እርግዝና በሽታ በኾነበት ውርጃ ጤና ጥበቃ ይባላል

✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ልጆቻችን እርግዝናን እንደ በሽታ፣ እንደ እርግማን፣ እንደ እንቅፋት እንዲቆጥሩት ይማራሉ። እርሱን ማቆየት፣ ማስቀረትና ማጨናገፍም ጤንነታቸውን የሚጠብቅ እንደኾነ ይረዳሉ፤ ልባቸውም ይጠፋል፤ ሰውነታቸውም እንዲሁ!

በዚህ ሠለጠነ በሚባለው ዘመን፣ ትውልዱን ከማንነቱና ከተፈጥሮው የሚያፋታ ክህደት በ”ሳይንስ” እና በ”መብት” ስም ልጆቻችን ስለሚጋቱት ውሸት ማውራት አለብን።

እርግዝና—ያ የሕይወት ምንጭ፣ የክብር ማኅተምና የተተኪ ትውልድ ተስፋ፤ ዛሬ እንደ በሽታ፣ እንደ እርግማን፣ እንደ እንቅፋት እንዲቆጥሩት ይማራሉ።

በዚያም ማርገዝን የሚጠየፍ፣ ሕይወትን እንደ እንቅፋት የሚያይና ለዚህም “ኢኮኖሚ፣ ነፃነት፣ ሥልጣኔ” የሚሉ ሰበባ-ሰበቦችን የሚደረድር ትውልድ ማፍራት፣ ሀገርንና ማንነትን ከመሠረቱ መናድ ነው።

ልጆቻችን በትምህርት ቤትም ሆነ በየሚዲያው የሚሰሙት ትርክት እርግዝና “የነፃነት ጠላት፣ የእኩልነት እንቅፋት” እንደኾነ ነው።

ይህን ተፈጥሯዊ ጸጋ እንደ በሽታ እንዲሸሹት፣ ሲከሰትም እንደ እርግማን እንዲቆጥሩት ይደረጋሉ። በዚያም ምክንያት ጽንሱን ማጨናገፍና ሕይወትን መቅጠፍ “የሥነ-ተዋልዶ ጤናን መጠበቅ” (Sexual Reproductive Health and Right) ተብሎ በቃላት ጨዋታ ይሞካሻል።

ይህ ግን ጤና ጥበቃ ሳይኾን የሞራል ዝቅጠት፣ ሰውነት የሚበየንበት ልብ ከእውነት እምነቱና እሴቱ መለየት፣ በዚያም እርሱን አጥፊ ትውልድንም አምካኝ መርዝ ነው።

ሕይወት በሚገደልበት ስፍራ ጤና፣ ትውልድም በሚጨናገፍበት መቃብር ሕይወት የለም፤ ይልቁንም የተማረ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ተብሎ የጠፋ ልብ ጎስቋላም ስብዕና እንጂ!

ትውልዱን፣ ዘሩንና ታሪኩን ማስቀጠል የማይፈልግ፣ ለዚህም ጠላትና ሆዳደሮች የሰጡትን ሰበቦች ጠዋትና ማታ እንደ ጸሎት የሚደግም ማኅበረሰብ፣ ለባርነት የሰጠ፣ የተመቸ አልጫ ነው።

ጠላት ይህን የሚያደርገው ለሴቷ ወይም ለወጣቱ አስቦ ሳይኾን፣ ተተኪ የሌለውና ለወሬ የማይተርፍ በድን ትውልድ ለመፍጠር ነው።

አንድም ተተኪ ቢኖረው እንኳ ወዶና ፈቅዶ፣ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት አሳቦ የወጣለትና የተዋጣለት ባርያ፣ ባርነቱንም የወደደና ያጸደቀ ከእርሱም መውጣት የማይፈልግ አልጫ ትውልድ ለማፍራት ነው።

እርግዝናን የሚጠየፍ ትውልድ፣ ነገ ሀገሩን የሚረከብ ዜጋ የለውም፤ ቤቱን የሚያቆይ ምሰሶ የለውም። ልጆቻችን እርግዝናን እንደ በረከት እንጂ እንደ እንቅፋት እንዳያዩት የማድረግ ኃላፊነት በእኛ ትከሻ ላይ ነው።

ይህ “የመብት” ጥያቄ ወይም አስተያየት ሳይኾን ጃንደርብነትን የሚጠየፍ የአባወራው ትውልድ የሕልውና ዘመቻ ነው።

ሕይወትን ማጨናገፍ እንደ ጤና ጥበቃ በሚቆጠርበት ዓለም ውስጥ፣ እውነተኛው ጤና፣ ጽድቅ መፈጸም የሚችለውም ስብዕና የሚገኘው ወደ ተፈጥሮአዊውና መለኮታዊው ሕግ በመመለስ ብቻ ነው።

ልባችሁንንና ሰውነታችንን ከዚህ የጥፋት ርዕዮተ-ዓለም ጠብቀን ታናናሾቻችንንም ማስተማር አለብን። እርግዝና በረከት እንደኾነ፤ ትውልድ ማፍራት፣ ማምጣት መመገብም ደግሞ የሰማዩ አባታችንን የምንመስልበት ጸጋ እንደኾነ ማስተማር!

አለበለዚያ ግን ጠላትና የራሳችን ሆዳደር ልሂቃንና ሊቃውንት እርግዝናን እንደ በሽታ፣ እንደ እርግማን፣ እንደ እንቅፋት እንዲቆጥሩት ልጆቻችንን ከሚያስተምሩበት ፍጥነትና ስፋት የተነሳ ሀገራችን በሕጻናት ግድያ፣ ደም ማፍሰስ፣ ለአጋንንት መስዋት መኾን በሐጢያት የምትጨቀይ ትኾናለች።

ልጆቻችን ውርጃን እንደ ጤና ጥበቃ ቀለል ተደርጎላቸው፣ ያውም እንደ “መብትና ነፃነት” በራሳችን “ምሁራን” እየተማሩ ነው።

ዛሬ ዛሬ በእርግዝናቸው ከሚደሰቱት ሴቶች ብዙሃኑ እድሜያቸው ከሠላሳና እና ከሠላሳ አምስት እድሜ በላይ የኾኑት ናቸው። ሌሎቹ ግን ባለትዳሮች ቢኾኑም እንኳ የማርገዛቸው ነገር ከበረከት ይልቅ እርግማን፣ ከደስታ ይልቅ ሐዘን የሚያመጣባቸው እንደኾነ እናስተውላለን።

ለምን?

ምንም እንኳ ወዳው፣ ፈቅዳው፣ መርጣው፣ ተኝታው ከተቀበለችው ዘር ብታረግዝም ለዓመታት፦

👉 በየመገናኛ ብዙኃኑ፣

👉 በየትምህርት ቤቱ፣

👉 በየመሥሪያ ቤቱ፣

👉 በየጤና ጣቢያው(ሐኪም ቤት)፣

👉 በእምነት ተቋማትም ጭምር የሰማችው እርግዝና መቆየት፣ ቢቻል መቅረት፣ አልያም በውርጃ መጨናገፍ የሚችል እንደኾነና ይህም ከወንዱ “እኩል” የሚያደርጋት “መብትና ነፃነቷ” እንደኾነ ነው!

ስለኾነም ከባሏ ስታረግዝ እራሱ ይጨንቃታል፣ ፈልጋ የያዘችው ጽንስ ይረብሻታል፣ ጠብቃ የመጣላት እርግዝና ይከብዳታል፤ ለዓመታት ጠላትና ሆዳደሮች ከጋቷት የጥፋት ትርክት የተነሳ።

ያቺ እደድሜዋ 35 እና ከዚያ በላይ የኾነችው ግን “እየተጠናቀቀ በመጣው የእርግዝና መስኮት” (እየተጠናቀቀ በመጣው የዝውውር መስኮት እንዲሉ የእግር ኳስ ተንታኞቹ) የተገኘ ዕድል ነውና ሕመሙን ዋጥ አድርገውም ይደሰቱበታል።

ራሳቸውን የሚያዩበት፣ ዘራቸውን የሚያስቀጥሉበት፣ በሰውነታቸው በተለይም በሴትነታቸው ከከፍተኛው የጸጋቸው ከፍታ፣ የሚናቸው ልዕልና እርሱም እናትነት ላይ የሚደርሱበት በረከታቸው ነውና።

ሆድ አደር፣ የበግል ለምድ ለባሽ ሊቃውንት ግን ይህንን ጸጋዋንና ሚናዋን “ማኅበረሰብ ሠራሽ፣ ጨቋኝ በዳዩ አባወራው አመጣሽ ነው” ሲሉ ትውልድን ያጠፋሉ!

ልጆቹ ቀና ብለው የሚያዩትን አባት ኮንነውባቸው፣ በጸጋቸው የሚያፍሩ፣ የሚያቀረቅሩ፣ የሚሸማቀቁ ራሳቸውን የጠሉትን ያፈራሉ።


Post a Comment

0 Comments