በአንዳንድ ክርስቲያኖች ዘንድ ያለ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እምነት ሲሆን፣ ይኸውም የአይሁድ ሕዝብ ወደ ቅድስት ሀገር መመለስና በ1948 ዓ.ም የእስራኤል መንግሥት መመሥረት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው የሚል ነው። ይህንን ሐሳባቸውን፣ ይደግፍልናል በማለት ከብሉይ ኪዳን የትንቢት መጻሕፍት ግዜ ያለፈባቸውን፣ እና ተፈጻሚነት ያገኙ፣ ትንቢቶችን፣ ከባህላዊና ከታሪካዊ አውዱ በመነጠል ሲጠቀሙ ይስተዋላል።
በተለይ በብሉይ ኪዳን በኋለኛው ቀናት (in the latter days)፣ኢሳ=11፣10፣ በዚያም ቀን (In that day)፣በኋለኛው ዘመን (in the latter years)፣ሕዝ=38፤8፡ የሚሉትን ምንባባት ለማስረጃነት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።
የኋለኛው ጊዜ፣ ወይም የኋለኛው ዘመን የሚለው ሐረግ ሁሉ ስለ ፍጻሜ አለም የሚናገር ነውን?
በብሉይ ኪዳን ውስጥ "በኋለኛው ዘመን" የሚለው ሐረግ 11 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። እንዲሁም "የኋለኛው ፍጻሜህ፣" "የመጨረሻው ቀን፣" "በኋለኛው ዓመታት፣" "በኋለኛው ጊዜ፣" "የመጨረሻዎቹ ቀናት" እና የመሳሰሉትን እናገኛለን። በትንቢተ ዳንኤል ላይ መልአኩ ሚካኤል "እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም" ይላል (ዳን. 12:4)።
እግዚአብሔር ኋለኛው ዘመን እያለ በትንቢት ሲያናገር፣ በቅርብ ካለው ወይም በቶሎ ከሚሆነው በተቃራኒ፣ ከብዙ ዓመታት በኋላ ስለሚመጣው የወደፊት ጊዜ ማለቱ ነበር፣ እንጂ ስለ አለም ፍጻሜ መናገር አይደለም።
ማስረጃ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፡
በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።(ዘኁልቁ 24:14)
በኋለኛው ዘመን ወደ አምላክህ እግዚ አብሔር ትመለሳለህ..። (ዘዳግም 4:30)
በመጨረሻው ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም (ኢዮብ 19:25)
ኤርምያስ 48:47፦ ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ ይላል እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 38:8፦በኋለኛው ዓመት... ወደ ምድር ትመጣለህ።
ዘዳ= 8:16፦በኋላው ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ...
ዘዳ=31:29፦በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኝኋችኋል።
ኤር= 23:20 /30:24፦በኋለኛው ዘመን ይህን በውኑ ታስተውላላችሁ።
ኤር= 49:39፦ ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የኢላምን ምርኮ እመልሳለሁ።
ሕዝ=38:16፦በኋለኛው ዘመን ይሆናል፤ ወደ ምድሬ አመጣሃለሁ።
ዳን= 2:28፦በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቆታል።
ዳን=10:14፦በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚሆነውን አውቅ ዘንድ መጥቻለሁ።
እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች "በኋለኛው ዘመን" የሚለውን ሐሳብ በተለያዩ ሁኔታዎች ይገልጻሉ፣ እንጂ፡ ስለ አለም ፍጻሜ ( የፍጻሜ ዘመን) የተነገሩ ቃላቶች ግን አይደሉም።
በተለይ ክርስቲያን ጽዮናውያን አሁን በዘመናችን ለተነሳው የኢራን እና እስራኤል ጦርነት፣ ሕዝ=ምዕ 38 እና 39፡ መዝ= 83፥ 1-18 ኤር=49፣34-39፣የሚጠቅሱ ሲሆን፣ እስራኤል በ1948፣ ሉዓላዊ ሀገር እንደምትሆን ደግሞ፣ኢሳ=11፡11-12፡ ሕዝ=22፥18-22፣ ሕዝ=36፥22-24፣ ሶፎ=2፥1-2ን ፡ ይጠቅሳሉ። ከላይ የተጠቀሱት የትንቢት ቃላት ሁሉም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ፍጻሜ ያገኙ እና ጊዜ ያለፈባቸው ነው።
የመጨረሻው ዘመን ወይም የፍጻሜ ዘመን፣ የሚለው ሐረግ ምን ማለት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች እና በሰንበት ስብከቶች ላይ "የመጨረሻው ዘመን" ወይም "የፍጻሜ ዘመን" የሚሉት ቃላት በተደጋጋሚ ይነሳሉ። እነዚህ ሐረጎች የአንድ "ክፍለ ዘመን" ወይም "የዘመን ሥርዓት" (Age) መደምደሚያንም ያመለክታሉ። ያ ዘመን ሲያበቃ "የመጨረሻዎቹ ቀናት" ይፈጸማሉ፣ ከዚያም አዲስ ዘመን ይጀምራል።
እዚህ ጋር ግን ትልቁ ጥያቄ የሚከተለው ነው፦ የተጠናቀቀው የትኛው ዘመን ነው? የጀመረውስ የትኛው ነው፣ የሚል ይሆናል? ሁላችንም እንደምናውቀው የተጠናቀቀው ዘመን የብሉይ ኪዳን ዘመን ሲሆን፣ የተጀመረው ደግሞ አዲሱ ኪዳን ነው።
ክርስቲያን ጽዮናውያን መሰረታቸው፡ ከእንግሊዝ ቢሆንም፡ በአሁን ሰዓት ዋና አቀንቃኞቹ፡ በአሜሪካ ያሉ ፡ የመሲሐዊያን አይሁድ፡የብልጽግና ወንጌል እና ጴንጤቆስጣል ሰባኪዎች ናቸው። እነዚህም ጆን ኔልሰን ዳርቢ (1830 ዓ/ም)፥ ሳይረስ ስኮፊልድ ( 1909 ዓ/ም)፥ ሃል ሊንዚይ ( 1970 ዓ/ም)፥ ዶ/ር ጆን ዋልቩርድ ( 1952 ዓ/ም የዳላስ ነገረ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ ፕሬዚደንት)፥ ዶ/ር ቲም ላ ሄይ፡ ዶ/ር ጄሪ ጄንኪን፡ ዶ/ር ግራንት ጄፍሪይ፡ ዶ/ር ጃክ ቫን ኢምፕ፡ ቻክ ሚስለር፡ ዶ/ር ማርክ ሂችኮክ፡ ዶ/ር ዴቪድ ጀረማያህ፡ ዶ/ር አርኖልድ፡ፍረችተንባም፡ ዶ/ር ዋይት ጴንጤቆስጥ፡ ፓስተር ጆን ሄግ ( ክርስቲያን እስራኤልን እንደግፍ የሚል ተቋም መስራች)፡ ፓስተር ሮን ሮድ፡ ዶ/ር ጆን ማካርተር፡ ዶ/ር ቶማስ አይስ፡ ዶ/ራንዳል ፕራይስ፡ ዶ/ር ፓውል ቤንዌር፡ ዶ/ር ሃሮልድ ዊልሚንግተን፡ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሂንድሰን፡ፕሮፌሰር፡ ቻርለስ ርይሪ፡ ዶ/ር ቻርለስ ስዊንደል፡ ዶ/ር ሪቻርድ ሂል፡ ወዘተ የመሳሰሉት ሲሆን እነዚህም አብዛኛው፡ ከሙዲ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተቋም፡ እና ከዳላስ የነገረ መለኮት መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የተመረቁ ናቸው። እነዚህ ሁለቱ በአሜሪካ የሚገኙ፡ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች፡ የቅድመ መከራ፡ ሥፍረ ዘመናት፡ ጽዮናውያን ( Pre-tribulation Dispensational zionist)፡ ትምህርትን በስፋት የሚያሰራጩ፡ በተለያየ፡ የፕሮቴስታንት ወንጌላውያን ቤተ እምነት ውስጥ የሚገኙ፡ ክርስቲያን ጽዮናውያን ናቸው።
አሁን አሁን ይህ የክርስቲያን ጽዮናውነት፣እምነት በይበልጥ በተወሰኑ የወንጌላውያን ፕሮቴስታንት (Evangelical Protestantism) ዘርፎች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም፣ ሥሩና ተጽዕኖው ወደ ተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ፖለቲካም ይዘልቃል።
የክርስቲያን ጽዮናውያን ቁልፍ ሥነ-መለኮታዊ እምነቶች
እንቅስቃሴው በዋነኝነት የሚመራው "ስለ መጨረሻው ዘመን" (Eschatology) በሚሰጡ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ነው።
የአብርሃም ቃል ኪዳን ፦
ተከታዮቹ እግዚአብሔር በኦሪት ዘፍ=12፥2-3 ለአብርሃም የገባው ቃል—"የሚባርኩህን እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ" የሚለው—ለአይሁድ ሕዝብና ለእስራኤል ምድር ድጋፍ ለመስጠት የተሰጠ ቃል በቃል የሚፈጸም የዘላለም ትእዛዝ ነው ብለው ያምናሉ። ቃል የተገባው፡ ለአብርሃም እንጂ ከ 500 ዓመት በኋላ፡ ለሚነሱት ለነገደ ያዕቆብ፡ ለእስራኤላውያን አይደለም። ይህን ለማወቅ የሥነ መለኮት ጥናት ተማሪ መሆንም አያስፈልግም።
ዳግም ማቋቋም (Restorationism)፦
ከ 70 ዓ/ም ጀምሮ የተሰደዱት አስራ ሁለቱ ነገዶች ወደ እስራኤል መሰብሰባቸው" ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው የሚል እምነትን በጽናት ያራምዳሉ። ክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም ወደ ምድር ተመልሶ እንዲመጣ ከተፈለገ፣ እስራኤል፣ ሉዓላዊ ህዝብ እና ሀገር ሆነው በፍልስጤም ምድር መስፈር፣ መኖር አለባቸው። ይህ በሆነ ከጥቂት አመታት በኋላ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ይመጣል ብለው ያምናሉ። በ1988 ዓ/ም ጌታ መጥቶ ነጥቆ ይወስደናል ተብሎ በፓስተር ሃል ሊንዚይ ቢነገርም፡ ወፍ የለም። ቀጥሎም፡ በነ ዶ/ር ቲም ላ ሄይ " Left Behind" የሚል መጽሐፍ ተጽፎ፡ በ2000 ዓ/ም በሁለተኛው ሚሊኒየም ጌታ ይመጣል፡ እንነጠቃለን ብለው፡ ያው የተለመደውን የሀሰት ትንቢት፡ ቢተነብዩም የተፈጸመ ነገር የለም።በቅርቡ የደቡብ አፍሪካ ፓስተር ጌታ በመስከረም 25/2025 በዳግም ልደት የተወለዱትን ወንጌላውያን ነጥቆ ሊወስድ ይመጣል ብሎ፡ ብዙ ሰዎች መደበኛ ሥራቸውን፡ ትተው፡ ቤታቸውን፡ ንብረታቸውን ሽጠው፡ ትምህርታቸውን አቋርጠው፡ ትዳራቸውን እና ልጆቻቸውን በትነው፡ ሲጠብቁ ምንም ሳይፈጸም ቀረ።
ዘመነ-ሥርዓት ወይም ሥፍረ ዘመን (Dispensationalism)፦
ብዙዎቹ ክርስቲያናዊ ጽዮናውያን እግዚአብሔር በሰባት የተለያዩ "የኪዳን ሥርዓት ዘመናት" (dispensations) ውስጥ እንደሚሠራ ያምናሉ። አሁን ያለው ዘመን የእስራኤልን ምድራዊ መታደስ እና ውሎ አድሮም የሦስተኛውን መቅደስ ዳግም መገንባትን ይጠይቃል ብለው ያምናሉ።ይህንን ለማሳካት ቀይ ጊደር ፍለጋ፡ ተራራ ሲወጡ፡ቁልቁለት፡ ሲወርዱ ቢውሉም ምንም የተለየ፡ የተለወጠ ነገር የለም።
ፖለቲካዊ ተጽዕኖና ንቅናቄ
ክርስቲያናዊ ጽዮንነት የግል እምነት ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከፍተኛ ድርጅታዊ መዋቅር ያለው፡ በከፍተኛ ባጀት ተመድቦለት የሚንቀሳቀስ፡ የፖለቲካም ኃይል ነው።
ተፅዕኖ መፍጠር እና በአለም ላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ማግባባት ላይ አጥብቀው ይሰራሉ(Lobbying)፦
በፓስተር ጆን ሄግ የተመሰረተው፣ "ክርስቲያኖች ለእስራኤል አንድነት" (CUFI) ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት ያሏቸው ድርጅቶች፣ የአሜሪካ፡እና የአውሮጳ፡ መንግሥታት ለእስራኤል ጠንካራ ወታደራዊ ፡ዲፕሎማሲያዊ፡ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፡ የኃይል አቅርቦትና፡ የስለላ፡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ግፊት ያደርጋሉ።
የገንዘብ ድጋፍ፦
ብዙ ቡድኖች ለአይሁዶች ወደ እስራኤል መመለስ (Aliyah) እና ዮርዳኖስ (West Bank) ለሚደረጉ የሰፈራ ፕሮግራሞች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ። ብዙዎችም አይሁድ ነን እያሉ፡ በአዳዲስ ሰፈራዎች ላይ፡ እንዲቀመጡ፡ አስፈላጊውን ከቁሳቁስ ጀምሮ፡ ማንኛውንም ድጋፍ ያደርጋሉ
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፦
ይህ ንቅናቄ እንደ እ.ኤ.አ በ2018 በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት፣ አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ ኢየሩሳሌም ለማዛወር ላሳለፈችው ውሳኔና መሰል የታሪክ ለውጦች ትልቅ ምክንያት ነው። ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ከተማ ነች፡ በማለት በተለይ ዶናልድ ትራምፕ ለክርስቲያን ጽዮናዊነት፣ እንደ ትሮይ ፈረሰ ሆኖ የሚያገለግል፣ጉዳይ አስፈጻሚ መሳሪያቸው ነው። ሰሞኑን ከኢራን ጋር ለገባበት ጦርነት ድል እንዲቀናው፣ከበውት ሲጸልዩለት፣ የነበሩት አብዛኛው፣ የክርስቲያን ጽዮናዊነት አቀንቃኞች የሆኑ ፓስተሮች ናቸው።
አመለካከቶችና ውዝግቦች የክርስቲያን ጽዮናዊነት እንቅስቃሴው እንደ ሃይማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ እይታው ሁኔታ በተለያዩ መንገዶች ስለሚታይ፣ በተለይ በሉተራን፣ በካልቪኒስት፣ በአንግሊካን፤ በሜኖናይት፣ በባፕቲስት እና በአብዛኛው ወንጌላውያን ዘንድ ቅቡልነት የለውም።
ክርስቲያን ጽዮናዊነት፣ በአሜሪካ ውስጥ በማኅበራዊ መገናኛው፣ ፕሮፓጋንዳውን ስለተቆጣጠሩትና የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት፣ ስለሚያስጮኹት ነው እንጂ፣ በአብዛኛው፣ ነባር ፕሮቴስታንቶች ዘንድ የሀሰት አስተምህሮ አራማጆች፡ የሐሳዌ መሲህ መንገድ ጠራጊዎች፡ ተብለው የሚፈረጁ ናቸው።
ምንጭ፡
- Israel 1948 Countdown to Nowhere. P.1-66
- Whose Land is Palestine. The Middle East Problem in Historical perspective. p.104-230
-The Invention of the land of Israel. from Holy Land to Home Land.
- The Invention of the Jewish People.
- Prophecy and the Church. p. 218-255.
- DNA Science and the Jewish Bloodline. P.45-98.
- On the Wrong Side of Just about Everything But Right about it All. p. 81-86.
- The End of America? Bible Prophecy and a Country in Crisis. p.61-80
- End Time Delusions. The Rapture, the Antichrist, Israel and the End of the World. p.173-180.
- Armageddon, What the Bible Really Says about the End. P. 92-108.
- The Thirteenth Tribe. p. 181-202.
- The Case for Zionism.Why Christians Should Support Israel. p.27-87.
- Israel in Prophecy a Chronology. p.29-76.
0 Comments