ግብር የማይከፍሉ የትውልድ ነጋዴ “ግብረሰናይ” ሱቆች

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ሀገር በከፍተኛ ኢኮኖሚ ድቀት፣ የስብዕና ወድቀትና የገበያ ግሽበት፣ በሰላም አጦትም በምትሰቃይበት ወቅት ግብር የማይከፍሉ “የግብረሰናይ” ሱቆችን እንደመክፈት የሚያዋጣ “የንግድ ዘርፍ” የለም!

ሀገር በቁም በምትሰቃይበት፣ ሕዝብ በኑሮ ውድነትና በጦርነት በሚታመስበት በዚህ የመከራ ዘመን፤ በጭንቁ ላይ ተቀምጠው የሚከብሩ፣ በቁስሉ ላይ የሚያተርፉ ነጋዴዎች በዝተዋል።

እነዚህ “ግብረ-ሰናይ” ተብለው የተሰየሙ፣ ነገር ግን ተግባራቸው “ትውልድ-አምካኝ” የኾነ ድርጅቶች፤ ሀገርን ለማዳን ሳይኾን፣ የትውልዱን ስብዕና አርክሰው ለባዕዳን ጌቶቻቸው ሪፖርት በማቅረብ የሚኖሩ የሸፍጥ ሱቆች ናቸው።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ NGO (የመንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች) መክፈት ያለ ትርፋማ ንግድ የለም። ግብር አይከፍሉም፤ ምርታቸው ግን ትውልድን ልብአልባ አድርጎ ለባዕዳን መሸጥ ነው።

ገበያው ቀላል ነው፦ ብዙ የውጭ ዶላር መቀበል፣ ከዚያም በ”ጾታ እኩልነት”፣ “በመብት” እና “በነፃነት” ስም የአባወራውን ግርማ የሚንቁ፣ እናትነትን የሚጸየፉ፣ ወንድነታቸውን የጠሉና ለባዕድ እሴት የተንበረከኩ አልጫዎችን ማምረት!

እነዚህ “ሱቆች” በየከተማው እንደ አሸን የፈሉት፣ በየገጠራቱ የሚራወጡት ሕዝቡን ለመርዳት ሳይኾን የትውልዱን ልብ ሰልበው፣ ለባርነት የተመቹ፣ በነፃነት ስም የተሰለቡ አድርጎ ማስቀረት ነው።

ለእነዚህ ግብርአልባ ገቢ አስገኝ “ግብረሰናይ ሱቆች፦

☀️ የሸቀጥ ዕቃቸው ትውልድ ወይም ልቡ ነው፦ እርዳታና ሥልጠና በሚል ሰበብ ገብተው፣ የወጣቱን ልቡን፦ እሴቱን፣ የቤተሰቡን መዋቅር፤ በመበዝበዝ እንደ ሸቀጥ ለባዕዳን አጀንዳ ይሸጣሉ።

☀️ ግብር አይከፍሉም፦ ይህ ግብር የገንዘብ ብቻ አይደለም። ለሀገር ባህል፣ ለሃይማኖት እሴትና ለትውልድ ቀጣይነት የሚከፈል የሞራል ግዴታ የለባቸውም። ከሀገር የሚወስዱ፣ ከትውልዱ የሚነጥቁ፣ ማኅበረሰቡን በልማት ስም የሚዘርፉ እንጂ ለሀገር የሚሰጡ አይደሉም።

☀️ የትርፍ አቅጣጫቸው መለኪያ ጥፋት ነው፦ ሪፖርታቸውና ውጤታቸው የሚለካው ለገንዘብ ለጋሾቻቸው በሚያቀርቡት “ስንት ወንድን ሰለብን? ስንት ሴትን አሳመጽን? ስንት ቤተሰብን አፈረስን? በዚያም ትውልዱን ከአባወራዊው ጭቆና ነፃ አወጣን” በሚል ስሌት ነው።

ይህንን የጥፋት መንገድ የሚመሩትና የሚያሳልጡት ደግሞ ማን እንደኾኑ ታውቃላችሁ ማስትሬትና ዶክትሬት የጫኑ፣ ነገር ግን የሀገራቸውንና የወገናቸውን እሴት የጠሉ “የተማሩ” የራሳችን አድርባይ ልጆች ባንዳዎች ናቸው።

እነዚህ ፊደል የቆጠሩ፣ ነገር ግን ልባቸው የሰለለ አሳላጮች፤ በዩኒቨርሲቲ ያገኙትን ዕውቀት ሀገር መገንቢያ፣ ተሰውልድ ማነጫ ከማድረግ ይልቅ፣ የባዕዳንን የጥፋት መርዝ ለትውልዱ በሚመጥን “ሳይንሳዊ” ቋንቋ አቀናጅቶ፣ ለጆሮ የሚስማማ ማቅረቢያ ያደርጉታል።

የእነዚህ “ምሁራን” ሥራ፦

🚨 ባህልንና እምነትን እንደ “ኋላ ቀርነት” እየፈረጁ ወጣቱን ማሳሳት፣

🚨🚨 ቤተሰብን የሚያፈርሱ ሕጎችንና አሠራሮችን በምርምርና በፖሊሲ ግብዓትና ማሻሻያ ስም ማሾለክ፣

🚨🚨🚨 ለዶላር ብለው የገዛ ወገናቸውን ሥነ-ልቦና ለባዕዳን ተገዢ እንዲኾን ወኔቢስ፣ ስልብ፣ አልጫም አድርጎ ማመቻቸት ነው።

ሀገር በኢኮኖሚ ትደቃለች፣ ሕዝቧም ከስብዕናው ይወድቃል፤ በዚህ ውድቀት ውስጥ እነዚህ “የግብረሰናይ ሱቆች” በሚሸጡት መርዝ ትውልዱን ከልጅነቱ ጀምሮ “ልብ-አልባ” እንዲኾን ይደረጋል።

ዛሬ በሰላም እጦት የምንሰቃየው፣ ዛሬ በገበያ ግሽበት የምንሳቀቀው፣ በኑሮ ውድነት የምንሸማቀቀው፤ ለእውነት የሚቆም፣ የአባቶቹን ፈለግ የሚከተል በጠንካራ ስብዕና የተገነባ፣ ጽድቅ ወኔ የሚሠራበት ያለው፣ ልባም ትውልድ ስላጣን ነው።

ወንድምዓለም! ዛሬ በደጅህ የተከፈቱትን እነዚህን “የጥፋት ሱቆች” ነቅተህ ካልተከታተልህ፣ ነገ የምትረከበው ቤትም ኾነ ሀገር አይኖርህም።

Post a Comment

0 Comments