በፍቅር ትውልዱ ባልጫነት ለባርነት ይገራበታል!


ባልጮች ክርስትና፣ በምንደኞችም ስብከት "ፍቅር" በእውነት ለጽድቅ የተፈጠረው ትውልድ የሚታነጽበት ሳይኾን ባልጫነት ለባርነት የሚገራበት ልጓም ነው!

“ፍቅር” የሚባለው ቃል ዛሬ ትውልድን አፍዝዞ ለባርነት የሚያዘጋጅ መንፈሳዊ ማደንዘዣ፣ ዘመናዊ ማጋዣ (ግዞት፣ ለባርነት የሚያግዝ፣ የሚያጓጉዝ) ኾኗል።

በአልጮች ክርስትናና በምንደኞች ስብከት የሚረጨው ይኸው “ፍቅር፤ በእውነት ለጽድቅ የተፈጠረውን ትውልድ ክንድ አልባ፣ ወኔቢስ የሚያደርገውና ለባርነት የሚገራበት ልጓም ነው። ይህም ትውልዱን የወጣለትና የተዋጣለት፣ የተማረና ባለማዕረግ እንከፍ እያደረገው ይገኛል።

👉 ፍቅርን ማን ይጠላል?

👉 ፍቅርንስ የመሰለ አንድነትን አጥባቂ ከወዴት ይመጣል?

👉 “ፍቅር፣ ፍቅር” ሲባል የሚከፋውስ ማን ይኖራል?

👉 “በፍቅር አምላክ” ሲባልስ የማይሸነፍ ማን ይኾናል?

ይህንን እኛ ብቻ አይደለንም የምናውቀው፤ ጠላትም እንዲሁ ከእኛ ይበልጥ አበጥሮና አንጠርጥሮ ያውቀዋል እንጂ። ለምን? ማጥቃት የሚፈልገውን ሁሉ በጥላቻ ሳይኾን በፍቅር መርታት ውጤቱ አመርቂ፣ ዘላቂና ይህም ታዋቂ ስለኾነ።

ትውልዱን ዐለም በጽድቅ በፍትሕ ከምትጣፍጥበት መሥዕዋትነት፣ ሰማዕትነት ለይተው የአልጮችና የምስኪናን ስብዕና እንዲላበስ በፍቅር ስም ይሰብኩታል።

በተለይም ወንዱ በተፈጥሮው የታደለውን ራሱን፣ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ቤተሰቡን፣ ማኅበረሰቡን፣ ሀገሩን፣ እምነቱን፣ እሴቱን ከባላጋራ ይጠብቅበት ዘንድ የታደለውን ወንድነት መክሊቱን፦ የጀብደኝነቱን ግርማ፣ የአባወራነት ማማ፣ የአርበኝነት አርማ፤ “እንሰሳዊ፣ ስጋዊ” እያሉ በመኮነን ስልብ ጃንደርባ እያደረጉት ይገኛሉ።

ይህ ባጋጣሚ የሚኾን አይደለም!

ጠባቂነት፣ መከታነት፣ ጋሻነት፣ አለኝታነት የሚጠበቅበት ወንዱ ክፉን የማይቃወም፣ ለጽድቅ የማይጨክን፣ ለፍትሕ የማይሟገት “ንክርርርር ያለ ምስኪን ኾኖ እንዲቀር ተፈርዶበታል።

አስረጅ፦ የዛሬዋን እንግሊዝና አውሮፓን ተመልከቱ! ኾን ተብሎ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ በፍቅር ስም በተዘራ እንክርዳድ አባታዊ ግርማቸውን፣ አርበኛዊ ወኔያቸውን፣ አባወራዊ ሚናቸውን ተነጥቀዋል።

ወኔው ተሟጦና ተንጠፍጥፎ እንዲወጣ የተደረገው ትውልዳቸው ዛሬ ማንነቱን አጥቶ፣ የቆመበት እትብቱ የተቀበረበት መሬቱ ከድቶት እየተናደ(እየጠፋ) ነው።

👉 ሴቶቻቸውና ደካሞች ጥቃት ሲደርስባቸው የሚከላከልላቸው ወንድ ከወንድም አባወራ በማጣታቸው ለውርደት ተጋልጠዋል።

👉 መንግሥት የልጆቻቸውን ባለአደራነት ነጥቋቸው፣ ሕጻናቶቻቸውን እንደ ግል ንብረቱ ቆጥሮ ጾታቸውን እንዲቀይሩ፣ የሥርዓተ ጾታና የሥነ-ተዋልዶ ጤና (sexual education) እንዲጋቱና እንዲጠፉ “ክፉን በክፉ አትመልሱ” ሲሉ ከዐውዱ ነጥለው በፍቅር ስም ባርነትን ባስተማሯቸው ለጥፋት ተሰጥተዋል።

👉 ቤተክርስትያናቸው “በፍቅር ያለ ልዩነት በእኩልነት ባሳተፈ” ሂደት ሴቶቻቸውን ከቤት ወደ ሀገረስብከት ለጵጵስና ስታመጣ፣ የግብረሰዶማውያን መናኻርያ ስትኾን መቃወም ያቃታቸው፤ ትናንት ሊቃውንቱ በፍቅር ስም ለእውነት የሚጨክንና የሚሟገት ወኔያቸውን ስለሰለቧቸው ነው።

እኛ ጋርስ? “ነግ በኔ” ብለህ ስማ ሥራም!

በተግባር የተገለጠ፣ በሕይወት የታየ፣ በኑሮ የተገለጠ ፍቅርንማ አባቶቻችን አሳይተውናል እኮን! ለእነርሱ ፍቅር ማለት ጠላትን በዝምታማስተናገድ፣ ክፋትን “አሜን ይኹንብኝ ይደረግብኝ” ብሎ መቀበል፣ ባርነትንም “በጄ” ብሎ መገዛት አይደለም!

የሀገርን፣ የሃይማኖትን፣ የቤተሰብን፣ ሕልውና፣ ሊያጠፋ የመጣን ጠላት፤ እርሱ ሳያጠፋቸው ቀድመው ያጠፉት ዘንድ በሠለጠኑበትና በታጠቁበት ልክ ድለኛ ክንዳቸውን አሳርፈውበታል።

እንደ እኔና እንዳንተ እንደ አንቺም ላሉት የልጅ ልጆቻቸው “ባርነትን አናወርሳቸውም” በማለት ልጆቻቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀብት ንብረታቸውን ጥለው ዘምተው በሰማዕትነት አልፈዋል። ነፍሱን ስለወዳጆቹ አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ከየት ይገኛል? ዮሐ 15፥13

ታናሼ! አባቶቻችን በኑሮ የሰበኩት ፍቅር ዛሬ ዛሬ ለልስልስ፣ ስልምልም፣ ቅልስልስ ሰባኪያን በአዞ እንባቸው እንደሚረጩት ሕይወት የተለየው የሞተ አይደለም!

እነርሱ በትውፊት የተቀበሉት፣ የነበራቸው እሴት፣ ያቀበሉንም ለእኛ ለጉስቁልና የሚዳርግ የአልጮች ፍቅር ሳይኾን ጽድቅን የሚፈጽም የአርበኞች፤ በጃንደርብነት ለባርነት የሚመለመሉበት ሳይኾን በአባወራነት ለነጻነት የሚሰፍኑበት ነው!

ወንድምዓለም! የሀገር ትንሳዔዋ ካንተ ከልብህ ይጀምራል። በራስህ ላይ ሠልጥነህ፣ ለቤተሰብህ ጽናት ቆመህ ለጽድቅ ጨክነህ ካልተነሳህ፤ በምንደኞች የፍቅር ስብከት ለባርነት ተገርተህ አልጨህ(demoralized) ትቀራለህ።

“እንትና የሚባለው ሰባኪ ሲመቸኝ፣ በእንትናማ አትምጣብኝ፣ እርሷቸውን ደግሞ ስወዳቸው....” እነዚህ ሐረጋት እውነትን የምር ከልቡ ሲያገኛት ሊኖርባት ከሚፈልጋት ሰው አንድበት ሊወጡ አይገባም! እውነትን ይናገራሉ ለሚባሉትም መግለጫ አይውልም!

ዛሬ ግን ግብዣ ድግሳችን “የዩቲዩብ ዕይታ፣ ላይክና ሰብስክራይብ ያስገኛል፣ መድረክ ያደምቃል፣ ሰዉም ይወደዋል፣ እያዝናና ቁምነገር ያስተምራል” እንጂ “ጣፈጠም መረረም ደረቅ እውነትን ይናገራል፣ ትውፊት ያቀብላል” ያሉትን አይጠሩም!


Post a Comment

0 Comments