✍ ናትናኤል ሰሎሞን | በማለዳ ንቁ | ኢትዮጵያ አውታር
ይሔ ዓለም የበርካታ ሥልጣኔዎች ድምር ነው፤ ከእነሱ ተሰርቷል፡፡ እነሱም በየዘመናቸው ተነስተው፣ አብበው፣ አፍርተው፣ ጨርሰዋል፡፡ እርግጥ ጥቂቶች አሉ፤ በተለይ መንፈሳዊው ነገር ማእከላቸው፣ ኀይላቸው የኾኑ ሥልጣኔዎች ጨርሰው አይጠፉም፡፡ ይቆያሉ፡፡ ተለውጠው ወይ ተሰውረው ወይም ተወስነው ይቀጥላሉ፡፡
ያለንበት ይህ የዘመናዊው ዓለም ሥልጣኔ እንደጀመረ መጠን ደሞ እየጨረሰም ነው የሚሉ ሀሳቦች ከየአቅጣጫው ይነገራሉ፡፡ በተለያየ ማስረጃና ማስተንተኛ የተለያዩ ሰዎች እንደዚህ ይላሉ፡፡ በእርግጥ እኛም ከውስጡ ነንና (እሱኑ ነንና) ዙሪያውን ስናየው ልናየው የምንችለው ብዙ ነገር አለ፡፡
የታሪክና የማሕበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች 'አንድ የዓለም ሥርዓት ውስጣዊ መፍረሶቹ ተሰበስበው መላውን ግንባታ ወደሚጥሉበት ነጥብ በመጨረሻም መድረሳቸው አይቀርም' ይላሉ፡፡ መውደቅ የሚጀመረው ከውስጥ ነው፥ ነው ነገሩ፡፡ ወንጌልም እንደዚያ ትላለች፡፡ የሚያረክሰው ከውስጥ ነው የሚወጣው፡፡
ሌላው ባለሙያዎቹ እንደሚጠቁሙት የመፍረስ ሂደቱ ሥልጣኔው በአንድ ወቅት ተነሥቶባቸውና ተመሥርቶም ዓምድ አድርጎ የቆመባቸውን ምሶሶዎች በመናድ እንደሚከናወን ይገልጻሉ፡፡
ለምሳሌ እንየው፡፡ ያለንበት ዓለም አቀፉ ምዕራብ መራሹ ሥልጣኔ በአጀማመሩና በጉልምስናው የተጠመቀው ከአራት ዋና ዋና አብዮቶች እንደነበረ ከዚህ በፊት ዳሰናል፡፡ በነዚህ አብዮቶችም ውስጥ የተገለጠው ሀሳብና ከዚያም ወጥቶ የተቀረጸው መዋቅር፣ የዚህ ሥልጣኔ ካስማዎች ናቸው፡፡ ከመስፋፋት ዘመን የተገኘው የጥቅልዮሹ አብዮት (Globalization)፣ የሳይንስ አብዮት፣ የአብርሆት ዘመን የአስተሳሰብ አብዮትና የኢንዱስትሪው ዘመን አብዮት የዚህ ዘመናዊው ሥልጣኔ መቆሚያ ናቸው፡፡ ከነዚህ ተሰርቶ ፋፍቷል፡፡
ስለዚህ ወደ ውደቀቱ መገስገስ ጀመረ ከተባለ፣ መብረክረክ የሚጀምሩት እነዚሁ መቆሚያ ጉልበቶቹ ይኾናሉ፡፡ የዚህን እንዴትነት ሰዎች በኑሮም፣ በሚዲያም ጊዜ ሰጥተው ቢፈትሹ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ለመጥቀስ ያህል ግን አንዳንዶቹን በገረፍታ ብናወራቸውስ?
1. አልቦ ፍትሕ ዕድገት (Economic Inequality)
በተለይ በከተሜው ዓለም የምናውቀው የኢኮኖሚው ሥርዓት፥ ከጥቅልዮሹ፣ ከሳይንሱና ከኢንደስትሪው ከነዚህ 3 አብዮቶች እንደተደራጀ ይታወቃል፡፡ ካፒታሊዝም አእምሮዉ ነው፡፡
እኛም በዚያ ውስጥ ገንዘብን መተሳሰሪያ አድርገን እንኖራለን፡፡ እንሰራለን፡፡ ታዲያ ይሄ ጥልፍልፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ አድሎቱ ለላይኛው እርከን ተቀማጮች ነው፡፡ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ለሥርዓቱ ተጨማቂ ፍራፍሬ ነው፤ ወዙን፣ እውቀቱን፣ ኀይሉን ይገብራል፤ ነገ ተመልሶ እንዲመጣ የሚያረገውን ያህል ይከፈለዋል፡፡ በአጭሩ ድሀው እጅግ ብዙ ነው፤ የዓለምም ሐብት በጥቂቶች ይዘወራል፡፡ ፍሰቱ ፍትሕ አልባ ነው፡፡ ይሔ በሂደት ሕዝቦች ላይ ሥነ ልቡናዊም፣ አካላዊም ድቀት እያመጣ ይታያል፡፡
ለመኾኑ ድህነት ግን ምንድነው? ሐብታምነትስ? በነገራችን 2ቱም ተፈጥሮ ውስጥ የሉም፡፡
2. የተፈጥሮ ሐብት ብዝበዛ (Environmental degradation)
ከላይ የጠቀስነው ግዙፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ ጥሬ ዕቃው ያው ተፈጥሮ ነው፡፡ አለበዚያ ከየት ያመጣል? ወደ ኢንደስትሪዎች ምድጃ የምትጣደው ተፈጥሮ ናት፡፡
ሥርዓቱ ከአግበስባሽነቱ የተነሳ በቃኝ አያውቅም፡፡ ሰንበት የለውም፡፡ ያመርታል፤ ያመርታል፤ ያመርታል፡፡ በዚሁ አንጻር የተፈጥሮንም ሐብት እያወጣ ይጠቀማል፡፡ ገጠሮችን የማከተሙ ሥራ (urbanization) ሚዛን መጠበቂያ የለውም፡፡ ስለዚህ ከአየሩ እስከ አፈሩ ኹሉም ተለውጦአል፡፡ የምንበላውና የምንጠጣው ጭምር፡፡ አስተሳሰባችንም እንዲያው ነው፡፡ እና አከባቢውን ያልጠበቀ፣ ከተፈጥሮ ያልታረቀ ሥልጣኔ ውድቀቱም ከዚያው ዘንድ ይደገስለታል፡፡
3. ሕይወት አልባ ተቋማት
ሀሳቦች ይነሳሉ፤ ከነሱም ዘንድ ሥርዓቶች ይዘረጋሉ፡፡ ተቋማት እነዚህን ሥርዓቶች የሚያስፈጽሙ ቅርጾች ናቸው፡፡
ይኹንና ሥልጣኔ ዕድሜውን ሲጨርስ የተነሳባቸው ሀሳቦች ያረጃሉ፡፡ ያኔ ተቋማት ሥጋቸው ብቻ ይቀራል፡፡ ነፍስ የላቸውም፡፡ ይሔን ከፖለቲካው እስከ ማሕበረሰብ ተቋማት ድረስ ዛሬ ላይ ማየት ነው፡፡ ከሕዝብ ልብ ተለያይተዋል፡፡ የሚገርመው ቤተ እምነታዊ ተቋማትም የዚሁ ገፈት ተቃማሽ ኾነው መታየታቸው ነው፡፡ ይልቁን እንደውም ባይብሱ ነውን? መከዳው በመዋቅር የለም፡፡
4. የሕልውና ትርጉም መጥፋት
ሰው የሚኖርለት ነገር ያሻዋል፡፡ ነፍስ ስላለቺው በእንጀራ ብቻ መኖር አይችልም፡፡ የሕልውና ጥያቄ አለበት፡፡ ምንድነው ሰው መኾን?
ይህ ዘመናዊው ሥርዓት፣ ማሰቢያ ልቡ ሳይንስ ነው፡፡ የአብርሆቱ ዘመን አመክንዮአዊነት ደሞ ናላው፡፡ ችግሩ ሳይንስ ወደ ውስጥ ቅጥር አይዘልቅም፡፡ ሥጋን እንጂ ተስፋን አይመረምርም፡፡ ምክንያታዊነትም በበኩሉ ኹሉን አይበይንም፡፡ ሕይወት ከነዚህ ትሰፋለች፡፡ እነ ታማኝነት በሳይንስ አይለኩልንም፡፡ የአብርሆቱ ዘመን የአስተሳሰብ ንቅናቄ እንዳለው ግለሰባዊነት የራሱ ጥቅም ቢኖረውም፥ የጋራ ከተማና የሰውነት ግብም ያስፈልገን ነበረ፡፡
ድብርት፣ ግራ መጋባት፣ መሄጃ ማጣት፣ ባዶነት አኹን ሕዝባዊያን ናቸው፡፡ በመዝናኛ፣ በወሲብ፣ በዐመፃ የምንታገላቸው፡፡
5. ቴክኖሎጂያዊ ጥገኝነት
ቴክኖሎጂ የዘመኑ ሥልጣኔ ትንፋሽ ነው፡፡ ቢቋረጥ ብዙ ነገር ይሞታል፡፡
በኢንደስትሪው አብዮት በኩል ከተፈጥሮ ስንርቅ የተቀበለን ቴክሎኖጂ ነው፡፡ ነገሩ ወደ ሥነ ልቡናችንም ሠርጿል፡፡ አኹን ሥልካችን ሥልክ ብቻ አይደለም፤ ሥራ ቦታ ነው፣ እምነት ቦታ ነው፣ የትዳር ቦታ ነው፣ የዕውቀት ቦታ ነው፡፡ ውስጡ ነን፡፡ ሥጋችን ነው መሬት የረገጠው፤ ስብእናችን ዲጂታሉ ውስጥ ነው፡፡ ትኩረት እየሸጥን አለን፡፡
ስለ መረጃ ጎርፍ፣ ስለ እውነተኛና ሐሰተኛ ዕውቀት መደበላለቅ፣ ስለ በብረት ተገናኝቶ በልብ ስለመለያየት፣ ስለ ሳይበር ጥቃት፣ ስለ AI ሰውን ተኪነት አልዘረዘርንም፡፡ ሌላው የትርምሱ አካል ቢኾንም፡፡
6. ራእይ ማጣት
አንድ ግንባታ ሲጀምር በትጋትና በሕግ ነው የሚጓዘው፡፡ ተፈላጊው ነገር ከተገነባ በኋላ ሌላ የሚገነባ ሀሳብ ከሌለ በዕረፍት ስም እናጠፋለን፡፡ ራእይ ነው ቀጣዩን ነገር የሚያስቀጥለው፡፡ ያለእሱ አንሄድም፡፡ እንቆማለን፡፡
ይሄም የ500 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው ሥልጣኔ፣ ከውጥኑ እስከ ከከፍታው በታላቅ ትጋትና ውጥረት ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ማፍራት ያለበትን ኹሉ አፍርቷል፡፡ መሠረቱን የጣለው በሳይንስ ነውና በተለይ በሚታየው በኩል ብዙ ነገር ሰርቷል፡፡
ነገር ግን እርጅናው ሲመጣ ቀጥሎ የሚወስደውን ራእይ አልተለመም፡፡ አኹን የዓለምን መንግሥታት ሰብስበን ለመኾኑ ዜጎቻችሁን ወደየት እየመራችሁ ነው ቢባሉ መልስ የላቸውም፡፡ ይሄ ሥልጣኔ የራሱ ከነዓን ጋ ደርሶአል፡፡ ስለዚህ ሙሴው ሞቶአል፡፡
እርግጥም ሕግ ከላይ እስከታች ሞቶአል፡፡ ከትንንሽ እስከ ትልልቅ ድረስ ያሉ ሕግጋት በጠመንጃ ነው የሚጠበቁት፡፡ ወይም በመደለያ፡፡ ይሄ የትም ያለመኼድ ቀንደኛ ምልክት ነው፡፡
ስለዚህ ምን እናድርግ? ብዙ ነገሮችን ስለ ዘመናዊው ዓለም ሥርዓት እየጠወለገ መኼድ ማውራት ይቻላል፡፡ ውስጡ ስላለን እኛም እየሰማነው ነው፡፡ ምን እናድርግ?
ሕይወት እስከቀጠለ ድረስ ትውልዶችም ይቀጥላሉ፡፡ ሥልጣኔዎች ዕድሜያቸውን ስለጨረሱ መወለድ የሚያቆሙ ሰዎች አይኖሩም፡፡ ፍጥረት ይቀጥላል፡፡
ይህ ከኾነ የዘመኑ ሀሳብ እየወደቀ ባለበት አንጻር እየተነሳ ሊመጣም ግድ የሚለው ሥርዓት መኖር ይገባዋል፡፡ ሽግግር በዚህ መካከል አለ፡፡ ልብ እንስጥ፡፡ ልብ እንበል፡፡ ሥልጣኔ የሚነሳው ከሰው ነው ፤ መንፈሳዊ መሠረትም ቢኖረው፡፡ ስለዚህ የሚመጣውም ነገር የሚወጣው ከእኛው ነው፡፡ እሱም ሲቀር እየፈረሰ ያለውን ደሞ መቋቋም የእያንዳንዳችን ነው፡፡ ተጠባቂ ተዓምር የለም፡፡ ምን እናድርግ ስለዚህ? ሦስት ነጥቦችን በአጭሩ፡፡
፩. ልብን መታዘዝ
እውነት በሰው ልብ አለች፡፡ የመገለጧ አድማስና ከፍታ ቢለያይም እኛ ውስጥ አለች፡፡ ስለዚህ ነው ስንዋሽ ኹሌ ውስጣችን የሚያውቅብን፡፡ ከራሱ መደበቅ የሚችል አለ?
በኛ ኹሌ እውነታውን ብቻ የሚናገር፣ የሚመራ አለ፡፡ ልቦና እውነተኛው ሀሳባችን ነው፡፡ እሱን መታዘዝ ከውስጣዊ ቀውስ ለመዳን ግድ ይላል፡፡ በተረበሸው መካከልም ሰላም የመኾኛው መንገድ ነው፡፡ አይብራራም፡፡ በቃ ግብር የሚገቡት ነው፡፡
በነገራችን ቂምና እውነት በአንድ ልብ ውስጥ አይኖሩም፡፡ ያለብን ቂም ካለ እንተው፡፡
፪. ማሕፀኑን መፈለግ
አስቀድሞ አላልንም? ሀሳቦች ናቸው ሥርዓት የሚዘረጉት፡፡ አኹን በዙሪያችን ተገንብቶ የምናየው ብዙ ሥርዓት፣ በፅንስ ዘመናቸው የሚወጡና የሚወርዱ ሀሳቦች ነበሩ፡፡ እነሆ ተሻጋሪውን ሀሳብ የሚፈልጉ ብፁዓን ናቸው፤ ያስቀጥሉናልና፡፡
ከክርሰትናው እንግባ፡፡ በፊት በወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስን በወቅቱ ያገኙ ሰዎች በሁለት ይከፈላሉ ብለን ነበር፡፡ አንደኞቹና የሚበዙት በዚህ ዓለም ሀሳብና ስለዚህ ሥርዓቱ ተወስነው የሚቀሩት ናቸው ብለናል፡፡ በሥጋቸው፣ ለሥጋቸው የሚያገኙቱ ናቸው፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ካገኙ በኋላ "በሰላም ወደቤታችሁ ተመለሱ" የሚባሉት ናቸው፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን ካገኙት በኋላ ወደቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ በተገኙበት ዘመን ሥርዓትና እንደ ግልም በኑሮአቸው ሀሳብ የሚቀጥሉ ናቸው፤ እነዚህ አብዛኛውን የዓለም ሰው (በክርስትና ምእመን) የሚወክሉ ናቸው፡፡ አኹን እዚህ የተጻፈው ራሱ አይኾናቸውም፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤታቸው የሚኼዱ ናቸዋ፡፡ ወደነበረው ሥርዓት፣ ወደነበረው ሀሳብ የሚመለሱ ናቸው፡፡ 75% የዓለም ሕዝብ ናቸው፡፡ በቃ የሚበሉት ጋ፣ የሚጠጡት ጋ፣ ትዳራቸው ጋ፣ በጥቅሉ በሥጋ መቆየት የሚባለው ጋ ናቸው፡፡
ሁለተኞቹ ደሞ አሉ፡፡ በዋናነት ሐዋሪያት፡፡ በአስኳልነት ድንግል ማርያም፡፡ እነዚህ የሚከተሉቱ ናቸው፡፡ ከብዙሀኑ የወጡት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ወደቤት አይኼዱም፡፡ በኼደበት የሚኼዱቱ ናቸው፡፡ አበው ሐዋሪያትን ሲናገሩ በዋለበት የዋሉ፣ በአደረበት ያደሩ ይሏቸዋል፡፡
እነዚህ ካገኙት በኋላ ወደቤት (ወደነበሩበት) ስለማይመለሱ፣ ከነበረው ነገር ኹሉ እየወጡ እየወጡ የሚኼዱ ናቸው፡፡ ከነበረው ሀሳብ፣ ከነበረው አኗኗር፣ ከነበረው ከዘመኑ ነገር እየወጡ ይኼዳሉ፡፡ ለምሳሌ ማቴዎስ አስቀድሞ ቀራጭ ነበር፡፡ በነበረበት ዘመን ለነበረው የሮማ ሥርዓት ተገዢ ነበረ፡፡ እዛ ውስጥ ይመላለሳል፡፡
ና ተከተለኝ ሲለው፣ ከዚህ ውስጥ ነው የሚጠራው፡፡ ተይዞ ይኖርበት ከነበረው የግልም የማሕበረሰብም ሀሳብ ውስጥ ነው የሚጠራው፡፡ ዘመኑ ካመጣው ሀሳብም ውስጥ ነው ና የሚለው፡፡ ከዚያ ዘመን ሥልጣኔም ጭምር እንደማለት፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ ከመገለጡ በፊት፣ በዘመኑ የነበረው በሮም ሥነ መንግሥት የሚመራው ሥልጣኔ ጊዜው እየጨረሰ መጥቶ ነበረ፡፡ ሮም እየደከማት ሳለ ነው የመጣው፡፡
ስለዚህ ተማሪዎቹን ተከተሉኝ እያለ ሲጠራቸው፣ በኋላ በነሱ በኩል አዲስ ለሚነሳው ሀሳብም ደሞ ነው የሚጠራቸው ማለት ነው፡፡ አስቀድሞ የነበረው ሥልጣኔ ሲወድቅ፣ ክርስትና ቀጣዩን ተረክቦ አዲስ ኾኖ ጀምሯል፡፡ በነዚሁ በተከተሉት ሰዎች ምክንያት፡፡ የምለው ግልጽ ነው?
እነዚያ ወደቤታቸው የኼዱቱ ብዙሃኑ፣ በነበረው ሀሳብ መኖር ቀጥለዋል፡፡ ቀድሞ በተዘረጋው ሥርዓት ውስጥ ይመላለሳሉ፡፡ እነ ማቴዎስ ግን እንዲያ አይደለም፡፡ ወደ አዲስ ሥርዓት (ትንሳኤው፣ ዕርገቱ፣ በዓለ ሐምሳ) ሊኼዱ ተከትለውታል፡፡ ከዚያም ተከትለው ከደረሱበት ነጥብ ተነስተው የዓለምን ታሪክ ለውጠውታል፡፡ እነሆ አዲስ ሥልጣኔ፡፡ ያለንበት የአኹኑ ዘመናዊ ዓለም ሥልጣኔ እንኳ የክርስትና መነሳት ከተነሳባቸው ሦስት ተጠቃሽ መስንፈጠሪያዎች መካከል አንዱ ስለመኾኑ አንዘንጋ ፤እዚህም ዳሰነው ነበር፡፡
ነጥቡ ምንድነው? ተከተለኝ የሚለው ያላቸው ናቸው ወደ ተሻጋሪው ሀሳብ የሚኼዱት፡፡ እንደውም በሥልጣን ከተናገርን ዓለም የቀጠለው በክርስቶስ ትንሳኤ ምክንያት ነው፡፡ አዲስ ነገር የሚመግቡን በአንድም በሌላም ትንሳኤውን ያገኙት ናቸው፡፡ ትንሳኤ ለእኛ መገለጥ ማለትም ነው፡፡ የሳይንሱም አብዮት እንኳ ከራሱ አልነቃም፡፡
ዞሮ 'ተከተለኝ' ወሳኝ ጥሪ ነው፡፡ ይሄን የሚሰሙት ርሃብ ያለባቸው ናቸው፡፡ ወደ ውስጥ መጥለቅን የሚነኾልሉበት ናቸው፡፡ ተሰርቶ ከመጣው ጀርባ ሠሪውን የሚያስሱሱቱ ናቸው፡፡ በራሳቸው ለመቆም ጥልቅ መሻቱ ያላቸው ናቸው፡፡ ወደ ሰው፣ ወደ ትውልድ የሚኾንን ነገር ለመስጠት ራሳቸውን ከልብ የሰጡቱ ናቸው፡፡ የቀደመውን ለመተው ድፍረቱ ያላቸው ናቸው፡፡ አስኳሉ ጋ ለመድረስ ናፍቆቱ ያላቸው ናቸው፡፡ ሕያው ነገር፣ እውነት ነገር፣ ጥበብ ነገር፣ መልስ ነገር ለማግኘት መቃተቱ ያላቸው ናቸው፡፡ ቃል የሚወዱ ናቸው፡፡ እኛስ?
፫. ሥጋው ደሙ
"ቃሉን ተምረው ሥጋው ደሙን ቢወስዱ ሚሥጢር ያቀብላልና..." ይላል የአበው ትርጓሜ፡፡ የላይኛዎቹ ኹለት ነገሮች ጋ ያለ ሰው፣ የበጉን ማእድ ለአእምሮዉ ብርሃን ይውሰድ፡፡ ትንሳኤ መገለጥ ነው አላልንም? ሥጋው ደሙ የሚነሳው እውነት የሚቀበርበት ነው፡፡ ጳውሎስ እንደነገረን በጥምቀት (በቃሉ፣ በኑሮ) እና በሥጋው ደሙ በኩል ከክርስቶስ ጋ ከተቀበርን፣ እንዲሁ ከክርስቶስ ጋ እንነሳለን፡፡ በኛ የሚነሳው እውነቱ መገለጥ ነው፡፡ ይህም አይብራራም፡፡ ማየትን ያዩበታል እንጂ ምን ያብራሩታል?
እንግዲህ ምን እንላለን? የጀመርነውን ጨርሰናል፡፡ አንድ ነገር የምንናገረው፣ አኹን ያለንበት ዓይነተ ብዙ ቀውስ ኹሉን አቀፍ ነው፡፡ ሰዎች እነሱ ብቻ የሚናወጹ አይምሰላቸው፡፡ እርግጥ ውጊያውም ረቂቅ ነው፡፡ ዘመኑ የታደሰ አእምሮ ይፈልጋል፡፡ ተስፋ ባለዋጋ ነው፡፡ ደሞስ የተነቃነቀው ነገር ኹሉ መጽናቱ ካልኾነለት ወልቆ ይለይለታ፡፡ በርታ፡፡ በርቺ፡፡ እንበርታ፡፡ በተሻለው ያቆየን፡፡
0 Comments