግራምሺያውን ተጥሷል።

ለምን?

እርሱ ጠንካራ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሕብረተሰብ፣ ብሔር(ሀገር) ይሠራልና።

ስለዚህም ማርክሳውያን በዚህ ተፈጥሮአዊ በኾነው ሥርዓት ውስጥ ያለውን፦

☀️ የሥልጣን መዋቅር (አባወራዊ ሥርዓት)ጠቅሰው፣

☀️ ከሥልጣኑ ስር ያሉትን ጠቅሰው፣

☀️ ከሥልጣኑ ላይ ያለውን (አባወራውን) ወቅሰው፤ በመኮነን ይህን ቅዱስ ተቋም የማፍረስ ዘመቻ ጀመሩ።

በዚህም አባወራው በዝባዥ፣ ጨቋኝ፣ በዳይ በተባለበት ሥልጣኑም የአንባገነን ተብሎ እንዲጠላ ተደረገ። ሴቷም የሰማይ አባቷ እንደፈቀደ ለባሏ መገዛት፣ መታዘዝና ማገዟን ጠልታ “በመብትና በነፃነት” ስም እንድታምጽበት ተደረገ።

በዚያም የተወለዱት ሕጻናት ሁሉ ይህንን “የጨቋኝና የተጨቋኝ” ትርክት እየተጋቱ አድገው፤ እርስ በእርስ ላለመተማመን፣ ለመጠራጠርና አልፎ ተርፎም ባሉባልታ ብቻ ለመጠላላት ተዳረጉ!

እነሆ! ትውልዴ ከዚህ የተነሳ ተፈራራ! ደርሶ ለመዳራት እንጂ ማንም ልቡን ቤተሰብ ለመመስረት፣ ትውልድን ለማስቀጠል፣ ነገንም ለመውረስ ፈሮቶ ዛሬውን ለጥጦ፣ በማለም ይኖራል!

እንዲህ የፈራውም በልኩና በመልኩ “ሰበባ ሰበቦችን” እየሰፋ የሚለብሳቸው፣ ሳይነጋገርም በወል የሚግባባቸው፣ “እውነታውን አንካድ” እያለ ስጋቱን የሚያንርባቸው፣ በዚያም ፍራቻውን የሚያጠናክሩለት ኾነ።

👉 “ዘመናዊ ነኝ” ባዩ የኑሮ ውድነቱን፣ የፍቺ ወረርሺኙን እየዘረዘረ ራሱን ሲሰልብ፤

👉 “መንፈሳዊ ነኝ” ባዩ ደግሞ የዐለም መጥፋቱን፣ የሐሳዊ መሲህ መምጣቱን፣ የክርስቶስ መምጫ መቅረቡን... እያነሳና እየጣለ በሰበባ ሰበቡ ይስማማል፤ አንዳንዱም በእነዚህ ትውልዱ ላይ ይሸቅላል።

ስለዚህም የተሻለ ነገር ካልመጣ፣ ቢመጣ፣ እስኪመጣ እያለ በፍርሃቱ ተሸብቦ በደመነፍስ ይኳትናል፤ ሳይነቃ ሲባዝንም ድፍን ሦስትና አራት አስርት ዓመታት ማለፋቸውን ከመስታወት ፊት ሽበቱ፣ እየተጨማደደ የመጣ ፊቱ ይነግረዋል።

መልአካዊ እውቀቱና ስጋዊ ፍላጎት-ስሜቱ በአንድ በልቡ ተስማምተውለት እንደ ተገኘ ልከኛ፣ መልከኛ አባቱን መሳይ፤ ስጦታ ጸጋውን አብዝቶና ገዝቶ፤ እርሱን የሚያካፍላቸው ወልዶ፣ አብዝቶ ለመኖር አይደፍርም!

ለምን?

ከእውነት የተለየ፣ እምነት የሌለው፣ የአባቶቹን እሴት የዘነጋ፤ ነገር ግን ያስመሳይ ኑሮን ስለሚኖር!

ይህንን እያወራሁ የኑሮ ውድነትን ታስብ ይኾናል እኮ!

ትውልዴ ሃይማኖት እንጂ እምነትየለሽ ኾኗል! እርሱ የሚያምነው ስጋት፣ ፍርሃት፣ ጥርጣሬን ነውና ልባም፣ ልበሙሉ፣ ወኔያም ያባቱ ልጅ መኾን አቅቶታል።

“ገንዘብ፣ ዝና፣ ሥልጣን ሳገኝ” አገባለሁ፣ እወልዳለሁ ይበል እንጂ ዛሬ ያለውን፣ የሚኖረውን ኑሮ አይቀበልምና እርሱ የማይቀበለውን የምትቀበል መቼም ለማግኘት ይቸግራል።

ሴቷን የሚማርክ አንዳች ተፈጥሮአዊ ባህርይ እርሱም ድፍረት፣ ጥንካሬውም የለውም። ቢኖሩትም በእርሱ በልቡ ያሉ ሳይኾኑ ከእርሱ ውጪ በአፍአ፦ በገንዘቡ፣ በደሞዙ፣ በልብሱ፣ በምላሱ፣ በዝናው፣ በመኪናው ላይ ናቸው።

ስለኾነም እነዚህንም ይዞ እንኳ ለመተዋወቅ፣ ለመፈቃቀድ፣ ለማግባትና ለመውለድ ይፈራል! “ሳገኛቸው ያንን ኑሮ እደፍራለሁ” ቢልም “ድፍረቱ” የልቡ አይደለምና፤ የገንዘቡ፣ የዝናው፣ የልብሱ፣ የምላሱ ነውና ዛሬም ይፈራል፣ ፍርሃቱን ሌሎችም ይጋሩታል፣ ይስማሙታል፣ ያጸኑለታል፣ ያጽናኑታልና ይጽናናልም፤ ደግሞ ወደ ሕልሙ ዋሻ፣ ወዳልጫነቱ ጎሬ ይመለሳል።

መፍትሔው የአባቶቹን ታሪክ፣ ትውፊት፣ እሴት መማር፣ ሲነገርም መስማት፣ ሲተረክም ማስተዋል ነበር። ከዚህ በባሰ በብዙ መከራዎች ውስጥ ያለፉ እነርሱ እምነታቸውን ከአባታቸው፣ ማንነታቸውን ከእሴታቸው ላይ አድርገው ዘሩ ትውፊትን አቀበሉ እርሱም ተገኘ።

እርሱ ግን በአጋንንት አይደለ፣ በስጋት ታስሮ፣ በፍርሃት ተቀፍድዶ ዛሬን ከመኖር ያልማል፣ በምኞት ይባክናል። ነገ ሲሄድ ግን ዘሩ ይጠፋል፣ ስሙ ይረሳል፣ የመሠረተው ይፈርሳል፣ ያስቀመጠው ይነሳል፣ የተከለው ይነቀላል፣ የእርሱ የነበረው ሁሉ ይወረሳል።

ለምን?

እሴቱን የሚያስቀጥል ትውልድ የለውምና! ቢኖረውም የእርሱ ቢጤ ልባልባ አል፣ ጃንደርባ ነውና!

ወንድምዓለም! ነገ የምትሰጠው ሰው፣ ትውልድ፦ ዛሬን የዘራባት የወለደባት እንጂ ከመውለድ በስጋትና በፍርሃት ተቀፍድዶ፣ ለእነርሱም “አሳማኝ” ሰበባ ሰበቦችን ተጎናጽፎ፣ በሕልም ለሚመኛት አይደለም!

ምን እየሠራህ ነው?

ለምን የብሶት ምሬተኞች፣ አዛኝ አላዛኞች፣ ለቀስተኛ ነፍራቆችን ወሬ እየሰማህ ልብህን ታደክማለህ? ተነስ በድፍረት በጥንካሬ በራስህ ላይ ሠልጥነህ፣ በእምነት በዘራኸው ዘር፣ በእርሻ ሰብልህም (በልጆችህ መካከል) በአርአያነት ተመላለስ፤ ጊዜ ወደፊት ይሄዳል እንጂ ላይመጣ ላይመለስ!

ሰምተሃል!

Post a Comment

0 Comments