የወሲብ ፊልሞችና ጠንቆቻቸው (ክፍል - 1)


ክፍል - 1 

በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ዝም ያለው የሚሊዮኖች ጩኸት 

ልቅ የሆኑ የወሲብ ፊልሞች መቼ እንደተጀመሩ በውል ባይታወቅም፤ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ተስፋፍተው፤ የወጣቱና የጎልማሳው የትውልድ ክፍለ ዘመን ፈተና ሆነው ሁሉም በየግል በየግል ከራሱ ጋር እንዲጣላና የሃይማኖት አካሄዶችን እንዲሸሽ ሰፊ ድርሻ የተጫወተ የአጥፊው ጥልቁ መልአክ አባዶን ሴራ ነው፡፡ 

በዘመናችን በወሲብ ፊልም ያልተጠመደ ወጣትና ጎልማሳ ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡ በተለይ የእጅ ስልክ በየግል በየግል አብዛኞቻችን እንደ መታወቂያ ካርድ ይዘነው የምንዞረው መለያችን ከመሆኑም ጋር ተያይዞ በቀላሉ የተለያዩ ድረገጾችን የማግኘት አጋጣሚዎች(Internet accessibility) በመኖሩ ሰዎች ሳይቸገሩ ወደ ወሲብ ፊልም ቁራኛነት በመግባት ለመውጣት ግን ተቸግረው ይስተዋላሉ፡፡ 

የወሲብ ፊልም ሱሰኝነት በአገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስነልቦናዊ፣ አካላዊና ማኅበራዊ ሰፊ ቀውሶችን በወጣቱ ትውልድ ላይ ለማድረስ ሆን ተብሎ በአጥፊ መናፍስቶችና የክፋት መሣሪያ በሆኑ ሰዎች የተቀናበረ የወጥመድ መረብ ሲሆን፤ ግቡንም አሳክቶ ልክ እንደ ወረርሺኝ በብዙ አገራት በመዝለቅ ሁለንተናዊ እና ዘርፈ ብዙ ቀውሶችን ከዘመን ዘመን በሚጋሽበው ትውልድ ላይ በጥልቅ መሠረት ለማስከተል ችሏል፡፡ ስለዚህም ነገር የዮሐንስ ራእይ ምን ይላል የሚለውን እንመልከት፡፡ 

(የዮሐንስ ራእይ ምዕ. 17)

3፤ በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ።

4፤ ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤

5፤ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም። ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ።

በሴት ጾታ የተገለጸው ይህ የጥልቁ መንፈስ፤ ትውልዱን በተብለጨለጨ የዘመን ውበትና መሣሪያ አነሁልሎ፤ ዜጎች ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር የሚኖራቸውን የቅደስና ሕይወት በመቀንጠስ፤ በታላቅ የዝሙት ማዕበል እንዲንሳፈፉ ያደረገ የጥልቁ አለቃ የአባዶን መንፈስ ምሪት ነው፡፡ 

ዛሬ ሲሆን የምናየው ሁሉ ምንድነው? ለምን ትውልዱ በወሲብ ግለት ነደደ? ለምን በመዝናኛው ኢንደስትሪ በኩል የሚቀርቡት  ጽሑፎች፣ ዘፈኖች እና ፊልሞች ላይ የወሲብ ድርጊቶችና የራቁትነት ገጽታዎች እጅግ በዙ? ዕድሜና የአገራትን ባሕል ሳይመርጡ ለሕዝብ ያለ ማቋረጥ የሚተላለፉ የሚዲያ ውጤቶች በብዛት የዝሙት ምኞትን የሚጠሩ ስለምን ሆኑ? ለምን የአስገድዶ መድፈር ዜናዎች፣ የጽንስ ማስወረድ ድርጊቶች፣ የእርግዝና መቆጣጠሪያና ማዘግያ ዘዴዎች ከመጠን በላይ እየጨመሩ ሄዱ?

 ምክንያቱም አበለጭልጫ በሐምራዊ ልብስ ተጋጊጣ የተገለጸቺው የዝሙት መንፈስ፤ የመጨረሻው ዘመነ ጊዜዋ ሆኖላታልና የሠራዊቶቿን የርኩሰት ጽዋ በዓለም ላይ ስላፈሰሰቺው ነው፡፡ 

የወሲብ ፊልሞች ሱስ ልክ እንደ ትምባሆ፣ አልኮልና አደንዛዥ ዕፆች ሱስ ከያዘ በቀላሉ የማይለቅ፤ ቀስ በቀስ በመቆራኘትም መላ የኑሮ አቅጣጫንና የውስጥ ሕይወትን መንገድ ወደ አንድ መስመር በመሳብ፤ የኢንተርኔትና ራስን በራስ የማርካት(ግለ-ሩካቤ) ተጠማጅ የሚያድርግ ያልተነገረለት እጅግ አደገኛ የመናፍስት ማፍዘዣ ነው፡፡ የወሲብ ፊልሞችን የመመልከት ልምምዱ ቀስ በቀስ እያደገና እንደ ግል ጠባይ እየጎለበተ የዘወትር እህል ውኃ የሚሆን መላ የስሜት ሕዋስን በዝግታ እየተቆጣጠረ የሚመጣ የአእምሮ ማስከሪያ ነው፡፡ ዝሙታዊ ፊልሞችን ለመመልከት ቀላል፤ ከማየት ለመራቅ ግን ፈታኝ የሆነበት አንደኛው መሠረታዊ ምክንያት የመናፍስት ሰንሰለትና ሰይጣናዊ እገዛ ያለበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፤ ግለሰቦች ከሱሱ ለመላቀቅ ብለው! ብለው! ሲሰለቻቸው፤ 'በራሱ ጊዜ ይተወኛል' እያሉ ተስፋ በማሳጣት እንዲኖሩ እያደረገ ነገን አጨልሞ ዛሬን በቁራኝነት የሚዋረስ አደንዣዥ ወረርሺኝም ነው፡፡

<< ቁራኛነት >> ከርኩሳን መናፍስት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያያዝ የጥፋት አሠራር አለው፡፡ ይህንን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ስለማይገነዘቡ፤ በሥጋዊ መፍትሔዎች ብቻ ተጉዘው ከጥገኝነት ችግር ለመላቀቅ በተደጋጋሚ ሲጥሩ ለጥቂት ቀናት አሊያ ሳምንታት ተሳክቶላቸው መፍትሔ ቢያገኙም፤ ዞሮ ዞሮ ወደ ተዘፈቁበት ማጥ እየወደቁ ተስፋ በመቁረጥም እንደ ልማድና አንድ የኑሮ አካል አስተናግደውት ዝም ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ዘመናዊ ነው በሚባል በዚህኛው ትውልድም፤ ግለ-ወሲብ እንደ አንድ የሥልጣኔ ክፍል ተቆጥሮ በየትምህርት ቤቱና መሥሪያ ቤቱ ቀልድና ስላቅ እየተበጀለት፤ በውስጥ ግን እየተለቀሰለት ያለ የብዙዎች ድምፅ አልባ ዋይታ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተው የወሲብ ፊልም ቁራኝነት ሲሆን ወጣቶች በጋራ ሲጨዋወቱ የሚስቁበት፤ በየግል በየግል ግን የሚያለቅሱበትና ራሳቸውን የሚጠሉበት አዚማዊ ጠባይ ያለው የውስጥ ድንዛዜንና ግዴየለሽነትን የሚያሰራጭ የርኩሳን መናፍስት የግብር ጭዳ የሚያደርግ የጓዳ የሚመስል የዓለም በሽታ ነው፡፡ 

ህቡዕ ሰይጣናዊ ድርጅቶች እንደ ኢሉሚናቲ፣ ዘ ናይት ቴምፕላርስ እና ፍሬመሰንስ ያሉት አጥፊዎች፥ ቀድመው ከጠለፉት የሴራ ድርጊቶችና የትውልድ ማደንዣዎች መካከል በሰፊ ጥናትና ዘመናትን በፈጀ የሴራ ቅንብር የተተገበረው የወሲብ ፊልም የጠምዛዥነት እቅድ(project)፤ ከፍተኛና ዓለም አቀፋዊ በጀት ተበጅቶለት፤ ዛሬ ላይ ሰለጠኑ በሚባሉ አገራት ላይ ራሱን የቻለ የመዝናኛ ማዕከል(Film industry) ሆኖ፤ ገና ከማለዳው ወጣቱን እያሰረና እያጨነገፈ፤ ከታለመለት እቅደ-ንድፍም አሻግሮ በመዝለቅ ጎልማሳና በዕድሜ የገፉ ባለትዳር የልጆች ወላጅ የሆኑ ሰዎችን ጭምር ሱሰኛ አድርጎ ያስቀመጠ ሲሆን፤ መፍትሔው ተሸፋፍኖ ያስከተለው ኪሣራ ግን የተገለጠ ደንበኛ የዲያቢሎስ ቀኝ እጅ ለመሆን ችሏል፡፡

ከኢንተርኔት ድረገጾችም ውስጥ ከ50% በላይ ሽፋን ያላቸው እነዚህ የፍትወት ፊልሞች፣ ምስሎችና ድምፆች፤ ከየትኛውም በኢንተርኔት በኩል ከሚኖሩ ድረገጾች የበለጠ ተከታታይ ቋሚ ተጠቃሚ ሰዎች እያፈሩ መሆኑን ስንመለከት፤ የአጥፊው አባዶን ሠራዊት ትውልድን የማደንዘዙ ተልዕኮ ምን ያህል ዘመናትንና ትውልዶቻቸውን አንድ'ጋ ሰብስቦ የማሰር አሠራሩን በተሳካ መልኩ ማከናወን እንደቻለ እንገነዘባለን፡፡

እንደ አሜርካ ባሉ አገራት እንደ አንድ የመዝናኛው ዘርፍ አውድና ይዘት ተቆጥሮ የልቅ ወሲብ ተዋናዮችን በመመልመልና በዓለምም ፊት በመሸለም የሥራ ዘርፍ አስመስሎ እንደ ማኅብረሰባዊ ልማዶች ለማስቆጠር በተደረገው የተጋድሎ ጥረት በኩልም የተለመደና የዘመን ለውጥ አንዱ ክፍል እንደሆነ በዘዴ ለማሳሰብና በሰው ልጆች ልቦና ላይ እንዲታተም ለማስገደድ በሙዚቃውና በፊልሙ ኢንደስትሪ አማካኝነት መጠነ ሰፊ ፕሮፖ-ጋንዳ ተሠርቶለትና ሕሊናን የመቆጣጠሪያ ቴክኒክ ተቀርጾለት በየቀኑ የሚሰራጭ በመሆኑ ከላይ ከባለሥልጣናት አንስቶ እስከ ታች ያሉ የሕብረተረሰብ ክፍላትን ጨምድዶ የያዘ አይነተኛ ልክፍት እንዲሆን በቀላሉ በእጅ ስልክና በላፕቶፕ ኮምፒውተሮች የመገኘት አቅሙን በማስፋት የአየር ሞገድ ምኅዋሩን በመቆጣጠር የሄዱበት ሚስጢራዊና መናፍስታዊ አካሄድ እጅግ የበዙ የሰው ልጆችን በአጭርና በተመሳሳይ መልኩ በማጨንገፍ ተሳክቶላቸዋል፡፡

ርኩስ መንፈሶች የሰውን ልጅ ትውልድ ሕይወት ወደ ረከሰውና በኃጢአት ወደተጨማለቀው ለመለወጥ በተለያዩ መንገዶች በሥጋዊ ድክመቱ በመዝለቅ መንፈሳዊ ሕልውናውን ለዘመናት ተፈታትነውታል፡፡ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጣቸው የበረከትና የጸጋ ማኅተም ውስጥ የተሰጠንን ታላቅ ረድኤተ-ቡራኬ ስጦታን ቀልብሰው ሥጋን በማርከስ እግዚአብሔር የተቀደሰበትና ስሙ የተጠራበት ሰማያዊ አኗኗር ከሰውነት እና ቤታችን አርቀው ዘባተሎ ኑሮን እንድንኖር የጽልመት መልአክት ይፋለሙናል፡፡ በመሆኑም አመንዝራነትና ሴሰኝነት ብዙዎቻችን ከማይታዩ ተጽዕኖዋቸው ግን ከሚታይ ርኩሳን መናፍስት የኃጢአት ግብር አስፈጻሚነት ጋር የሚገናኝ ሳይሆን ሰዎች በሞራላዊ የሥነ-ምግባር መዛነፍና መበላሸት ወይም በዘመኑ አመጣጥ የሚላከክ የአጉል ዘመናዊነት ጊዜ የመዝቀጥ ውጤት ብቻ አድርገነው ፈዘን ተቀምጠናል፡፡

በተሰወሩ የመናፍስት ወጥመድ ሥር የመግባት አንደኛው ገጽታ፤ በወሲብ ፊልሞችና ምስሎች የመለከፍ እድል ውስጥ ለመገኘት፤ በአንዳንዶች ላይ ልክ እንደተፈጥሮ አጋጣሚ የተለመደ ሁነት አስመስሎ በሕሊና ውስጥ አሊያ በሌሎች ሰዎች ግፊት እያሳመነ እንዲመለከቱት በማለማመድ እንደ ሱስ እንዲቆራኛቸው የአእምሮ ወሳኝነትን ይቆጣጠራል፡፡ አንዴ እንዲመለከቱት አጋጣሚና ሁኔታው ከተመቻቸ፤ መናፍስቱ ከውስጥም ከውጪም ሆነው በመዋረስ፤ የሰው ልጆች ከተፈጥሮና ከእምነትም ምግባር የወጣ የጋጠወጥነትና የእንስሳት ጠባይ የሚንጸባረቅበት አረማዊ ምግባር እንደሆነ በልቦና ቢረዱም፤ በፍትወት እያቃጠለ በስሜት እንዲነዱ ሕሊናን እየተጫነ እንዲለከፉበት ያስገድዳል፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥም ሦስት ደረጃዎችን ያሳልፋሉ፦

  ➊• በምናብ ውስጥ የሚያውቁትን ወይም የማያውቁትን ሰው ምስል እየሳለ የወሲብ ስሜትን ይቀሰቅስባቸዋል፡፡ ወይም ከዚህ በፊት ያዩትን የወሲብ ፊልም ደግሞ ከውስጥ ያሳያቸዋል፡፡

  ➋• ከሕሊና ውስጥ ሆኖ እንደግል አሳብ እያስመሰለ ልብ ላይ የሱሰኝነቱን አዚማዊ ኃይል ስለሚጽፈው፤ ውስጣዊ ውጊያውን በተፈጥሮ ስሜት ወስዋሽነት በኩል ገፋፍቶ ገፋፍቶ በመጨረሻም እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል፡፡

  ➌• ተመልክተው ራሳቸውን በማርካትም ሲጨርሱ ወደ ልቦናቸው በመመለስ 'ምን ነካኝ' እያሉ በራሳቸው እንዲበሳጩና እንዲሸማቀቁ እያደረገ ከውስጥ ኃጢአተኛ እንደሆኑ እየደሰኮረ ከእግዚአብሔር እንዲርቁ መንገዶችን ያመቻቻል፡፡

 መናፍስት እንዴት በወሲብ ፊልም በኩል ይዋረሳሉ?

1) ቡዳ በመሆን

ከላይ ለመግለጽ እንደምከርኩት የወሲብ ፊልሞች የጀርባ አጥንት የሆኑት መናፍስታዊ ድርጅቶች የጥፋት መናፍስቱን ለራሳቸው የተንኮል ሥራና የአመፃ ስልት ስለሚጠቀሙባቸው፤ ከኖህ ዘመን አንስቶ የነበሩት ልቡሳነ ሥጋ መናፍስት-የኔፍሊም ሠራዊት ዳግም ከጥፋት ውኃ በኋላ በድጋሚ ወደ ሰው ልጆች ትውልድ ዘልቀው የሚገቡበትን ዕድል ስላገኙ እነዚህንና የዝሙት መናፍስት እንደ ሩሃንያ አባድ የሚባሉ የጽልመት መልአክትን በግብርና በተለያየ ጭዳ በመሳብ፤ በጥንቃቄ እንደ መደበኛ ፊልም ድርሰት አዘጋጅተው በሚለቁት የወሲብ ፊልምና ምስሎች ውስጥ መናፍስቱን አዚማዊ ቡዳ እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል፡፡ በዓይን በመመልከት ብቻ በቀጥታ ውስጣዊ ሕይወትን እንዲቆጣጠሩም ተደርገው ስለሚላኩ፤ መናፍስቱ ቡዳ በመሆን የወሲብ ፊልሙን የሚያየውን ሰው ከውጪ ወደ ውስጡ ይመለከቱታል፡፡ እነዚህ ርኩሳን መናፍስት የሰው ልጆችን ሕይወት ለመያዝና በዝግታ ለመቆጣጠር የሚፈልጉት አንድ ፊልም አሊያም ምስል ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ ብዙ ሰዎች በመጀመሪያ የወሲብ ምስሎችን ያዩበት ቀንን እስከተገኙበት ዕለተ ቀናቸው እየረገሙና እየተበሳጩ መፍትሔ ባጣ አኗኗር እየዋተቱ ታስረው ታስረው ተቀምጠዋል፡፡ 

2) ቀድሞ ውስጥ ባለ መንፈስ አዚም በመሆን

ከውስጥ ያደፈጠ ማንኛውም አይነት ርኩስ ኃይል ሲገኝ፤ ከውጪ በምናስገባው መረጃ መሠረት ላይ እየተመረኮዘ፤ የማጥፋትና ወደ መሰነካኪያው ጎዳና የሚመራ ዘዴንና ስልትን በጥንቃቄ እየቀየሰ፤ ግዜያቸው፣ ኑሮአቸው፣ ሕሊናቸው፣ እፎይታቸው የሚያለቅስ ሰዎችን እየጨመረ፤ ወደ ተስፋ ማጣትና የብስጭት አኗኗር ከማማረር ሕይወት ጋር እያንደረደረ ለስቃይና ለመከራ የተፈጠርን እስክንመስል ድረስ ይፈትነናል፡፡፡ 

አንደኛው ከውጪ ወደ ውስጥ የምናስገባው መረጃ ታዲያ፥ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ጽሑፍ፣ ንግግርና የመሳሰሉትን ነው፡፡ እነዚህ መረጃዎች ለኃጢአት ግብር መንስኤ መሆን የሚችሉ ከሆነ ያደፈጠው ጠላት ይጠቀምባቸዋል፡፡ ግለ ሩካቤ ሥጋንም እንድንወድቅበት የሚያደርጉት መንሸራተቻዎች እነዚሁ የወሲብ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች፣ ጽሑፎችና መሰል መረጃዎች ናቸው፡፡

ከሠለጠኑ አገራት በከፍተኛ ግፊትና ፍጥነት እየተንሰራፋ የመጣው የወሲብ ፊልሞችና መልእክቶች ዛሬ በአብዛኛው ወጣቶች ሥልክ ውስጥ ተስግስገው፤ እንደ አንድ የእውቀትና የመዝናኛ ክፍል በመታየት የስሜት ማብረጃ እየሆኑ ውስጣዊ ማንነታችንን እየበሉት፤ በውጪ ግን እየሳቅንና እየተጫወትን የምናስመስል ፍጥረቶች ሲያደርጉን ማስተዋል ተሳነን፡፡ የሚገርመው፥ ባለትዳሮች፣ አዛውንታንና በዕድሜ ያልደረሱ ትንንሽ ልጆችንም የሚለክፈው የወሲብ ፊልም ቁራኝነት፤ እነርሱም የእነዚህ የፈረንጅ አተላ የወሲብ ግብአቶችን እንደ ሕይወታቸው አንድ የተለመደ ክፍል ይዘውት በድብቅ ይጠቀሙበታል፡፡

አሁን እነዚህን ፊልሞችና መሰል መረጃዎች የምታይ ከሆነ፤ ከውስጥም ያለው ጠላት በምታየው ነገር ልክ የምትጠፋበትንና ቁራኛ የምትሆንበትን ችግር ይቀርጽለሃል፡፡ ኦሪት ዘዳግም 28፥ 

34 ላይ " ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ።" ይላል፡፡ ምን ከምትለው የተነሣ? ዓይኖችህ ከሚያዩት የተነሣ፡፡ በእውነትም ታዲያ ከምታየው የወሲብ ፊልሞችና ምስሎች የተነሣ፤ ከራስህ ጋር እየተጣላህ በግለኝነት ጸብ የምትማስን የውስጥ ዕብድ ሆነህ ትገኛለህ፡፡ 

3) የሚዘዋወሩ መናፍስት አጋጣሚውን ይጠቀማሉ

መጽሐፍ ቅዱስ በጴጥሮስ መልእክት በኩል << ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል >> በማለት ከባቢያችን ላይ የሚያንዣብቡ ጠላቶች እንዳሉ ቁልጭ ባለ ቃል አስቀምጦልናል፡፡ ከሩቅ ያያችኋል አይደለም የሚለው፡፡ በዙሪያችሁ ይዞራል ነው የሚለው፡፡ እነዚህ የሚያንዣብቡ መናፍስት የወሲብ ፊልሞችንና ምስሎችን በምንመለከትበት ጊዜ ወደኛ ለመምጣት በር ያገኛሉ፡፡ ምን ማለት ነው ለምሳሌ አበባ ንብን እንደሚጠራ ሁሉ ዝንብ ቆሻሻ ይስባታል፤ እንዲሁ የኃጢአት ልምምዶችና የአመፃ ድርጊቶች በአየር የሚዘዋወሩትን መናፍሰት እይታ ስለሚስብ፤ ክፉውንና የረከሰውን ምግባር በምናደርግበት ቅጽበት ውስጥ መናፍስቱ ወደ ሕይወታችን ሊገቡ የሚችሉበትን ዕድል ያገኛሉ፡፡ ወደ ባሕሪያችን ሲቀላቀሉም መጀመሪያ ሲገቡ የተጠቀሙበትን የርኩሰት ምግባር ግብር አድርገው ስለሚቆጥሩት፤ በርኩሰት ልምምድ ውስጥ እንድንቀር ግብራቸውን ከውስጥ ሆነው በግፊትና በከፍተኛ ጫና በየጊዜው በተደጋጋሚ በመጠየቅ ከእስራታቸው እንዳንወጣ በተጽዕኖ ኃይል እጅጉን ይታገላሉ፡፡ 

በጥልቀትና ከእግዚአብሔር አምላክ የእውነት ቃል ጋር በማያያዝ በቀጣይ በሚኖሩኝ ተከታታይ ስድስት ክፍሎች የምዳስሰውን የሚከተሉት ርዕሶች ይዤ እመለሳለሁ፡፡

➊• የወሲብ ፊልምና የስነልቦና ጉዳቱ

➋• የወሲብ ፊልም የቱን ያህል በዘመኑ ፋሽን ዘልቆ ሄደ?

➌• የወሲብ ፊልምና የመዝናኛው ኢንደስትሪ ተያያዥነት

➍• የወሲብ ፊልምና ከእምነት መሸሽ

➎• የወሲብ ፊልም ለአስገድዶ መድፈር ያለው ተጽዕኖ

➏• ከወሲብ ፊልም ጥገኝነት እንዴት እንላቀቅ?

Post a Comment

1 Comments