✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ታሪክን መናገር አይደለም! ብሶትና ሮሮን ፈልጎና ፈልፍሎ ወደ አደባባይ በማውጣት በእውነት፣ በእምነትና በእሴት ላይ ትውልዱን ማሳመጽ እንጂ!
በየመድረኩና በየመንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት (NGOs) ሰርጥ “Storytelling” (ትረካ) የሚል ቃል እንደ አዲስ ግኝት ይነፋል።
ነገር ግን ይህ ቃል ታሪክን ለመዘከር ወይም እውነትን ለመግለጥ የመጣ አይደለም። ይልቁንም የድሮው ማርክሳዊ የጥል ቀመር ስሙን ቀይሮ፣ ብሶትን አቆላምጦና አኳኩሎ ትውልዱን በገዛ ማንነቱ ላይ ለማሳመጽ የተዘጋጀ የመርዝ ጽዋ ነው።
ይህ “Storytelling” የሚሉት ድራማ፣ ማርክሳውያንና ፌሚኒስቶች “የጭቆና ምንጭ ነው” የሚሉትን ነባር እሴት በማፍረስ ማኅበረሰብን ለመበተን የሚጠቀሙበት የቆየ ስልት ነው።
ድሮ በማኦኢስት ቻይና “Spitting Bitterness” (ምሬትን መትፋት) ይሉት ነበር። ስልቱ ቀላል ነው፦ በቤተሰብ መካከል ያሉ ጥቃቅን አለመግባባቶችን በመፈለግ፣ ፈልፍሎ በማውጣት፣ እና እነዚያን ቁስሎች በትረካ እያሳበጡ፣ እየለጠጡና እያፈረጡ “ተበድለሻል/ተበድለሃል” በሚል ጩኸት ትውልዱን ማሳመጽ ነው።
(ይህንን ጉዳይ ከዚህ በፊት የጻፍኩትን በተለይም ደግሞ ከወንድሜ አብርሃም ጋር በጠባቧ ደጅ ዩቲዩብ ያነሳነውን አስታውሰህ ከልስ)
በማኦኢስት ቻይና ማርክሳውያን ሶሻሊስቱ ማኦ ኮሚዩኒዝምን እውን ለማድረግ “ጭሰኛውን በከበርቴው”፣ ሴቶቹን በባሎቻቸው ላይ ምሬት፣ ብሶታቸውንን፣ ሮሮ፣ ለቅሷቸውን በአደባባይ እንዲናገሩት ያደርግ ነበር።
ይኸው መንገድ ለዓመጽ የተመቸ፣ የሰጠ እና ውጤታማም እንደኾነ የተረዱት ፌሚኒስቶች ደግሞ consciousness raising ሲሉ ወደ ፈጠሩት ነውጥ አስገቡት።
ዛሬ ደግሞ ግራዘመሞቹ፣ አዛኝ ቅቤ አንጓቾቹ፣ ሆድ የባሰውን ፈልገው በብሶቱ ገብተው ባርነቱን የሚያጸኑት ይህንኑ መንገድ ይጠቀሙታል።
Storytelling ይሉታል! በእርሱ የነበረው፣ የተረጋገጠው፣ ውጤታማው፣ ትውልድን ያነጸው፦ እውነት፣ እምነት፣ እሴት አይተረክበትም።
ይልቁንስ በትውልዱ በነባር እሴቱ፣ በተለይም በአባወራዊው ሥርዓት፣ እምነት ባህሉ “ደረሰብኝ፣ ጎደለብኝ፣ ተለየብኝ...” የሚለውን ምሬት ብስጭቱን እንዲናገር ይበረታታል እንጂ።
እነዚህ ሆዳደር ምሁራን ልጆቻችንን፣ በተለይም ሴቶችን፣ ይበልጡንም “ጥቃት የደረሰባቸውን” ሴቶችን(በእርግጥ በእነርሱ የብሶት ትረካ ጥቃት ያልደረሰባት ሴት የለችም) ሰብስበው “ታሪካችሁን ንገሩን” የሚሉት ቁስላቸውን ለማከም ሳይኾን፣ በቤተሰባቸው፣ በእምነታቸው፣ በባህላቸው በተለይም በአባታቸው ላይ ያላቸውን አመኔታ አጥፍተው “ሮሮአቸውን” ለፖለቲካዊ ፍጆታ ለመጠቀም ነው።
በ”Storytelling” ስም የሚካሄደው ሸፍጥ ትውልዱን “እናንቃው” (Consciousness Raising) ሲሉ የፈጠሩት የማታለያ ስልት ነው።
🚨 ሴቷ በቤቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ያላትን ውሎዋን እንድትናገር ትበረታታለች፤ ከዚያም በቤቷ ያላት እመቤትነት “ጭቆና” እንደኾነ ይነገራታል፤
ሌሎቹም ይነሳሉ፣ የእነርሱንም “ምሬት” ይተፋሉ፣ አወያዩም “መበዝበዝ፣ መጨቆናቸውን መበደል መገፋታቸውን” ያጸናላቸዋል።
የገፋ የደፋቸው አባታዊው ሥርዓት፣ እርሱን የሚያበረታታው ባህልና እምነት እንደኾነ ይነገራቸዋል። ሴቶቻችን ገና ከልጅነታቸው አፋቸውን በቅጡ ሳይፈቱ ይህንን ይማራሉ!
ይህንንም Storrytelling ይሉታል!
🚨 ወንዱ ልጁም እንዲሁ በአባቱ መመራቱ፣ የአባቱን ሥርዓትና ቅጥ ማክበሩ “ባርነት” እንደሆነ እንዲያምን ይደረጋል፤
በየወረዳው፣ በየመንደሩ፣ በየደብሩ በሚዘጋጁ የወጣቶች ክበባት፣ የሰንበቴ ማኅበራት ወጣቱ አባቶቹን ከመስማት ይልቅ መንግሥት ያጎናጸፈውን ነፃነት ተጠቅሞ ከስሩ፣ ከሕጉ እንዲያምጽ ይደረጋል።
የበዛ የአባቱን፣ የቤተሰቡን ክልከላ አልፎ ለመጣው የወረዳ የወጣቶች ክበባት አባል በ”ብሶት ትረካው” storytelling አባቱም ኾነ ባህሉ የትውልዱን ነፃነት የማይፈልግ አንባገነን ተደርጎ ይሳልለታል።
በሰንበት ትምህርት ቤትና ሌሎችም ማኅበራት ለመሳተፍ ከአባቱ ስር ከሕጉ “አሻፈረኝ” ብሎ ለሚመጣው ደግም አባቱም ኾነ ባህሉ እነርሱ በጨቋኙ አጋንንት እስራት መያዛቸውና ከእነርሱም እስራትን እንዳመለጠም ይነግሩታል።
ይህንንም Storytelling ይሉታል!
በማሳረጊያውም አባወራው ቤተሰቡን መጠበቁ “ኃላፊነት” ሳይኾን “አምባገነንነት” ተደርጎ፤ አልፎ ተርፎም የአጋንንት አሽክላ ተደርጎ በትረካ በስብከትም መልክ ይቀርባል።
ለዚህም ነው አሁን የምናያቸው እናንተ አየነኩብን፣ አይወቀሱብን አይከሰሱብን የምትሏቸው መምህራን ሊቃውንት ዘንድ ተፈጥሮአዊው የኾነው የአባወራዊው ሥርዓት፣ የወንድነት ጠል ያለባቸው፣ ከንግግራቸውም ኾነ ከአኳኋናቸው ተፈጥሮአዊው ወንድነት፣ አርበኝነት፣ አባወራነት የማይታይባቸው። ይልቁንስ ጃንደርብነትና በላጭነት ምስኪንነትና አልጫነት የሞላቸው።
ይህ ንቃተ-ህሊና ሳይኾን፣ ትውልዱ በእውነት፣ በእምነትና በአባቶቹ እሴት ላይ እንዲያምጽ የሚደረግ የጥፋት ዘመቻ ነው። ከትውልዱ ግን ይህንን ማን አስተዋለ!
“ታሪክህን ንገረኝ” እያለ ቁስልህን የሚያከውን ሁሉ አትመን፤ ያከከልህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለምና። እውነተኛ ታሪክ አርበኝነትና ጽናት እንጂ ሮሮና ብሶት አይደለም።
እነዚህ “ትረካ” በሚል ስም ብሶትን የሚያቆላምጡ ማርክሳውያንና ፌሚኒስቶች፣ ዓላማቸው መቅደስ ቤተሰብህን፣ ቤተመንግሥት ቤትህን ማፍረስ መኾኑን እወቅ። የቤት እመቤትህንም ከነዚህ “የብሶት ነጋዴዎች” ጠብቅ!
አልጨረስኩም!
0 Comments