ባፍጢም በወደቁት ሊቃውንት ምትክ፤ ዐዲስ ትውልድ ይነሳል!



ትውልዱን በጽድቅ ሊመሩ፣ በተለይም ወንዱን ወደ ተፈጠረበት ልኩ በእውነት መሠረት ላይ ሊያቆሙ ይገባቸው የነበሩ ሊቃውንት ባፍጢማቸው ተደፍተው ቢጥሉት ጽድቅን የተራበ፣ ፍትሕን የናፈቀ ትውልድ ትቢያውን አራግፎ ይነሳል!

ባህላችንን የሚበርዙ፣ እሴታችንን የሚደልዙና ትውፊታችንን የሚሰርዙ፣ የሚሰርዙትንም ዝም የሚሉ ሊቃውንት፤ ትውልዱ የመጣበትን መሠረት፣ የጸናበትን ምሰሶ ነቅለው፣ ከአባቶቹ ጋር የሚያመሳስለውን “አባወራዊ” ማንነት እንዲያጣ እያደረጉት ነው።

ሰውነቱን የሚበይነውን፣ ወኔውን የሚቀሰቅሰውንና ወንድነቱን የሚያጸናውን “ልቡን” አውጥተው፤ በምትኩ “ልባልባ” ያልጫ ማንነትን እየሰፉለት ነው።

ዛሬ የምናያቸው ብዙዎቹ ልሂቃን አእምሮአቸው በምዕራባውያን አስተሳሰብ የሰከረ፣ ልባቸውም የተኮላሸ ነው። ትውልዱን ልብ-አልባ፣ ወኔ-ቢስና “አልጫ” የሚያደርገውን የባዕድ ትምህርት በሥርዓተ-ትምህርት ስም ሲፈቅዱና ሲያበረታቱ፤ ከትውልዱ ኅልውና ይልቅ የዶላር ጥቅማቸው በልጦባቸዋል።

እነዚህ ሊቃውንት ራሳቸው በመንፈስ የከሸፉ “ጃንደርባዎች” በመኾናቸው፤ የሚፈለፈለውም ትውልድ እንደ እነርሱው ማንነቱን የካደ፣ ለባዕድ ጌቶች ያደረ፣ ታይታና ይኹንታ ፈልጎ የቀበጠ “ቅልጥ” ትውልድ እንዲኾን ይተጋሉ።

አባቶቻችን በደማቸው ጠብቀው ያቆዩልንን የቤተሰብና የጾታ ቅድስና፤ እነዚህ ሆዳደሮች በ“ሰብዓዊ መብት” ስም ይነግዱበታል፣ ይሸቅሉበታል ይቸበችቡታልም።

ትውልዱን ከማንነቱ ጋር ከእናት-ቤተክርስትያኑ፣ ከአባት-ባህል እሴቱ የሚያቆራኘውን እምብርት በጥሰው፣ በባዕድ አጀንዳ ልቡን አጥፍተው ትውልድ አልባ ዘር አልባ ሊያደርጉት ቆርጠው ተነስተዋል።

ሰውነቱን የሚወስነውን፣ ማስተዋያ ልቡን የሚያጠፋ ውሸትን፣ ጽድቅ የሚሠራበት ወንድነትን መክሊቱን የሚያከስም አጀንዳን “ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት” እያሉ ይግቱታል።

ሕም!

እነርሱ ትውልዱን በቀናው መንገድ ለማነጽና አባወራዊ ክብሩን ለመመለስ እንቢ ቢሉ፤ የተፈጥሮ ሕግ ግን ዝም አይልም። ከእነዚህ “የተማሩ መሃይማን” ፍርስራሽና ፍራሽ ሥር፣ የአባቶቹን እሳት የጨበጠ ዐዲስ ትውልድ ይነሳል!

ይህ ትውልድ፦

👉 እንደ ሊቃውንቱ ቁሳዊ ጥቅምን ሲያሳድድ የወጣለትና የተዋጣለት አስመሳይና አድርባይ ለመኾን አይፋጠንም፤ ጽድቅን ለመፈጸም ይቸኩላል እንጂ።

👉 እንደ ጃንደርባዎቹ ወኔው ተኮላሽቶ በታይና ይኹንታ ቅብጠት በተኮነነው ቀላጭነት ራሱን አኮላሽቶ አይገኝም፤ በተሰጠው ጸጋ ፍጹም በተለየለት ሚና በወንድነቱ ያጸናል እንጂ።

👉 እንደ ልባልባዎቹ በማንም ሸፍጠኛ የትም ለጥፋቱ አይነዳም፤ ይልቁንስ በተሰጠው የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ ሠልጥኖ፤ በልባምነት በእውነት ዓለት ላይ ይቆማል እንጂ።

እነዚህ ሆዳደር ሊቃውንት ትውልዱን የመለወጥ አቅማቸው ባፍጢማቸው ሲደፋ፤ በዐዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ የሚቀጣጠለው እውነት ግን ሀገርን ትውልድንም ትታደጋለች!

እነዚያ ሆዳቸውን ለሞላላቸው የሚደፉ፣ ሆዳቸውን በሚሞላላቸው ፊት የሚጮሁ ናቸውና፤ ትውልዱ ወደ ልቡ ከሚመለስበትን እውነት ይልቅ ቁሳዊነትን ያስተምሩታል።

የማንነትህ መበረዝ፣ የትውልድህ መጥፋት፣ የትውፊትህ ተቀባይ ማጣት፣ የባህልህ መበረዝ፣ የእሴትህ መደለዝ እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ አይደለም!

ይህ በልሂቃንና በሊቃውንቱ በተለይም በመንፈሳዊ መምህራኑ ኾን ተብሎ ሲሰናዳ የነበረ ባፍጢም በተደፉበት ልክ፣ በአስመሳይነት ሰፍተው በአድርባይነት በወደቁበት ጥግ ስር የሰደደ ስለኾነ እንጂ!

ችግሩን የሚያከፋው እንዲህ ኾነው ባፍጢም የተደፉትን “ሊቃውንት” ወይም አሰላሳዮች ሌላ የሚተካቸው የሌለ ይመስል መልሰን መላልሰን በየመገናኛ ብዙኃኑ ስናቀርባቸው፤ የትውልዱን የባርነት ሕይወት እያረጋገጥን እያጸናንም መኾኑን አላስተዋልንም!

በተጨማሪም እናንተም “ስወደው፣ ሲመቸኝ እኮ፣ ስወዳቸው እኮ....” እያላችሁ በሰማችኋቸው ቁጥር ከተፈጥሮአችሁ እየራቃችሁ፣ ከእውነቱ እየተለያችሁ፣ ልብ-አልባ ፍዝና አልጫ፣ አላዛኝና ነፍራቃ እየኾናችሁ መኼዳችሁ እንጂ፤ እነዚህንም ደግሞ በመንፈሳዊነት አጽድቃችሁ የምትታጀሩበት እብሪተኞች እየኾናችሁ ትሄዳለችሁ!

💪🌟👉 ትናንት በሕይወት ያሉት ምዕመኗም፣ ንጉሧም፣ ሊቃውንቷም፣ ካህናቷም፣ ታቦቷም፤ በስጋ የሌሉ ሰማዕታቷም በአርበኝነታቸው የሚታወቁባት ሀገር፤ ለዘመናት በተሠራ ሸፍጥ ዛሬ በሆዳደር ሊቃውንቷ መሪነት፦

☀️ ትውልዱ እውነት-እሴቱን ሰርዘውበት ልብ አልባ፣

☀️ ከተፈጥሮውና ማንነቱ የራቀ አልጫ፣

☀️ ወዶገብ ባርነቱን ያጸደቀ ጃንደርባ ኾኖባታል!

💪 ይኹን እንጂ ዐዲስ ትውልድ ይነሳል!

💪 ትንሳኤውም ከራሱ፣ የተጫነበትን የውሸት ድንጋይ አንከባሎ መውጣቱም ከልቡ ይኾናል!


Post a Comment

0 Comments